በምያንማር በታጣቂዎች ሥር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ወሲባዊ ትንኮሳ እየደረሰባቸው እንደሆነ ተናገሩ

በምያንማር የሳይበር ወንጀል ካምፖች በግዳጅ ሲሰሩ የቆዩ እና አሁን ላይ ከካምፖቹ ወጥተው በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ወሲባዊ ትንኮሳ እየደረሰባቸው እንደሆነ ለቢቢሲ ተናገሩ።
"ታይላንድ ሥራ አለ" በሚል ተታለው ከአገራቸው እንደወጡ የሚገልጹት እነዚህ ሴቶች፣ወደ ምያንማር ተወስደው በሳይበር የወንጀል ካምፖች ውስጥ በግዳጅ ሲሰሩ መቆየታቸውን ይገልጻሉ።
ሴቶቹ 'ማይዋዲይ ከሚገኙ የወንጀል ካምፖች የወጡ ናቸው።
ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በታጣቂዎች ሥር የሚገኙ ሁለት ሴቶች፣ ከወንጀል ካምፖቹ በምያንማር እና በታይላንድ መንግሥት ወታደሮች አማካይነት ከወጡ በኋላም ደኅንነት እንደማይሰማቸው ተናግረዋል።
ካረን በተባለው የምያንማር ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀሱት "ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ" (DKBA) እና "ቦርደር ጋርድ ፎርስ" (BGF) የተባሉት ታጣቂ ቡድኖች በካምፖቹ ውስጥ በግዳጅ የተያዙ ሰዎችን እንዳስወጡ የተገለጸው ከሁለት ወር ገደማ በፊት ነበር።
የምያንማር ወታደራዊ መንግሥት አጋር የሆነው "ቦርደር ጋርድ ፎርስ" የተባለው ታጣቂ ቡድንም ከ29 አገራት የተውጣጡ ከሰባት ሺህ በላይ የግዳጅ ሠራተኞችን ከካምፖቹ ማስወጣቱን በወቅቱ ገልጾ ነበር።
ከእነዚህ መካከል ከ800 በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን በእነዚህ ሁለት ታጣቂዎች እጅ ላይ እንደሚገኙ በታይላንድ ያሉ የእርዳታ ድርጅት ምንጮች እና በታጣቂዎቹ ሥር ያሉ ኢትዮጵያውያን ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
በ"ቦርደር ጋርድ ፎርስ" ሥር 430፣"ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ" ሥር ደግሞ 430 ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙም ምንጮቹ ጠቅሰዋል።
ሆኖም የወንጀል ሰለባዎቹ በበርካታ የተለያዩ ካምፖች ስለሚገኙ ምን ያህል ሴቶች ወደ ታይላንድ ለመግባት እየተጠባበቁ እንዳሉ የሚያሳይ የተደራጀ መረጃ የለም።
በቦርደር ጋርድ ፎርስ (BGF) ታጣቂዎች ሥር እንደሚገኙ የገለጹ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሴቶች፣ እነርሱ በሚገኙበት ሕንፃ ከሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን መካከል ሰባቱ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ቀን መጠባበቅ ከጀመሩም ከአንድ ወር በላይ እንደሆናቸው ተናግረዋል።
በሕንፃው ውስጥ የካሜሩን፣የቻድ፣ የኮንጎ፣ የኔፓል፣ የፓኪስታን እና የኬንያ ዜጎች እንደሚገኙ፤ ነገር ግን ኬንያውያኑ በቅርቡ መውጣታቸውንም ተጎጂዎቹ ይናገራሉ።
በሳይበር ወንጀል ካምፖች ውስጥ ሳሉ የተለያዩ አካላዊ ቅጣቶችን ሲያስተናግዱ እንደነበር የሚያስታውሱት የወንጀል ሰለባዎቹ፣" ከዚህ የሥነ ልቦና ቁስል ሳንድን ከወንጀል ካምፑ ከወጣን በኋላም ለወሲባዊ ትንኮሳ እየተዳረግን ነው" ይላሉ።
በዚህም ምክንያት ራሳቸውን ለመጠበቅ ሲሉ አንድ ላይ ተሰባስበው ማደር መጀመራቸውን ይገልጻሉ።
"ኢትዮጵያውያኑ በሕንፃው አንድ ወለል ላይ ነው ያለነው።ወደ ታች መውረድም ሆነ ወደ ላይ መውጣት አንችልም።ኮሪደሮቹ በወታደሮቹ ይጠበቃል። ከእነርሱ በተጨማሪም ሌሎች ታጣቂዎች አሉ" የሚሉት ሴቶቹ፣ ታጣቂዎቹ ማታ ማታ ሰክረው እንደሚመጡ እና በራቸውን እንደሚያንኳኩ፣ አንዳንዴም ወደ ክፍላቸው ገብተው እንደማይወጡ ያስረዳሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራት አንዲት ተጎጂ "ወደ ክፍላችን በሚገቡበት ሰዓት ወሲባዊ ወሬዎችን ነው የሚያወሩን፤ መኝታችን ላይ [ችቡድ] ላይ ተቀምጠው ይቆያሉ፤ ልብሳችንን ይነካካሉ፤ ከእነ ትጥቃቸው ስለሆነ የሚገቡት ያኔ በፍርሃት እንርዳለን" ስትል ስላሉበት አስጨናቂ ሁኔታ ገልጻለች።
እስካሁን ወሲባዊ ጥቃት የደረሰበት ባይኖርም በስጋት ምክንያት ከሌሊት ይልቅ ቀን ቀን ለመተኛት መገደዳቸውንም ትናገራለች።
" ቀን ቀን ኢትዮጵያውያን ወንዶች ስለሚንቀሳቀሱ እነሱ ይጠብቁናል ብለን ነው ቀን የምንተኛው።በሥነ ልቦና በጣም ተጎድተናል" ስትል ወደ አገራቸው በአፋጣኝ እንዲመለሱ ትማፀናለች።
በደቡብ ምሥራቅ እስያዋ ምያንማር ብዛት ያላቸው የሳይበር (የበይነ መረብ) ማጭበርበር የሚከናወንባቸው ካምፖች የሚገኙባት አገር ነች።
በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ቢያንስ 154 ግቢዎች ውስጥ የሚፈጸሙት የማጭበርበር ወንጀሎች በአብዛኛው የሚከናወኑት "የሥራ ዕድል ታገኛላችሁ" በሚል ተታልለው በግዳጅ ለዚህ ድርጊት በተዳረጉ የተለያዩ አገራት ዜጎች ነው።
በማኔጅመንት በዲግሪ እንደተመረቀች እና ለሽያጭ ሥራ በሚል ተታልላ ወደ ታይላንድ እንደሄደች የገለጸችው ወጣት፣ ከካምፑ ከወጡ ከአርባ ቀን በላይ እንደሆናቸው ጠቅሳ፣ ከሚመገቡት ምግብ እና መሠረታዊ ፍላጎት እጦት ባሻገር በሴትነታቸው የከፋ ተፅዕኖ እየደረሰባቸው እንደሚገኙ ትናገራለች።
ወደ አገራቸው ለመመለስ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ በተደጋጋሚ ቢገለጽላቸውም አፋጣኝ ምላሽ እንዳላገኙም ትገልጻለች።
ከወራት በፊት በወንጀል ካምፖቹ በግዳጅ ሲሰሩ የነበሩ 138 ኢትዮጵያውን ተለቅቀው ወደ ታይላንድ መግባታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሰው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከማይናማር እገታ ወጥተው ታይላንድ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መካከል 130ዎቹ በሁለት ዙር ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
ሆኖም አሁንም በተለያዩ ታጣቂዎች እጅ ሥር የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምያንማር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን መንግሥት እንዲታደጋቸው እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ኬንያንና ሕንድን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ዜጎቻቸውን እንዳስወጡ የሚገልጹት ተጎጂዎቹ፣ ለእነርሱ ግን ከተስፋ ውጭ የተሰጣቸው አፋጣኝ ምላሽ እንደሌለ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉት በሕንድ እንዲሁም በጃፓን ከሚገኙት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ኢትዮጵያውያኑ ስላሉበት ሁኔታ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም።












