በናይጄሪያ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ700 በላይ ሰዎች ሳይሞቱ አይቀርም ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Mikail Musa
ሐሙስ ዕለት በናይጄሪያዋ ሞካዋ ከተማ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተፈጠረ ከባድ ጎርፍ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200 በላይ መሆኑ ሲገለጽ ይህ ቁጥር እስከ 700 እንደሚደርስ ተነግሯል።
በአገሪቱ ማዕከላዊ ናጀር ግዛት ውስጥ በደረሰው አደጋ እስካሁን 500 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን ተከትሎ የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሕይወት የሚገኝ ሰው ከዚህ በኋላ አይኖርም በሚል እምነት የነፍስ አድን ጥረቱ ተቋርጧል።
ባለፉት 60 ዓመታት አገሪቱ ካጋጠማት የጎርፍ አደጋ ሁሉ የከፋው ነው የተባለው ይህ ጎርፍ ቲፊን ማዛ እንዲሁም አንጉዋን ሃኡሳዋ የተባሉ ከተሞች ላይ ከባድ ውድመት አድርሷል።
በአካባቢው ተላላፊ በሽታ እንዳይዛመት ለማድረግ በጎርፉ የተቀበሩ ግለሰቦችን ቆፍሮ በማውጣት ተገቢው የቀብር ሥነ ሥርዓት ማከናወን በቅርቡ እንደሚጀመር የሞካዋ አካባቢ አስተዳዳሪ ሙሐመዱ አሊዩ ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ዓይናቸው እያየ ቤታቸው እና ቤተሰቦቻቸው በጎርፍ ሲወሰዱ መመልከታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለቤቱ እና ጨቅላ ልጁ በጎርፍ የተወሰዱበት አዳሙ ዩሱፍ የተባለው ግለሰብ "ቤተሰቤን ጎርፍ ሲወስድ ምንም ማድረግ ሳልችል ቆሜ ተመልክቻለሁ። እኔም መዋኘት በመቻሌ ነው የተረፍኩት" ብሏል ለቢቢሲ።
ሳሊኡ ሱሌይማን የተባለ ሌላ ግለሰብ ጎርፉ ቤት አልባ እንዳደረገው ገልጾ፤ ከንግድ ያገኘው ገንዘብ እና ንብረት አብሮ መወሰዱን ተናግሯል።
"በጎርፉ የተነሳ 1500 ዶላር የሚያወጣ ንብረት ወድሞብኛል። ቀደም ብሎ ከሸጥኩት የግብርና ምርት ያገኘሁት ነበር። ከተቀመጠበት ቀጣይ ክፍል ሄጄ ማውጣት ፈልጌ ነበር፤ ነገር ግን የውሃው ግፊት አስፈራኝ።"
እሁድ ዕለት የአገሪቱ ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኤጀንሲ በጎርፍ አደጋው ለተጠቁ ሰዎች የእርዳታ አቅርቦት ማዳረስ እንደሚጀምር ተናግሯል።
ኤጀንሲው በፌስቡክ ገጾ ላይ በለጠፈው መረጃ መሠረት በጎርፉ መንገዶች እና ድልድዮች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ይህም በአካባቢው የኢኮኖሚ እና የትራንስፖረት እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
የናይጄሪያ ቀይ መስቀል አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተው ጎርፍ "ከባድ የሕይወት መጥፋት እና ሰፊ ስጋት ፈጥሯል" ብሏል።
በናይጄሪያ ከሚያዝያ እስከ ጥቅምት ወር ባለው የዝናብ ወቅት የጎርፍ አደጋ በተደጋጋሚ ያጋጥማል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2024 የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰው የጎርፍ አደጋ በርካቶች ሲሞቱ ሌሎች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል።
በ2022 እንዲሁ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ600 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ 1.3 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ደግሞ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።















