ባለመረጋጋት እና በጫና ምክንያት የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ሥራ ማቆሙን ባለሙያዎች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Finoteselam Communication
የአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ፍኖተ ሰላም በተደጋጋሚ በነበረ ግጭት፣ ባለመረጋጋቱ እና ባለሙያዎች ደረሰብን ባሉት ጫና ምክንያት በከተማዋ ያለ ሆስፒታል ሥራ ማቆሙ ተነገረ።
ባለፉት ሳምንታት በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በክልሉ ተባብሶ በቀጠለው ግጭት ምክንያት፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ጫና መፈጠሩን ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል በጎንደር ከተማ እና በፍኖተ ሰላም ከተማ የሚገኙ ሆስፒታሎች ባለው አለመረጋጋት እና በሠራተኞች ላይ በደረሰ ጫና ምክንያት የዕለት ከዕለት ሥራቸውን በተገቢው ሁኔታ ማከናወን ከማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የሆስፒታሎቹ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በክልሉ ውስጥ ግጭቶች መካሄድ ከጀመሩ በኋላ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እና ግጭቶች ባጋጠማት የፍኖተ ሰላም ከተማ ውስጥ የሚገኘው ሆስፒታል ሠራተኞች፣ ከመንግሥት ኃይሎች “የፋኖ ታጣቂዎችን ታክማላችሁ” የሚል ጫና እየደረሰባቸው መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተመሳሳይ ጫና እንዳለባቸው የተናገሩ የጎንደር ሆስፒታል ባለሙያዎችም ባለመረጋጋቱ ሳቢያ የተፈጠረውን የአቅርቦት ችግርን ጨምሮ ከፀጥታ ኃይሎች በገጠማቸው ጫና ምክንያት በሕክምና እርዳታ መዳን የሚችሉ ህሙማን ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አስረድተዋል።
በተለይ በፍኖተ ሰላም በባለሙያዎች ላይ ካለው ጫና ባሻገር በአሁኑ ጊዜ ሆስፒታሉ መደበኛ ሥራውን እንዳቆመ ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እና ለጊዜው ከአካባቢው ሸሽተው ያሉ የሆስፒታሉ ሠራተኛ ተናግረዋል።
በፍኖተ ሰላም እና በአካባቢው ለሳምንታት ዘልቆ የነበረውን ግጭት ተከትሎ መብራት ተቋርጦ በጄኔረተር እየታገዙ ለቀናት ሕክምና ይሰጡ እንደነበር እኚህ የሆስፒታሉ ሠራተኛ ገልጸዋል።
ሆኖም ግን “ጄኔሬተሩ በከባድ መሣሪያ በመመታቱ ሥራው እንዲቆም ምክንያት ሆኗል” በማለት ሆስፒታሉ የሕክምና አገለግሎት መስጠት ለማቆም መገደዱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም “ሽፍታ እያከማችሁ ነው” በማለት ዛቻ እንደሚያደርሱባቸው የተናገሩት የሆስፒታሉ ሠራተኛ፣ በከተማው በተካሄደው ጦርነት የተጎዱ “ሰላማዊ ሰዎችንም እንዳናክም ተደርገናል” ይላሉ።
“እኛ የሕክምና ባለሙያዎች ነን፣ ሥራችን ሕሙማንን ማከም ነው። ከየትኛውም አካል ጋር ውግንና የለንም ብለን መልስ በምንሰጥበት ጊዜ የምናገኘው ምላሽ ማስፈራራት ነው” ብለዋል።
በዚህም ሳቢያ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ሥራ በማቆማቸው የሕክምና አገለግሎት መቋረጡን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላኛው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ሠራተኛ ገልጸዋል።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ከባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መስከረም 12/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ መቆሙን እና ከ120 በላይ ሠራተኞቹ መበተናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከከተማው ርቀው የሚገኙት የሕክምና ባለሙያ እንደሚሉት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ማታ ለሕክምና ገብተው “ቀዶ ሕክምና የሚያደርግ ሐኪም በመጥፋቱ አርብ ጠዋት ሁለት ወላድ እናቶች ሕይወታቸው አልፏል” ብለዋል።
