ስደተኞችን ጭና ወደ ጣሊያን ስታመራ የነበረች ጀልባ ሰጥማ 11 ሰዎች ሞቱ

የቱኒዚያ የባሕር ዳርቻዎች የሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻን በማቐረጥ ወደ አውሮፓ የሚገቢ ሰዎች ወነኛ መንገዶች ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቱኒዚያ የባሕር ጠረፍ አካባቢ በደረሰ የጀልባ መስጠም አደጋ ቢያንስ 11 ሰዎች መሞታቸው የተሰማ ሲሆን ሌሎች 12 ሰዎች እስካሁን ድረስ ደብዛቸው አልተገኘም።

የአገሪቱ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች 37 ስደተኞችን አሳፍራ ወደ ጣልያን ስትጓዝ የነበረች ጀልባ መስጠሟን ተከትሎ 14 ሰዎችን ባለፈው ሳምነት ማክሰኞ ማዳን ችለዋል።

ከቀናት በኋላ ቅዳሜ ምሽት አምስት አስከሬኖች መገኘታቸውን የቱኒዚያ የዜና ወኪል የዘገበ ሲሆን ይህም የሟቾች ቁጥርን ወደ 11 ከፍ አድርጓል።

በተያዘው የአውሮፓዊያኑ ዓመት ከ1 ሺህ በላይ ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባሕርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ሕይወታቸው አልፏል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ አድርጓል።

ሕይወታቸው አልፏል ወይም ጠፍተዋል ተብለው ከሚታመኑት ከ1,033 ስደተኞች መካከል 960 ያህሉ በባሕር ውስጥ የሰጠሙ መሞታቸውን ተመድ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አሃዝ ያሳያል።

በቱኒዚያ የሰጠመቸው ጀልባ ስፋክስ ከተሰኘው አካባቢ ተነስታ 64 ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዘች በኋላ ቼባ ተብሎ በሚታወው የባሕር ዳርቻ ውስጥ ሰጠመች።

ይህ አካባቢ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ተስፋ የሚያደርጉ ስደተኞች የሜዲትራኒያን ባሕርን ለማቋረጥ የሚመርጡበት ዋና መነሻ ቦታ ሆኗል።

የባሕር ዳርቻው የጣሊያን ደሴት ለሆነችው ላምፔዱሳ ቅርብ ሲሆን የሲሲሊ ደሴትም አዋሳኙ ነው። በአብዛኛው ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመድረስ ለሚሞክሩ ሰዎች መዳረሻ ነው።

እንደ የአውሮፓ ሕብረት የድንበር ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ በዚህ ዓመት ከጥር እስከ ነሐሴ ባለው ግዜ መካከል የመካከለኛው ሜዲትራኒያን ባሕርን መንገድ በመጠቀም 52 ሺህ ሰዎች "በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ገብተዋል"።

ስደተኞቹ በዋናነት ከቱኒዚያ፣ ግብፅ እና ባንግላዲሽ የተነሱ እንደሆኑም መረጃው ያመላክታል።