በናይጄሪያ በከባድ ዝናብ ምክንያት ጉዳት ከደረሰበት ማረሚያ ቤት ከ100 በላይ እስረኞች አመለጡ

አብዛኛዎቹ የሱሌጃ እስር ቤቶች በቅኝ ግዛት ወቅት የተገነቡ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Nigeria Correctional Service

በናይጄሪያ የጣለው ከባድ ዝናብ በአንድ ማረሚያ ቤት ክፍሎች እና በአጥሩ ላይ ጉዳት በማድረሱ ከ100 በላይ እስረኞች አመለጡ።

እስረኞቹ ያመለጡት ሱሌጃ ከተሰኘው ከናይጄሪያ ዋና ከተማ አቅራቢያ ከሚገኘው ማረሚያ ቤት ነው።

እንደ ባለስልጣናቱ ገለጻ ከሆነ 118 እስረኞች መጀመሪያ ከሱሌጃ ማረሚያ ቤት ቢያመልጡም 10ሩ በድጋሚ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ሌሎቹንም በቁጥጥር ስር ለማዋል ፍለጋ ተጀምሯል።

እስካሁን ድረስ የእስረኞቹ ማንነት ግልጽ ባይሆንም አንዳንዶቹ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ማረሚያ ቤቱ በሰጠው መግለጫ ገልጾ፣ ህዝቡ ያለምንም ፍርሃት መደበኛ ህይወቱን እንዲከውን አሳስቧል።

"ከሌሎች የደህንነት ኤጀንሲዎች ጋር በመተባበር ካመለጡት እስረኞች መካከል እስካሁን 10ሩን መልሰን ወደ እስር ቤት አስገብተናል። የቀሩትን ለመያዝ ደግሞ ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው" ሲል የአቡጃ ማረሚያ ቤት በመግለጫው ጠቁሟል።

ከአቡጃ በ50 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሱሌጃ የሚገኙ አብዛኛዎቹ እስር ቤቶች በቅኝ ግዛት ዘመን የተገነቡ በመሆናቸው ያረጁ እና የተዳከሙ መሆናቸውንም አመልክቷል።

ከሰሞኑ በናይጄሪያ የነበረው የሙቀት ወቅት አብቅቶ ዝናብ ወቅት መግባቱን ተከትሎ ነው ረቡዕ ዕለት ለበርካታ ሰዓታት የዘነበው።

በአንዳንድ ግዛቶች ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል የናይጄሪያ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከሰሞኑን ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

ከሁለት ዓመት በፊት በአቡጃ ከሚገኝ ሌላ እስር ቤት ከ400 በላይ እስረኞች አምልጠዋል።

በእስር ቤቱ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ አራት እስረኞች፣ አንድ የጥበቃ ሠራተኛ እና በርካታ ጥቃት አድራሾች መገደላቸውን ባለስልጣናት በወቅቱ መግለጻቸው ይታወሳል።

እስላማዊ ታጣቂዎች ጥቃቱን የፈጸሙት የተወሰኑ አባሎቻቸውን ለማስለቀቅ እንደሆነ በወቅቱ ተናግረው ነበር።

እአአ ከ 2020 ወዲህ ከናይጄሪያ እስር ቤት ከአምስት ሺህ በላይ እስረኞች አምልጠዋል።

ምንም እንኳን ባለስልጣናት ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራን ነው ቢሉም በርካታ የናይጄሪያ እስር ቤቶች የተጨናነቁ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች የሚሰጡ አይደሉም። ምንም ዓይነት ክስ ያልቀረበባቸው በርካታ እስረኞች መኖራቸውን ተገልጿል። በአንድ እስር ቤት እስከ 70 በመቶ የሚደርሱ እስረኞች ፍርድ እየተጠባበቁ እንደሚገኙ አንድ እስረኛ በቅርቡ ተናግሯል።