ለግዳጅ ዘመቻ ብቁ የሆኑ ዩክሬናውያንን ከአገር ያሸሹ ወታደራዊ ባለስልጣናት ተባረሩ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዩክሬን በጦርነቱ ለግዳጅ ዘመቻ ብቁ የሆኑ ግለሰቦችን ጉቦ በመቀበል ከአገር አሽሽተዋል የተባሉ ወታደራዊ ባለስልጣናትን ከሥራ አባረረች።
ባለስልጣናቱ በሕገወጥ መንገድ ከአገር በማስወጣትና ጉቦ በመቀበል ነው ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉት።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከ30 በላይ ወታደራዊ ኃላፊዎች የወንጀል ክስ እንደሚመሰረትባቸው አረጋግጠዋል።
ወታደራዊ የግዳጅ ምልመላን በኃላፊነት ሲያካሂዱ የነበሩ ሁሉም የክልል ባለስልጣናት ተወግደዋል።
ፕሬዚዳንቱ በጦርነት ወቅት ጉቦ “ከፍተኛ የአገር ክህደት ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
የዩክሬን የመልሶ የማጥቃት ዘመቻ በቀጠለበት እና የታጠቁ ኃይሎችን ለማጠናከር እየተደረገ ባለው ጥረት ወቅትም ነው ይህ ውሳኔ የተላለፈው።
የሙስና ውንጀላዎች “በዩክሬን ብሔራዊ ደህንነት ላይ ስጋት የሚጋርጡ እና በመንግሥት ተቋማት ላይ ያለውን ሕዝባዊ እምነትን የሚሸረሽሩ ናቸው” ሲልም የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት መግለጫ አትቷል።
የጦር ሜዳ ልምድ ያላቸው እና በደኅንነቱ እና በስለላ መሥሪያ ቤቱ ማጣሪያ የተደረገባቸው እጩዎች እንደሚመረጡና እንደሚተኩም ተገልጿል።
ባለስልጣናቱ የጥሬ ገንዘብ እና የክሪፕቶ ጉቦ በመቀበል ለግዳጁ ብቁ የሆኑና እንዲዋጉ የክተት ጥሪ የተደረገላቸውን ግለሰቦች ከአገር ውስጥ አስወጥተዋል ሲሉም ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፉት ቪዲዮ ላይ ተናግረዋል።
ዩክሬን ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸውና ብቁ የሆኑ ወንዶች ለግዳጁ እንዲሰማሩ የክተት ጥሪ አውጃለች። በዚህም መሰረት ከ60 ዓመት በታች የሆኑ አዋቂ ወንዶች ከአገር እንዳይወጡ ተከልክለዋል።
“የክልሉ ወታደራዊ ኮሚሽነሮችን በሙሉ እያሰናበትን ነው” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
“ይህ ስርዓት ጦርነቱ ለዩክሬን ምን ማለት እንደሆነ በትክክል በሚረዱ ሰዎች መመራት አለበት። በጦርነት ጊዜ ጉቦ ከፍተኛ የአገር ክህደት ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
የግዳጅ ዘመቻው በትክክል እየሰራ እንዳልሆነ የተቹት ፕሬዚዳንቱ “ተዋጊዎችን የሚይዙበት መንገድ፣ ሥራቸውንና ኃላፊነታቸውን ማናናቃቸው ሥነ ምግባር የጎደለው ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
የሙስና ወንጀሉ ይፋ የሆነው በአካባቢው ባሉ ወታደራዊ ቢሮዎች ላይ ፍተሻ መደረጉን ተከትሎ ነው።
ፕሬዘዳንት ዘለንስኪ እንዳሉት በ33 የክልሉ ወታደራዊ ባለስልጣናት ላይ 112 የወንጀል ክሶች ምርመራ የተከፈተባቸው ሲሆን ይህ ሙስና በመላ አገሪቱ መከሰቱንም ተናግረዋል።












