የናይጄሪዋ ቦርኖ ግዛት አስተዳዳሪ ቦኮ ሃራም ተመልሶ ሊመጣ እንደሚችል አስጠነቀቁ

የተቀመጡ አዛውንት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቦኮ ሃራም በፈጸማቸው ጥቃቶች ሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሲሰደዱ፣ ከ 40 ሺህ በላይ ደግሞ ሞተዋል

የናይጄርያዋ ቦርኖ ግዛት አስተዳዳሪ የቦኮ ሃራም ተዋጊዎች የግዛቲቱ ሰሜን ምሥራቅ አካባቢ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት መሰንዘር እና የተወሰኑ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ አማጽያኑ ተመልሰው ሊመጡ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገለፁ።

የግዛቱ አስተዳዳሪ ባባጋና ዙሉም፤ በአካባቢው አማፂያኑን ለመዋጋት ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግ ለፌደራል መንግሥቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የናይጄርያ መንግሥት የአስተዳዳሪውን ፍርሃት ቀለል አድርጎ የተመለከተ ሲሆን፣ ባለፉት 18 ወራት የአገሪቱ ደህንነት ተሻሽሏል ብሏል።

ቦርኖ ግዛት ለ15 ዓመት ያህል ቦኮ ሃራም ሲንቀሳቀስበት የነበረ አካበቢ ሲሆን፣ በአካባቢው በነበረ ግጭት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሲሰደዱ ከ 40 ሺህ በላይ ደግሞ ሞተዋል።

እአአ በ2015 ቦኮ ሃራም የቦርኖ ግዛት በርካታ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የነበረ ሲሆን፣ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ተከፍቶ የያዛቸውን አካባቢዎችን ለቅቆ እንዲወጣ ተደርጓል።

ታጣቂ ቡድኑ በሚያዝያ 2014 በቦርኖ ግዛት ከምትገኘው የቺቦክ ከተማ ከ270 የሚበልጡ ተማሪዎችን ማገቱን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ታዋቂነትን አግኝቷል።

በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው አንጻራዊ መረጋጋትን ተከትሎ አማፂዎቹ ወታደራዊ ካምፖችን፣ ፖሊስ ጣቢያዎችን እና የገጠር ማኅበረሰቦችን ዒላማ አድርገው ጥቃት ማድረስ ቀጥለዋል።

በጥር ወር ከቦኮ ሃራም የተገነጠለ አንጃ የአገሪቱ ምዕራባዊ ግዛት በሆነችው ኢስዋፕ ባካሄደው የደፈጣ ጥቃት፤ በትንሹ 20 የናይጄሪያ ወታደሮች መግደሉ ሲገለጽ፣ በተመሳሳይ ጊዜ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት 40 ገበሬዎች ሞተዋል።

የቦርኖ ግዛት አስተዳዳሪ ዙሉም፤ ቡድኑ በየቀኑ ማለት በሚያስደፍር መልኩ በበርካታ ማኅበረሰቦች ላይ ጥቃት እና እገታ መፈጸሙን "ተስፋ አስቆራጭ" ሲሉ ገልጸውታል።

አስተዳዳሪው ከብሔራዊ ደህንነት ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ የቦርኖ ግዛት በጂሃዲስቶች ላይ "ያለውን የበላይነት" እያጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የፀጥታ ተንታኞች እንደሚሉት በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ የአገሪቱ ወታደሮች ሽፍቶችን እና የሚፈጸሙ እገታዎችን ለመከላከል በመሰማራታቸው በአገሪቱ ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች በሚገኙት በቦርኖ እና በሌሎች ስፍራዎች ከቦኮሃራም ጋር በመዋጋት ላይ የሚገኙት ወታደሮች ቁጥር ቀንሷል።

ጎረቤት ኒጀር የጂሃዲስት ቡድኑን ለመመከት ከተቋቋመው የቀጠናው ጥምር ጦር ወታደሮቿን ካስወጣች በኋላ ከታጣቂዎቹ ጋር የሚደረገው ውጊያ የበለጠ አዳጋች ሆኗል።

ሃሚሱ ሳኒ የተባሉ ሌላ ተንታኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቦኮ ሃራምን ማሸነፍ ቀላል ባይሆንም የማይቻል ግን አይደለም።

"የእኛ ወታደሮች የቱንም ያህል ቢያዳክማቸው ሁል ጊዜ እንደገና ተሰባስበው ስጋት ሆነው ይቀጥላሉ" ብለዋል።

"መፍትሄው አማፂያኑን ሙሉ በሙሉ መደምሰስ ነው። ይህም ለሠራዊቱ ተገቢውን ድጋፍ በመስጠት የሚቻል ነው።"