የትራምፕን ታሪፍ ተከትሎ ከ50 በላይ አገራት ለመነጋገር መጠየቃቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ውሳኔ ተከትሎ ከ50 በላይ አገራት ወደ አሜሪካ ስለሚልኳቸው ምርቶች ለመነጋገር ዋይት ሃውስን መጠየቃቸውን ባለስልጣናት ተናገሩ።
የፕሬዚዳንቱን ታሪፍ ተከትሎ የአሜሪካ አክሲዮን ገበያ ከፍተኛ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን የዓለም ገበያ ላይም ለውጥ ታይቷል።
ይኹን አንጂ የትራምፕ ባለስልጣናት ኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን ዘላቂ ጫና አሳንሰው አቅርበዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና አማካሪዎቻቸው በገቢ ምርቶች ላይ የተጣለው ታሪፍ በዓለም ገበያ ላይ የፈጠረውን አለመረጋጋት "አንዳንድ ነገሮችን ለማስተካከል መድሃኒት መውሰድ ያስፈልጋል" ሲሉ ተከላክለዋል።
እሁድ እለት ወደ ኤር ፎርስ 1 እያመሩ ባሉበት ወቅት ለጋዜጠኞች ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ፣
"ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለመበልጸግ" ሥራዎች እና ኢንቨስትመንት ዳግም ወደ አሜሪካ እንደሚመለሱ ተናግረዋል።
የትራምፕ ከፍተኛ ባለስልጣናት ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው ታሪፍ በታቀደው መሰረት ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸው፤ የኢኮኖሚ ሪሴሽን ሊኖር ይችላል የሚለውን አጣጥለዋል።
ትራምፕ ይህንን አስተያየት ከሰጡ ሰዓታት በኋላ በእስያ የአክሲዮን ገበያዎች ሰኞ ማለዳ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሱ ሲሆን፤ የጃፓኑ ኒኬኪ በ6.3 በመቶ ሲወርድ የሆንግ ኮንግ ሃንግ ሴንግ ደግሞ 9.8 በመቶ ያህል ድርሻውን አጥቷል።
አርብ ዕለት ሦስቱ የስቶክ ማርኬት አመላካቾች በአሜሪካ ከ5 በመቶ በላይ ማሽቆልቆላቸው የታየ ሲሆን ኤስ ኤንድ ፒ 500 ደግሞ ከ2020 ጀምሮ በአሜሪካ የአክሲዮን ገበያ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በ6 በመቶ ቀንሷል።
የሳዑዲ አረቢያ የአክሲዮን ገበያ እንዲሁ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወዲህ ከፍተኛው ነው በተባለ መልኩ የ7 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
በአሜሪካ ግዙፉ የሆነው ጄፒ ሞርጋን የትራምፕን የታሪፍ እርምጃ ተከትሎ የአሜሪካ እና የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ 60 በመቶ የመውደቅ እድል እንዳለው ተንብዮ ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ዕለት ወደ ኤርፎርስ ዋን እየተሳፈሩ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የአውሮፓ እና እስያ አገራት "ከስምምነት ላይ ለመድረስ እየተሟሟቱ ነው" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከአንድ ጋዜጠኛ ሸማቾች የዋጋ ጭማሪ እና የገበያ ግሽበት መጨመር ስጋት አላቸው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ "ጥያቄህ የሚረባ አይደለም" ሲሉ ምላሽ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ "ምንም ዓይነት ነገር መጥፎ ነገር እንዲፈጠር አልፈልግም። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን ለማስተካከል መድሃኒት መውሰድ ያስፈልጋል" ብለዋል።
ከእሁድ ቀደም ብሎ በነበሩ ተከታታይ የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቆች የትራምፕ ከፍተኛ ባለስልጣናት እየታየ ያለውን የአክሲዮን ገበያ መውደቅ አሳንሰው አቅርበዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ስኮት ቤሴንት ለኤንቢሲ እንደተናገሩት በዚህ የተነሳ "የኢኮኖሚ ውድቀት" አይከሰትም ብለዋል።
አክለውም "ይህ የማስተካከያ እርምጃ ነው" ሲሉ አክለዋል።
ቤሴንት ፕሬዝደንት ትራምፕ "ለራሳቸው በሚያተርፉበት መልኩ ነው እርምጃውን የወሰዱት፤ እናም ከ 50 አገራት በላይ አስተዳደሩን ከታሪፍ ውጪ የሆነው ንግድ ዝቅ እንዲል፣ ታሪፉ እንዲቀነስላቸው እንዲሁም የምንዛሬ ማስተካከያ ለማቆም ጠይቀዋል" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የንግድ ሚኒስትሩ ሀዋርድ ሉትኒክ ለሲቢኤስ በሁሉም ገቢ እቃዎች ላይ የተጣለው የ10 በመቶ "መነሻ" ታሪፍ "ለቀናት እና ሳምንታት ተግባራዊ ሆኖ ይቀጥላል" ብለዋል።
ሉትኒክ አክለውም በምላሹ ከፍተኛ የሆነ ታሪፍ በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
አሜሪካ "ከባድ አጥፊዎች" ባለቻቸው 60 አገራት ላይ የጣለችው ከፍተኛ ታሪፍ ከረቡዕ ሚያዝያ 1/ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግበራዊ መሆን ይጀምራል።
ስለ እነዚህ ታሪፎች የተጠየቁት ሉትኒክ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተናግረው "[ትራምፕ] ይፋ አድርጓል፤ እየቀለደ አልነበረም" ብለዋል።
በተጨማሪም ሉትኒክ በፔንግዊን ብቻ በተሞሉት ሁለት አነስተኛ የአንታርክቲክ ደሴቶች ላይ የተጣለውን ታሪፍን በሚመለከት ሲናገሩ እንደ ቻይና ያሉ አገራት "ለማጓጓዝ" የሚጠቀሙበትን "ክፍተት" ለመድፈን ነው ሲሉ እርምጃውን ተከላክለዋል።
እንደ ኢንዶኔዢያ እና ታይዋን ያሉ አገራት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ወደ አሜሪካ በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ የ32 በመቶ ታሪፍ ቢጣልባቸውም የአጸፋ እርምጃ እንደማይወስዱ አሳውቀዋል።
የቬትናም መሪ ቶ ላም ትራምፕ ከቬትናም በሚገቡ ምርቶች ላይ የጣሉትን የ46 በመቶ ታሪፍ "ቢያንስ ለ45 ቀናት" እንዲያዘገዩት የሚጠይቅ ደብዳቤ መጻፋቸውን ኤኤፍፒ እና ኒውዮርክ ታይምስ ዘግበዋል።
ቻይና ግን አርብ ዕለት ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ34 በመቶ ታሪፍ ከሐሙስ ጀምሮ ለመጣል ውሳኔ አሳልፋለች።