ይህንን የሁለት እናቶች መሞትን በተመለከተ ሌላኛው የሆስፒታሉ ባለሙያ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
እስከ እሁድ [መስከረም 13/2016 ዓ.ም] ድረስ በቦታው እንደነበሩ የተናገሩት የሕክምና ሙያተኞቹ፣ በወቅቱ “ወደ ሆስፒታሉ መሄድ አስፈሪ በመሆኑ፣ ከዚያ በኋላ ማንም ተመልሶ አልሄደም” ብለዋል።
አንደኛው የሆስፒታሉ ሠራተኛ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ቆስለው በሆስፒታሉ ይታከሙ የነበሩ ወንዶችን እየመረጡ “የፋኖ ታጣቂ ናችሁ” በማለት ያንገላቷቸው እንደነበርና ይዘዋቸው የሄዱም እንዳሉ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
እንግልቱ በነዋሪዎች ላይም እንደሚፈጸም የተናገሩት የሕክምና ባለሙያዎቹ “የሚፈጸመው ግፍ እና በደል ከቃላት በላይ ነው፣ ወደፊት ሲወጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሆነውን የሚያይበት ዕድል ይኖራል” ይላሉ።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲን በመወከል የአማራ ክልል እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ሃብታሙ በላይነህ የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያዎች በጫና እና ዛቻ ምክንያት ሥራ ማቆማቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሐኪሞቹ ሥራ በማቆማቸው ምክንያት ለሳምንታት በዘለቀው ጦርነት በተለያየ ሁኔታ ጉዳት የደረሰባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በሆስፒታሉ ውስጥ ተኝተው ይከታተሉት የነበረው ሕክምና ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል ብለዋል።
የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ሐኪሞቹን “የፋኖ ደጋፊ ናችሁ። እናንተ ናችሁ እኛን እየወጋችሁን ያላችሁት” በማለት በሚያደርሱባቸው ጫና ምክንያት ሆስፒታሉን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል ብለዋል አቶ ሃብታሙ።
በአሁኑ ወቅትም የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ ሥራ በማቆሙ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በባህላዊ የመጓጓዣ መንገዶች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሂደው ለመታከም መገደዳቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ከአካባቢው ባለሥልጣናትም ሆነ ከመከላከያ ሠራዊት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ የተነሳ አልተሳካም።
በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማ ያገረሸውን ግጭትን ተከትሎም የሆስፒታል ሠራተኞች ላይ “ዛቻ እና እንግልት መድረሱን” እንዲሁም ታካሚዎች በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው መወሰዳቸውን የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ስሜ ቢጠቀስ ችግር ይደርስብኛል ያሉ የጎንደር ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያ፣ ባለፈው እሁድ በከተማዋ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሐኪሞች እና በታካሚዎች ላይ “ያልተገባ ድርጊት ፈጽመዋል” በማለት ከሰዋል።
በጎንደር ከተማ አዘዞ በሚገኘው አይራ ሆስፒታል “ሁለት ተረኛ ሐኪሞችን ደብቃችሁ የምታክሟቸውን ፋኖዎች አምጡ” በማለት ለሰዓታት እንዳንገላቷቸው እና ከዚያም በኋላ አንደኛውን የሕክምና ባለሙያ ለብቻው አግተው በመውሰድ ካቆዩት በኋላ ማታ ላይ እንደለቀቁት የሆስፒታል ምንጫችን ገልጸዋል።
