ጂቡቲ የሳተላይት እና የሮኬት ማስወንጨፊያ ማዕከል ልትገነባ ነው

የፎቶው ባለመብት, @IsmailOguelleh
የአፍሪካ ቀንድ ትንሿ አገር ጂቡቲ ለሳተላይቶች እና ለሮኬቶች ማስወንጨፊያ የሚሆን መሠረተ ልማት ልትገነባ መሆኗን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ጂቡቲ ይህንን የመሠረተ ልማት ግንባታ ለማከናወን ሆንግ ኮንግ ኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከተባለ ተቋም ጋር የአገሪቱ ባለሥልጣናት መፈራረማቸውን የአገሪቱ ዜና ወኪል ዘግቧል።
በዚህ ስምምነት መሠረት ከሳተላይት እና ሮኬት ማስወንጨፊያ ማዕከሉ ጋር በተያያዘ የሚያስፈልጉ የግንባታ አቅርቦቶችን ለማቀላጠፍ በሰሜናዊ የአገሪቱ ኦቦክ ክፍል ውስጥ ወደብ እና አውራ ጎዳና የሚገነባ ይሆናል።
የመሠረተ ልማቱ አጠቃላይ የግንባታ ሥራውም 1 ቢሊዮን ዶላር ያህል የሚያስወጣ ሲሆን በአምስት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።
ስምምነቱ ሲፈረም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ የተገኙ ሲሆን በትዊተር ገጻቸው ላይም አገራቸው ይህንን የሳተላይትና የሮኬት ማስወንጨፊያ ማዕከል ለመገንባት ከስምምነት መድረሷ እንዳኮራቸው እና አገሪቱን የሚያስወጣትን የገንዘብ መጠን ጽፈዋል።
“አገራችን ለዚህ ተስፋ ሰጪ ቴክኖሎጂ እና የኃይል ልማት ፕሮጀክት ሥራ እንዲጀምር ከስምምነት በመድረሷ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል ፕሬዝዳንት ጉሌህ።
የሳተላይት ማስወንጨፊያ ማዕከሉ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ ለ30 ዓመታት ያህል በሆንግ ኮንጉ ኩባንያ እና በጂቡቲ በጋራ የሚተዳደር ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ጂቡቲ ማዕከሉን ሙሉ ለሙሉ ትረከበዋለች ተብሏል።
በአፍሪካ የሳተላይት ሮኬት ማስወንጨፊያ በሰባት አገራት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን እነሱም በኬንያ፣ በግብፅ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በሊቢያ፣ በሞሪታኒያ፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ በአልጄሪያ ውስጥ ነው የሚገኙት።
ጂቡቲ ለመገንባት የተነሳችው የሳተላይት እና የሮኬት ማስወንጨፊያ ማዕከል ከአምስት ዓመታት በኋላ ሲጠናቀቅ በአህጉሪቱ ከሚገኙ ተመሳሳይ ማዕከላት አንዱ ይሆናል።












