ሁቲዎች በተከለከለ ክላስተር ቦምብ በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈፀሙ

እስራኤል ሁቲዎች የሚሳዔል ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በወታደራዊ ተቋማት ላይ ድብደባ ፈጽማለች

የፎቶው ባለመብት, MOHAMMED HUWAIS/AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል ሁቲዎች የሚሳዔል ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በወታደራዊ ተቋማት ላይ ድብደባ ፈጽማለች

ሁቲዎች አርብ ዕለት ወደ እስራኤል የተከለከሉ የክላስተር ቦምቦችን የያዘ ሚሳዔል ማስወንጨፋቸውን ተከትሎ በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ ውስጥ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ የአየር ድብደባ ፈፀመች።

የእስራኤል ጥቃት ዒላማ ያደረገው የፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት፣ የነዳጅ ዴፖ እና የኃይል ማከፋፈያዎች የሚገኝበትን ወታደራዊ ካምፕ ነው።

የሁቲ ባለስልጣናት ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እና 86 መቁሰላቸውን አሳውቀዋል።

የእስራኤል ጦር እንዳለው በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በእስራኤል ላይ የተከለከሉ ቦምቦችን ሲጠቀሙ ይህ የመጀመርያቸው መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እና ኤፒ ዘግበዋል።

የእስራኤል መከላከያ ከየመን የተወነጨፉትን ሚሳዔሎች ለምን ማክሸፍ እንዳልቻለ ምርመራ እያደረገ ሲሆን ሚሳዔሉ የያዛቸው ቦምቦች ከ100 በላይ አገራት የተከለከሉ ናቸው ብሏል።

እስራኤል በሰንዓ ላይ የወሰደችውን የአጸፋ እርምጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና በመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትስ በበላይነት የመሩት ሲሆን የእስራኤል መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴል አቪቭ በሚገኘው የዕዝ ማዕከል ሆነው የሚያሳይ ፎቶግራፍ አሰራጭቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ "የሚያጠቃንን ሁሉ መለሰን እናጠቃለን። እኛን ለማጥቃት ያቀደ ሁሉ እንጠቃዋለን። መላው ቀጠና የእስራኤልን መንግሥት አቅም እና ቁርጠኝነት እየተማረ ነው ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።

ከአርቡ ጥቃት በኋላ ሁቲዎች ቦምቦች በአየር ላይ ሲፈነዱ የሚያሳይ ቪዲዮ ለቅቀዋል።

የእስራኤል መከላከያ እሁድ ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለፀው ከሆነ አንዱ ቦምብ በእስራኤል ማዕከላዊ ጂናቶን ከተማ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ወድቆ ቀላል ጉዳት አድርሷል።

የመከላከያ የምርመራ ማዕከል ቦምቦቹን የተሸከመው ሚሳዔል ከመፈንዳቱ በፊት ለምን ማክሸፍ አልተቻለም የሚለውን ምርመራ እያደረገ መሆኑን የእስራኤል ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ክላስተር ቦምቦች ሮኬቶች፣ ሚሳዔሎች ወይም ሌሎች ተተኳሾች ላይ በመሆን በአየር ላይ ተበትነው የሚፈነዱ ናቸው።

ቦምቦቹ ዒላማ ባደረጉት ስፍራ ላይ እንዲፈነዱ የታቀዱ ቢሆንም ከፍተኛ መጠን ያላቸው ግን መጀመሪያ ላይ አለመፈንዳታቸው ታውቋል።

ይህ ሊሆን የሚችለው በተለይ እርጥብ ወይም ለስላሳ መሬት ላይ በማረፋቸው ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

ከዚያም በኋላ ሲነሱ ወይም ሲረገጡ ሊፈነዱ እና ሰዎችን ሊገድሉ ወይም ሊጎዱ ይችላሉ።

ሁቲዎች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘውን መንግሥት ከሰንዓ ካባረሩ እና አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ከቀሰቀሱ በኋላ አብዛኛውን የሰሜን ምዕራብ የመን ተቆጣጥረዋል።

መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በጋዛ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሁቲዎች ለፍልስጤማውያን አጋርነታቸውን በመግለጽ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፤ ወደ እስራኤልም ሚሳዔሎችን አስነወንጭፈዋል።

እስራኤል አማፅያኑ በኢራን ይደገፋሉ ስትል የምትወነጅላቸው ሲሆን በሰኔ ወር ከእስራኤል ጋር በነበራት የ12 ቀን ጦርነት ወቅት ክላስተር ቦምቦችን ተጠቅማለች ብላለች።

ኢራን ለዚህ ውንጀላ በወቅቱ ምላሽ አልሰጠችም።