ቻይና በአሜሪካ ምርቶች ላይ የ84 በመቶ ታሪፍ በመጨመር ለዶናልድ ትራምፕ እርምጃ ምላሽ ሰጠች


የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አገሪቱ የትራምፕን ታሪፍ በመቃወም "እስከመጨረሻው ለመዋጋት" መገደዷን ገልጿል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ፣ መጋቢት 24/2017 ዓ.ም. ይፋ ያደረጉት የታሪፍ ጭማሪን ተከትሎ ቻይና ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ84 በመቶ ታሪፍ መጣሏን ይፋ አድርጋለች።

ቤጂንግ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ትራምፕ ባስፈራሩት መሠረት በቻይና ላይ ታሪፉን እጥፍ በማድረግ ወደ 104 በመቶ ከፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

ይህ የንግድ ጦርነት እየተጋጋለ ሄዶ የኢኮኖሚ ድቀት ያስከትላል የሚል ስጋት እየፈጠረ መሆኑ ተገልጿል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አገሪቱ የትራምፕን ታሪፍ በመቃወም "እስከመጨረሻው ለመዋጋት" መገደዷን እና ኋይት ሃውስ "የጉልበተኞችን አካሄድ" መርጧል ሲልም ከሷል።

ቻይና ቀደም ሲል 34 በመቶ የነበረውን የታሪፍ መጠን ከፍ በማድረግ 84 በመቶ አድርሰዋለች።

ከነገ ጀምሮም 12 የአሜሪካ ኩባንያዎችን ወደ ውጭ ሲልኩ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ተቋማት ዝርዝር ውስጥ ይካተታሉ ተብሏል።

በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች ምርታቸውን ከአገር ለማስውጣት የኤክስፖርት ፈቃድ ሊጠይቁ የሚችሉ ተብለው የተለዩ ናቸው።

የሰው ሠራሽ አስተውህሎት ኩባንያዎችን ጨምሮ ስድስት የአሜሪካ ኩባንያዎች ወደማይታመኑ ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል።

በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሚገቡ ኩባንያዎች ቻይና ውስጥ እንደልብ ለመሥራት የማይችሉ ከመሆኑም በላይ እገዳ እና ቅጣትም ሊተላልፍባቸው ይችላል።

ቻይና ካልቪን ክሌይን እና ቶሚ የመሳሰሉ ልብሶችን የሚያመርተው ፒቪኤችን ቀደም ብላ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ማካተቷ ተዘግቧል።

ቻእና አስቀድማ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የንግድ ሕጎችን እየጣሰች ነው በማለት ቅሬታውን ለዓለም ንግድ ድርጅት አቅርባለች።

ቻይና ውሳኔዋን ይፋ ካደረገች በኋላ ትራምፕ በሰጡት የመጀመሪያ አስተያየታቸው አሁን ወደ አሜሪካ ፋብሪካዎቻቸውን ለማዛወር "ታላቅ ጊዜ" እንደሆነ ለንግድ ድርጅቶች ተናግረዋል።

የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት በበኩላቸው ከቻይና ጋር ጠንካራ ትብብር ማድረግ አስከፊ መዘዝ እንደሚያስከትል ለአሜሪካ አጋሮች ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

የእስያ የአክሲዮን ገበያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የስፔን ኢኮኖሚ ሚኒስትር ሰኞ ዕለት ቤጂንግ ለአገራቸው እና ለሌሎች የአውሮፓ አገራት ወሳኝ ስትራቴጂካዊ አጋር ልትሆን እንደምትችል መጠቆማቸው ይታወሳል።

በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ቢሴንት ግን ከቻይና ጋር የበለጠ መወዳጀት ማለት "የራስን ጉሮሮ እንደመቁረጥ" ነው።

ቀደም ሲል ከፎክስ ቢዝነስ ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ደግሞ ቻይና በአሜሪካ ምርቶች ላይ 84 በመቶ ታሪፍ ለመጣል መወሰኗን "አሳዛኝ" ውሳኔ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ቻይና ከምትገዛው በላይ ለአሜሪካ የምትሸጠው እንደሚበልጥ በመግለጽ "በዚህ በኩል የበላይነት የላትም። ስለዚህ ታሪፋቸውን ከፍ ማድረግ ይችላሉ። ግን ምን ያገኛሉ?" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ኅብረትም ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ታሪፍ ለመጫን ድምጽ ሰጥቷል።

የኅብረቱ ኮሚሽን እንዳስታወቀው ከሆነ አባል አገራቱ ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ታሪፍ ለመጨመር የቀረበውን ሃሳብ በድምጽ ብልጫ አጽድቀውታል።

አዲሱ ታሪፍ ከሳምንት በኋላ ተግባራዊ እንደሚደረግም ታውቋል።

"የአውሮፓ ኅብረት የአሜሪካን ታሪፍ ፍትሃዊ ያልሆነ እና ጎጂ እንደሆነ አድርጎ ይቆጥረዋል። ይህም በሁለቱም ወገኖች እና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያስከትላል" ሲል ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል።

