ኢሊምፒክን የምታስተናግደው ፓሪስ የትኋን ወረርሽኝ ስጋት ፈጥሮባታል

ትኋን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፓሪስን ጨምሮ በተለያዩ የፈረንሳይ ክፍሎች የተከሰተው የትኋን ወረርሽኝ አገሪቱ በተጣይ የአውሮፓውያን ዓመት በምታስተናግደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ የጤና እና የደኅንነት ጥያቄን አስከትሏል።

ባለፉት ሳምንታት በአገሪቱ የትኋን ቁጥር መጨመሩን ብዙዎች ተመልክተዋል።

በማርሴይ ዋና ሆስፒታል ኢንቶሞሎጂስት የሆኑት ዢን ሚሼል በረንገ “በሞቃታማ ወራት የትኋኖች ቁጥር በጣም ሲጨምር እናያለን” ብለዋል።

“ዋናው ምክንያት ደግሞ ሰዎች በሐምሌ እና በነሐሴ ወራት ከሚያደርጉት ጉዞ በኋላ ትኋኖቹን በሻንጣቸው ይዘው ስለሚመለሱ ነው” ብለዋል።

አክለውም “በዚህ ዓመት የታየው የተባዮቹ ወረርሽኝ መጨመር ካለፈው የበለጠ ይሆናል” ሲሉ አመልክተዋል።

የፓሪስ ቤት አከራዮች ቤታቸው በትኋን እንዳይወረር ስጋት ውስጥ እየወደቁ ነው።

በቅርቡ ትኋኖች በአገሪቱ ሲኒማ ቤቶች ተስፋፍተዋል የተባለው ሪፖርት አለመረጋገጡ ታውቋል። ባቡር ላይም በትኋኖች ተነከስን የሚሉ ስሞታዎች በዝተዋል።

የፓሪስ ማዘጋጃ ቤት እና የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስተዳደር የትኋን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያስችል እርምጃ እንዲወስዱ ጥያቄ እየቀረበላቸው ነው።

የሚወሰደው እርምጃም ከወራት በኋላ ከሚካሄደው የ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ በፊት ጉዳዩን ምን ያህል በትኩረት እንደሚመለከቱት እና የፓሪስን ገጽታ እንዴት እንደሚጠብቁ የሚታይበት አጋጣሚም ነውም ተብሏል።

የተባዮቹን ወረርሽኝ በተመለከተ አስፈሪ ታሪኮች በበይነመረብ ላይ በፍጥነት እየተሰራጩ ጉዳዩን ወደ ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋነት እየቀየሩት ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተመልካች መቀነስ የሚያብሰለስላቸው የፈረንሳይ ሲኒማ ባለቤቶች በየወንበሮቻቸው ላይ የሚታዩ ትኋኖች የንዴታቸው ምክንያት ሆነዋል። የባቡር ተጠቃሚዎች ደግሞ ከመቀመጣቸው በፊት ወንበራቸውን ይፈትሻሉ አልያም ቆመው መሄድን ምርጫቸው ያደርጋሉ።

ሰዎች ችግሩን በፍጥነት ማወቃቸው ቶሎ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያግዝ የሚናገሩት በረንገ፤ የትኋን ወረርሽኙን በተመለከተ የሚነገሩት አብዛኞቹ ችግሮች መጋነናቸውንም አይደብቁም።

እውነታው ትኋኖች ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት እየተስፋፉ ነው። ይህ ችግር ግን የፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም አገራት ጉዳይ ሆኗል።

ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች የሚቀመጡ ሲሆን የኮንቴይነር ንግድ፣ ቱሪዝም እና ስደት ቀዳሚዎቹ መሆናቸው ይጠቀሳል። የአየር ንብረት ለውጥ ግን ምክንያት አይሆንም ተብሏል። ትኋኖች ከሰው ጋር የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ አይፈጥርባቸውም።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ትኋኖች በዲዲቲ ምክንያት ቁጥራቸው ቀንሷል።

አሁን ያሉት ትኋኖች ደግሞ በጊዜ ሂደት ዲዲቲን የበለጠ መቋቋም የሚችሉ ሆነዋል።

በረሮዎች ትኋኖችን ይመገባሉ። በዘመናዊ ኑሮ መስፋፋት ምክንያት በረሮዎች ቁጥራቸው ቀንሷል። ይህም ለትኋኖች ቁጥር መጨመር ሌላው ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።

ትኋኖች አደጋ ያስከትላሉ። ይህ አደጋ ግን ከአካላዊነቱ ይልቅ ሥነ ልቦናዊ ነው። ንክሻቸው ቢያምም ብዙ አይቆይም። በሽታም አያስተላልፉም ይላሉ ባለሙያዎች።

አንዳንዶች አንድ ጊዜ ትኋን አልጋቸው ላይ በማየታቸው ብቻ ለመተኛት ይቸገራሉ።

“በእኔ ዕይታ ትኋኖችን ለማስወገድ ሁሉም ላይ ከማነጣጠር ዋናዎቹ አሰራጮች ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነው” በማለት በረንገ ይመክራሉ።

በቁጥር ጥቂቶች ቢሆኑም ለተባዮቹ መስፋፋት አብዛኛውን ሚና የሚጫወቱት እነዚህ ሰዎች ናቸው ሲሉም ገልጸዋል። እነዚህም ብዙውን ጊዜም የተገለሉ፣ ድሆች፣ የአዕምሮ ህሙማን እና የማኅበራዊ አገልግሎት አቅርቦታቸው አነስተኛ የሆኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በርገን “እነዚህ ሰዎች ከቤት በወጡ ቁጥር ትኋኖችን ያሰራጫሉ። እርዳታ የሚያስፈልጋቸው እነሱ ናቸው” በማለት የተባዮቹን መስፋፋት ለመግታት የእነዚህን ሰዎች ሕይወት ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ።