የየመን ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ

አህመድ ጋሌብ ናስር አል ራሃዊ እአአ ከነሐሴ 2024 ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አህመድ ጋሌብ ናስር አል ራሃዊ እአአ ከነሐሴ 2024 ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል

የሁቲ አማፂያን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው የሾሟቸው አህመድ ጋሌብ ናስር አል ራሃዊ ሐሙስ ዕለት እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት መገደላቸው ተገለፀ።

በኢራን የሚደገፈው ቡድን ሐሙስ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በየመን ዋና ከተማ ሰነዓ ላይ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት ሌሎች በርካታ ከፍተኛ ባለስልጣናትም መገደላቸውን አስታውቋል።

የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በሰነዓ አካባቢ ተሰብሰብው በነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃት በሰነዘሩበት ወቅት ራሃዊ እና ሌሎች የሁቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት "መወገዳቸውን" ገልጾ ነበር።

ሁቲዎች ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውንን መንግሥት ከሰነዓ ካባረሩ እና አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ አብዛኛውን የሰሜን ምዕራብ የመን ተቆጣጥረው ይገኛሉ።

ሁቲዎች ራሃዊ መገደላቸውን ባስታወቁበት መግለጫ ላይ ሌሎች የተገደሉ ባለሥልጣናትን ማንነት ሳይገልፁ በደፈናው በርካታ ሚኒስትሮች አብረው መገደላቸውን አስታውቀዋል።

የሳዑዲ አረቢያ የዜና ድረ ገጽ አል ሃዳት የሁቲዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣የፍትህ፣ የወጣቶች እና ስፖርት፣ ማኅበራዊ እና ሠራተኛ ሚኒስትሮች መገደላቸውን ዘግቧል።

የሁቲዎች ፕሬዝዳንት የማህዲ አል ማሻት ጽሕፈት ቤት እንደገለፀው በጥቃቱ ምክንያት ሌሎች በርካታ ሚኒስትሮች "መጠነኛ እና ከባድ የአካል ጉዳት" ደርሶባቸዋል።

የሁቲ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሀመድ አህመድ ሚፍታህ የራሃዊን ቦታ ተክተው ኃላፊነቱን እንደሚረከቡ አስታውቋል።

ራሃዊ እአአ ከነሐሴ 2024 ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣኑን ተረክበው ሲሰሩ የነበረ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ይታዩ የነበረው ቁልፍ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ የአገሪቱ ትልቅ ባለሥልጣን ወይንም ወታደራዊ ዘመቻዎችን እንደሚወስን ወታደራዊ መሪ ሳይሆን የእንቅስቃሴው ትዕምርት ተድርገው ነበር።

በሐሙሱ ጥቃት ከሞቱት መካከል የንቅናቄው ዋና መሪ፣ የቡድኑ የመከላከያ ሚኒስትር እና የጦር ኃይል አዛዥ አብዱል ማሊክ አል ሁቲ መሆን አለመሆናቸው አልተገለጸም።

የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ቅዳሜ ዕለት ረፋድ ላይ በሰጠው መግለጫ ስብስቡን በሚመለከት መረጃ በደረሰው በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ጥቃቱን መፈፀሙን ተናግሯል።

ጥቃቱ ያደረሰውን ሙሉ ውድመት እየገመገመ መሆኑን አክሎ ተናግሯል።

ሁቲዎች እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻዎችን በመጀመር ሐማስ ላይ ጥቃት ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ ለፍልስጤማውያን አጋርነታቸውን በመግለጽ፣በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ ሚሳዔሎችን በማስወንጨፍ ጉዳት አድርሰዋል።

እስራኤል በበኩሏ በሁቲ ቁጥጥር ስር ባሉ የየመን ክፍሎች ላይ የአየር ድብደባ በመፈጸም የአማፂውን ቡድን ጥቃቶች ለመግታት ሞክራለች።

ባለፈው ሳምንት ሁቲዎች ወደ እስራኤል ክላስተር ቦምብ የያዘ ሚሳዔል ማስወንጨፋቸውን ተከትሎ ሰነዓ ውስጥ የሁቲ ዒላማዎችን መምታቷን ተናግራለች።