"የአውሮፓ ኅብረት ከአሜሪካ ጋር የተመጣጠነ እና ሁለንተናዊ ጥቅም ያለው ድርድር ማድረግን ቀዳሚ ምርጫው ማድረጉን ገልጿል" ሲልም አክሏል።

ወደ 60 የሚጠጉ አገራት ላይ የተጣለው ቀረጥ ዛሬ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት፣ ትራምፕ በሰጡት አስተያት ብዙ አገራት ስምምነት ለማድረግ "እየተጣጣሩ ነው" ብለዋል።

"እውነቴን ነው የምላችሁ እነዚህ አገራት እየደወሉ ጭራቸው በመቁላት ላይ ናቸው" ብለዋል።

የቻይናን ውሳኔ ተከትሎ የአውሮፓ የአክሲዮን ገበያ ይበልጥ ማሽቆልቆሉ ታውቋል።

የታሪፍ ጦርነቱ ከየት ተነስቶ እዘህ ደረሰ?

ከቀናት በፊት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ 100 ገደማ አገራት ወደ አሜሪካ በሚልኳቸው ሸቀጦች ላይ ታሪፍ ጥለዋል።

ትራምፕ ረቡዕ፣ መጋቢት 24/2017 ዓ.ም. ይፋ ያደረጉት ታሪፍ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ የዓለም አቀፍ ንግድ ለውጥ ነው ተብሎለታል።

ትራምፕ በአገራቱ ላይ የጣሉት የመነሻ ታሪፍ ምጣኔ 10 በመቶ ነው።

ይህ የታሪፍ መጠን ለምርጫ ቅስቀሳ ባደረጉ ጊዜ የእቅዳቸው አካል አድረገው ከጠቀሱት ቁጥር ጋር ተመሳሳይ ነው።

የአሜሪካ መንግሥት ወደ አገሪቱ ምርቶችን የሚልኩ 60 አገሮች "የለየላቸው አጥፊዎች" የሚል ምድብ ውስጥ አካትቷል።

በዚህ ምድብ ውስጥ የተካተቱት የአውሮፓ ኅብረት፣ ቻይና ለተከተሉት ፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ ፖሊሲ ምክንያት ከፍተኛ የታሪፍ ምጣኔ እንደሚጣልባቸው ትራምፕ ተናግረዋል።

እንደ ኋይት ሃውስ ገለጻ 10 በመቶ የታሪፍ ምጣኔ በተጣለባቸው አገራት ላይ እርምጃው ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ካለፈው ቅዳሜ፣ መጋቢት 27/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ነው።

በኢትዮጵያ ላይ የተጣለው የታሪፍ ምጣኔ 10 በመቶ ሲሆን በዚህ መሰረት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ወደ አሜሪካ የሚላኩ ምርቶች ተጨማሪ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።

ትራምፕ ኢትዮጵያ ላይ የጣሉት 10 በመቶ ታሪፍ፤ በሁሉም ሀገራት ላይ ያስቀመጡት የታሪፍ መነሻ ምጣኔ (baseline tariff) ነው።

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2024፤ 465.8 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት ወደ አሜሪካ መላኳን የአገሪቱ መንግሥት መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ ዋነኛዎቹ ቡና እና የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያን ከሚያዋስኑ ስድስት ሀገራት ውስጥ አምስቱ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ቡጢ አርፎባቸዋል። በአሜሪካ ታሪፍ ያልተጣለባት ብቸኛዋ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገር ሶማሊያ ነች።

ጎረቤት አገራት ኬንያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የተጠላባቸው ታሪፍ ምጣኔ ከኢትዮጵያ በጋር ተመሳሳይ 10 በመቶ ነው። ግብጽም በተመሳሳይ የ10 በመቶ ቀረጥ ተጥሎባታል።

የነጩ ቤተ መንግሥት ባለስልጣናት "የለየላቸው አጥፊዎች" ተብለው በተለዩ 60 ገደማ አገራት ላይ ከሚያዝያ 1 ጀምሮ የአጸፋ ታሪፍ እንደተጣለባቸው ገልጸዋል።

እነዚህ አገራት ከአሜሪካ የሚመጡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ የጣሉ፣ አሜሪካ ላይ ከታሪፍ ውጪ የሆኑ የንግድ መሰናክሎችን ያስቀመጡ ወይም የአሜሪካን ኢኮኖሚያዊ ግብ ለማሳነስ እንደተንቀሳቀሱ መንግሥት ያመነባቸው እንደሆኑ ተነግሯል።

ይህ አይነቱ ታሪፍ ከተጣለባቸው የአሜሪካ የንግድ አጋሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡

አውሮፓ ኅብረት (20 በመቶ)፣ ቻይና (54 በመቶ)፣ ቪየትናም (46 በመቶ)፣ ታይላንድ (36 በመቶ)፣ ጃፓን (24 በመቶ)፣ ካምቦዲያ (49 በመቶ)፣ ደቡብ አፍሪካ (30 በመቶ) እና ታይዋን (32 በመቶ) ናቸው።