ተመድ በኢትዮጵያ አስቸኳይ ድጋፍ ካላገኘሁ 750 ሺህ ስደተኞች ‘የሚበሉት አይኖራቸውም’ አለ

በግጭት እና በድርቅ መክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ታዳጊዎች በአፋር ሰመራ

የፎቶው ባለመብት, UNICEF/UN0639245/Sewunet

የምስሉ መግለጫ, በግጭት እና በድርቅ መክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ታዳጊዎች በአፋር ሰመራ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ኤጀንሲ አስቸኳይ ድጋፍ ካልተገኘ ከ750 ሺህ በላይ ስደተኞች የሚበሉት አይኖራቸውም አሉ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የስደተኞች እና የስደት ተመላሾች አገልግሎት በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ የማይገኝ ከሆነ ከመስከረም 2015 ዓ.ም. በኋላ በአገሪቱ ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞች የሚበሉት አይኖራቸውም ብለዋል።

ተቋማቱ ሊያጋጥም የሚችለው ቀውስ ስደተኞችን ለምግብ እጥረት እና በሽታ መቋቋም አቅማቸውን እንዲያጡ ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

“በአስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ ካላገኘን በሳምንታት ውስጥ 750 ሺህ ሰዎች የሚበሉትን ያጣሉ” ሲሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ እና ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር ተናግረዋል።

የእርዳታ ቅነሳ

የተባበሩት መንግሥታት ባለፉት ዓመታት ለስደተኞች ይሰጥ የነበረውን የእርዳታ መጠን ለመቀነስ መገደዱንም በዚሁ መግለጫ ላይ አመልክቷል።

እአአ 2015 በኢትዮጵያ ላሉ ስደተኞች ይሰጥ የነበረው የእርዳታ መጠን በ16 በመቶ እንዲቀነስ የተደረገ ሲሆን፣ ከኅዳር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በ40 በመቶ እንዲሁም ከአንድ ወር ገደማ በፊት የእርዳታ መጠኑን 50 በመቶ ለመቀነስ ተገድዷል።

ለስደተኞች ይቀርብ የነበረው የእርዳታ መጠን የቀነሰው በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ አቅርቦት በመቀነሱ፣ የዓለም ኢኮኖሚ ድቀት፣ የምግብ እና የኃይል ወጪ በመጨመሩ እንዲሁም በግጭት ምክንያት ናቸው።

የምግብ ድጋፍ እጥረቱ በስደተኞች ላይ ያደረሰው ተጽእኖ ለማወቅ በመንግሥታቱ ድርጅት ኤጀንሲዎች እና የስደተኞች እና የስደት ተመላሾች አገልግሎት አማካኝነት የዳሰሳ ጥናት ተከናውኗል።

ይህ የዳሰሳ ጥናቱ የእርዳታ አቅርቦት የቀነሰባቸው የቤተሰብ አባላት ችግሩን ለመቋቋም የሚመገቡትን የምግብ መጠን መቀስ እንዲሁም በቀን የሚመገቡትን ቁጥር ለመቀነስ መገደዳቸውን አሳይቷል።

“የስደተኞችን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት የ73 ሚሊዮን ዶላር እጥረት አጋጥሞናል፤ የገንዘብ እርዳታ የማይገኝ ከሆነ ደኅንነታቸው ሳይረጋገጥ ስደተኞች ወደ ቀደመ መኖሪያቸው የመመለስ አማራጭን ሊወስዱ ይችላሉ” ሲሉ ክላውድ ጂቢዳር አስጠንቅቀዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ድጋፍ ሰጪዎች የጠየቀውን ገንዘብ የሚያገኝ ከሆነ በአካባቢው ከሚገኝ ገበያ ምግብ ገዝቶ እንደሚያከፋፍል እና ተፈናቃዮች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን እንዲሟሉ እና የአካባቢውን ገበያ ለማነቃቃት ጥሬ ገንዝብ እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል።