በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮችን እያደነ የገደለው ግለሰብ ህይወቱ አለፈ

በደቡብ አፍሪካ በርካታ ጥቁሮችን በማደን “የአፓርታይድ ገዳይ” የሚል ስያሜ ያተረፈው ግለሰብ ህይወቱ አለፈ።
በርካታ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን የገደለው ሉዊስ ቫን ሹር ህይወቱ ያለፈው በርካቶች አሁንም ፍትህ እየጠየቁ ባለበት ነው።
የ72 ዓመት ግለሰብ እግሩ ላይ ባጋጠመው ቁስለት ሆስፒታል ገብቶ የነበረ ሲሆን ይህም ተወሳስቦ ሐሙስ ዕለት ህይወቱ እንዳለፈ ሴት ልጁ ገልጻለች።
ባለፈው ሳምንት በጨቋኙ የነጭ አናሳ አፓርታይድ አገዛዝ መገባደጃ፣ በ1980ዎቹ ወቅት ግለሰቡ የፈጸማቸውን ግድያዎች በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎች ቢቢሲ በምርመራ ዘገባው አጋልጧል።
ግለሰቡ ከገደላቸው መካከል የአንደኛው እህት የአፓርታይዱ ገዳይ ህይወቱ ቢያልፍም ፖሊስ ክሱን በድጋሚ ምርመራ እንደሚከፍት ለቢቢሲ ተናግራለች።
የዘረኛው አፓርታይድ ስርዓት ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን በበላይነት የሚያስቀምጣቸውን ህጎች በሚያስተገብርበት ወቅት ቫን ሹር ምስራቅ ለንደን በተሰኘው የባህር ጠረፍ ከተማ በግል ጥበቃ ሰራተኛ ነበር።
ቫን ሹር በአውሮፓውያኑ 1986 እስከ 1989 ባለው ወቅት 39 ጥቁሮችን እያደነ ገድሏል። ከሟቾቹ ውስጥ የ12 ዓመት እድሜ ያለው ህጻን ነበረበት።
የአፓርታይድ ስርዓት ከመገርሰሱ በፊት በአውሮፓውያኑ 1991 በሰባት የግድያ ወንጀሎች ቢፈረድበትም ለ12 ዓመታት ብቻ በእስር ቤት ካሳለፈ በኋላ በነጻ ተለቋል።
ግለሰቡ የፈጸማቸው ሌሎቹ 32 ግድያዎች በወቅቱ በነበረው ስርዓት “ምክንያታዊ በተባሉ ግድያዎች” ተፈርጀዋል።
ቫን ሹር የገደላቸው ሁሉም ጥቁሮች “እጅ ከፍንጅ” የያዛቸው ወንጀለኞች መሆናቸውን ተናግሯል።
ግለሰቡ በአፓርታይድ ዘመን ህጎች ላየይ ተመርኩዞ ነጻ ነኝ ቢልም ቢቢሲ በሰራው የምርመራ ዘገባ እነዚህ ሆን ብለው የተፈጸሙ ግድያዎች መሆናቸውን አጋልጧል።
በዚህም ዘገባ ላይ ቫን ሹር ይፈጽማቸው የነበሩ ግድያዎችን “አስደሳች” እና “አደን” ሲል የገለጸበት ቃለ መጠይቅ እንዲሁም ፖሊስ ለምን ጣልቃ ይገባብኛል በሚል በ1980ዎቹ ያቀረባቸው ክሶችን አካቷል።
የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ በተጨማሪም በግለሰቡ ላይ በወቅቱ የተሰጡ በርካታ ምስክርነቶችን ገምግሟል።
ከነዚህም ውስጥ እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በጥይት የገደላቸው ጥቁሮች እንዳሉበት ይህ የታሪክ ማህደር ያስረዳል።
በወቅቱ የ14 ዓመት ልጅ የነበረ ታዳጊ ግለሰቡ በጠረጴዛ ላይ አስደግፎ እንደተኮሰበት እና እንደ እድል ሆኖ እንደተረፈም መናገሩ ሰፍሯል።
ግለሰቡ ህይወቱ ቢያልፍም የበርካታ ተጎጂ ቤተሰቦች የወንጀል ክስ እንዲጀመር እና ፍትህን እየጠየቁ ይገኛሉ።












