ጣልያን ውስጥ ቱሪስቶችን ያሳፈረ አውቶብስ ከደልድይ ላይ ወድቆ ቢያንስ 21 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, VIGILI DEL FUOCO
በጣሊያን ቬንስ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኝ የተሽከርካሪዎች ማሳለጭ ድልድይ ላይ አንድ አውቶብስ ወድቆ ተከስክሶ በእሳት በመያያዙ ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ 21 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
አውቶብሱ የድልድዩን ማገጃ ብረት ጠርምሶት ካለፈ በኋላ ከቬነስ ከተማ ጋር በድልድይ የሚገናኛው ሜስትሬ አውራጃ ከሚገኝ የባቡር ሀዲድ አቅራቢያ ለይ ወድቋል።
ከሟቾቹ መካከል አምስት ዩክሬናውያን፣ አንድ ጀርመናዊ እና ጣሊያናዊው ሹፌር እንደሚገኙበት ተነግሯል።
የቬንስ ከተማ ከንቲባ ሊይጂ ብሩግናሮ ክስተቱን እጅግ አሰቃቂ ሲሉ ገልጸውታል።
ከንቲባው አደጋውን “የሚገልጹ ቃላት የሉም” ካሉ በኋላ የዓለም ፍጻሜ ትዕይንት ይመስላል በማለት በማኅበራዊ ተግስስር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
አደጋው የደረሰበት አውቶብስ ከቬንስ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ማርጋራ አውራጃ ቱሪስቶችን ለማመላስ በኪራይ መልክ ጥቅም ላይ እንደዋለ የተገመተ ሲሆን፣ ቱሪስቶቹን ወደ ማረፊያቸው ይዞ እየተመለሰ ሳለ ነው አደጋው ያጋጠመው።
በሚቴን ጋዝ የሚንቀሳቀሰው አውቶብሱ የኤሌክሪክ መሰመር ላይ ወድቆ በእሳት መያያዙን አንዳንድ ሪፖርቶች ጠቁመዋል።
የጣሊያን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማቲዎ ፒንታዶሲ የሟቾች ቁጥር ከተገለጸውም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ገልጸዋል።
የአደጋው ምክንያት እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን፣ የነፍስ አድን ሠራተኞች ክስተቱ ባጋጠመበት ቦታ ሥራቸውን እንደቀጠሉ ናቸው።
በአደጋው ቢያንስ 18 ሰዎች መጎዳታቸው የታወቀ ሲሆን፣ አምስቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
አደጋው በደረሰበት አካባቢ በሚገኘው ሆስፒታል የተጎጂ ቤተሰቦችን ለመደገፍ የሥነ ልቦና እና የሥነ አእምሮ ባለሙያዎች መዘጋጀታቸውም ተሰምቷል።
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በአደጋው የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ በአደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች ቤተሰቦች እና ወዳጆች ጋር መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንቷ ኡርሱላ ቫንደር ሊን “በዚህ ከባድ የሐዘን ጊዜ” ከጣልያን መሪዎች ጎን እንቆማለን ብለዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 በጣልያን ደቡባዊ ክፍል አንድ አውቶብስ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ 21 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ አውቶብሱ ገደል ውስጥ ከመግባቱ በፊት በርካታ ተሽከርካሪዎችን ገጭቷል።