ቸቸላ ሆስፒታል [ዋናው የጎንደር ሆስፒታል] “አራት ታካሚዎችን ከአልጋ አስነስተው ወስደዋቸዋል” የሚሉት የሕክምና ባለሙያው፣ “አብዛኞቹ በተባራሪ ጥይት ነው የመታነው ቢሉም ፋኖ ወይም የፋኖ ደጋፊ ናችሁ” በሚል በመኪና ጭነው ወስደዋቸዋል” ብለዋል።
እሁድ ዕለት በነበረው ግጭት አይራ ሆስፒታል ብቻ 11 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና መወሰዳቸውን ሐኪሙ ይናገራሉ።
ተጎጂዎቹ መኖሪያ ቤት ላይ በወደቀ ከባድ መሣሪያ እና በተባራሪ ጥይት ተመትተው የተጎዱ ሴቶች እና ሕጻናት በመሆናቸው፣ የመከላከያ ሠራዊት በፋኖ ታጣቂነት ጠርጥሮ ሊወስዳቸው አልቻለም ብለዋል።
ነገር ግን ሆስፒታል ውስጥ ሕሙማን እየተያዙ መሆናቸውን መረጃ ሲደርሳቸው፣ በርካቶች ከእነቁስላቸው በቤታቸው ሊቀሩ እንደሚችሉ ባለሙያው ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው እሁድ በነበረው ግጭት ወንድማቸው በተባራሪ ጥይት ተመትቶ በጎንደር ሆስፒታል ሲያሳክሙ የነበሩ የከተማዋ ነዋሪ፣ ወንድማቸውን ጨምሮ አምስት ታካሚዎች በመከላከያ ሠራዊት ከሆስፒታል ተይዘው መወሰዳቸውን ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
በሐኪሞቹ ላይ ዛቻዎች እና ማስፈራሪያች ቢፈጸሙም እንዲሁም ታማሚዎች ከሆስፒታል ቢወሰዱም የጎንደር ሆስፒታሎች አሁንም ሥራቸውን እንደቀጠሉ ሐኪሙ ተናግሯል።
ከሁለት ወር በፊት በአብዛኛው የአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል።
በአብዛኛው የጎጃም እና አንዳንድ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ደግሞ ከሳምንታት በፊት ከኢንተርኔት በተጨማሪ የስልክ አገልግሎትም ተቋርጧል።
በመሆኑም ከየአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች ቢቢሲ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አልቻለም።
በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች እየተካሄደ ባለው እና ጋብ እያለ በሚያገረሸው ግጭት ሳቢያ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ውስጥ መደበኛ እንቅስቃሴዎች እክል ገጥሟቸዋል።
በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በሚካሄዱ ግጭቶች እና የተኩስ ልውውጦች ምክንያት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ባለፉት ሳምንታት ሲዘገብ ቆይቷል።
ግጭቱ በጤና በተገልጋዮች፣ ተቋማቱ እና በባለሙያዎች ላይ ጫና እያሳደረ ሲሆን ከአንድ ወር በፊት የጎንደር ሆስፒታል የሕክምና አቅርቦት እጥረት እንዳጋጠመው ለቢቢሲ ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም አምነስቲ በፍኖተ ሰላም፣ በባህር ዳር እና በሸዋ ሮቢት ከተሞች የተፈጸሙ ግድያዎች መኖራቸውን መረጃዎች እንደ ደረሱት ጠቅሶ ተጨማሪ ምርመራ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ገልጾ ነበር።
በዚህ መግለጫው ላይ በአማራ ክልል ከተጣለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሪፖርት መደረጋቸውን ተከትሎ ገለልተኛ መርማሪዎች ወደ ስፍራዎቹ እንዲገቡ መንግሥት ፍቃድ እንዲሰጥ አምነስቲ መጠየቁ ይታወሳል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት የአቅርቦት መስመሮችን በማስተጓጎል ሰብዓዊ እርዳታን ማድረስ እና ግንኙነትን ለማስቀጠል ከባድ ያደርገዋል ብለው ነበር።
አክለውም ግጭቶች በሰዎች ጤና ላይ በፍጥነት አሉታዊ ተጽእኖ ከማሳደራቸው በተጨማሪ በጤና ሥርዓት ላይ ዘላቂ ጉዳት ስለሚያስከትሉ፣ ሰዎች የጤና ድጋፍ እንዳይቋረጥባቸው ባለሙያዎች ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ የክልሉ የጤና ሥርዓት ጥበቃ እንዲደረግለት ዶ/ር ቴድሮስ ባለፈው ነሐሴ መጠየቃቸው ይታወሳል።












