ምዕራባውያን ቢሊዮኖችን እያፈሰሱ ዩክሬንን የሚያስታጥቋት ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች

ከባድ የጦር መሣሪያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን የሚሆን 62 ቢሊዮን ዶላር አጽድቀዋል። ይህ ማለት አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ዩክሬን የጦር መሣሪያ እና ተተኳሾችን በገፍ መቅረቧን ትቀጥላለች ማለት ነው።

ዩክሬን አሁን የሚያስፈልጋት ሚሳዔል ነው። በተለይ ደግሞ የሩሲያ ሠራዊት በጦር አውድማ ድል እየቀናው መሆኑን ተከትሎ የጦር መሣሪያ አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ ብሏል።

ለዩክሬን የተገባው ቃል

አሜሪካ ለዩክሬን ብቻ ሳይሆን ለእስራኤል እና ለታይዋንም ወታደራዊ ድጋፍ ታደርጋለች። በጠቅላላው ገንዘቡ 95 ቢሊዮን ዶላር ነው።

አሜሪካ ለዩክሬን ስታደርግ የነበረው ወታደራዊ ድጋፍ የነጠፈው ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት መባቻ ላይ ነው።

የአገሪቱ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ለዩክሬን በሚደረገው ድጋፍ ላይ ባለመስማማቱ ነበር ለዩክሬን ሊደረግ የታሰበው እርዳታ የዘገየው።

አሁን ድጋፉ መጽደቁን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ባይደን የጦር መሣሪያ “አሁኑኑ” መላክ እንጀምራለን ብለዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የተገባው ቃል “አሜሪካ የዲሞክራሲ መከታ መሆኗን እና የነፃው ዓለም መሪ መሆኗን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

ስምንት ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ገንዘብ ለዩክሬን ሚሳኤሎችን እና ተተኳሾችን ለማስታጠቂያነት የሚውል ነው።

የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ደግሞ አገራቸው ቀደም ሲል ለዩክሬን ቃል ገብታ የነበረው 2.5 ቢሊዮን ፓወንድ ድጋፍ እንዳለ ሆኖ 500 ሚሊዮን ፓውንድ ለመጨመር አቅደዋል። ይህ ገንዘብ ተጨማሪ ሚሳኤል ይገዛል፤ የተተኳሽ እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ወጪንም ይሸፍናል።

ሃንጋሪ ለዩክሬን የሚደረገውን ድጋፍ ማገድ ማቆሟን ተከትሎ የካቲት 2024 የአውሮፓ ኅብረት 50 ቢሊዮን ዩሮ እርዳታ አጽድቋል።

ኅብረቱ መጋቢት 1 ለዩክሬን አንድ ሚሊዮን የከባድ መሣሪያ ተተኳሾችን እሰጣለሁ ያለውን ቃል አልፈጸመም።

ነገር ግን ቼክ ሪፐብሊክ ለ18 የኔቶ እና የአውሮፓ ኅብረት አገራት ለ800 ሺህ ተተኳሾች መግዣ የሚሆን 1.5 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች። በርካታ ኪሎ ሜትሮች የሚጓዙት አረሮች የሚገዙት ከአውሮፓ ውጪ ነው።

የለጋስ አገራት ዝርዝር

ከዚህ ቀደም ለዩክሬን የተሰጠው

አሜሪካ እንደምትለው ዩክሬን የጦር መሣሪያ እጥረት ስለገጠማት ወታደሮቿ ለመዋጋት ያላቸው ሞራል አሽቆልቁሏል።

አንደኛው ዩክሬን ያጠራት የአየር መቃወሚያ መሣሪያ ነው።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ዩክሬን ከተሞቿን ለመጠበቅ “ሰባት ፓትሪዮት የተባሉ የአየር መከላከያ ሚሳኤሎች አሊያም ተመሳሳይ መሣሪያ ያስፈልጋታል” ይላሉ።

የለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ ምሑሯ ማሪና ሚሮን “እኒህ መሣሪያዎች ሞስኮ በተለይ የኤልክትሪክ ኃይል ማመንጫ እና ማሰራጫዎችን የመሳሰሉ ሥፍራዎችን እንዳትመታ ያግዛሉ” ይላሉ።

ሩሲያ ለድንበሯ ቅርብ የሆነችውን የዩክሬን ሁለተኛ ትልቋ ተከማ ኻርኺቭን በተደጋጋሚ ደብድባለች። የዩክሬን ብሔራዊ ዘብ አዛዥ ኦሌክሳንድር ፒቬንኮ የሩሲያ ጦር ወደ ከተማዋ መዝለቅ ይጀምራል የሚል ስጋት አላቸው።

ዩክሬናውያን ወታደሮች በቀን መተኮስ የሚፈቅድላቸው 2000 ጥይት ብቻ ነው ይላል የዩኬው ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስስ የተሰኘው ተቋም።

በተቃራኒው የሩሲያ ወታደሮች በቀን እስከ 10 ሺህ ጥይት መተኮስ ይችላሉ። ተቋሙ እንደሚለው ሩሲያ ራሷ ከምታመርተው እና ከሰሜን ኮሪያ የምተቀበለውን ጨማምራ በዓመት 3 ሚሊዮን ጥይት አላት።

ዩክሬን ካለፈው ጥቅምት 2023 ጀምሮ በምሥራቁ በኩል 583 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆነውን ድንበሯን በሩሲያ ኃይሎች የተነጠቀችው በጦር መሣሪያ እጥረት ነው።

ባለፈው የካቲት አቭዲቭካ ከተማ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር የዋለችው በጦር መሣሪያ እጥረት ምክንያት መሆኑን ተናግራ ነበር።

አሁን አሜሪካ የጦር መሣሪያ ድጋፍ አደረገች ማለት ዩክሬን መልሶ ማጥቃት ትጀምራለች ማለት ነው።

ከባድ የጦር መሳሪያዎች ምስል

ምዕራባዊያን ለዩክሬን የሰጡት የጦር መሣሪያ

ፀረ-ታንክ

ምዕራባዊያን ለዩክሬን መከላከያ ሠራዊት የጦር መሣሪያ በመስጠት ሩሲያ ለከፈተችባት ጦርነት ያላቸውን አመለካከት አሳይተዋል።

አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ጃቪሊን እና ንላው የተባሉ ፀረ-ታንክ ሚሳኤሎችን አስታጥቀዋታል።

እነዚህ የጦር መሣሪያዎች ሩሲያ ወደ ዩክሬን መዲና ኪዬቭ የምታደርገውን ግስጋሴ በመግታት ይታወቃሉ።

ምዕራባዊያን ከፀረ-ታንክ ሚሳኤሎች ባለፈ የተለያዩ የአየር ጥቃት መቃወሚያ መሣሪያዎችን ለዩክሬን ሰጥተዋል።

ፀረ ታንክ

አየር መቃወሚያ

ዩኬ አጭር ርቀት የሚጓዙ ፀረ-አውሮፕላን መሣሪያዎችን ለዩክሬን ሰጥታለች። ሌሎች አገራት ደግሞ ስታርስትሬክ እና ፓትሪዮት የተባሉ ሚሳኤሎችን አስታጥቀዋታል።

ፓትሪዮት የሚባሉት ሚሳኤሎች እጅግ ውድ ሲሆኑ፣ አንድ ሚሳኤል ለመተኮስ 3 ሚሊዮን ዶላር ያስወጣል።

አሜሪካ እና ኖርዌይ ደግሞ ከምድር ወደ ሰማይ የሚምዘገዘጉ ናሳምስ የተባሉ መሣሪያዎችን ሲያዋጡ፣ ጀርመን አይሪስ-ቲ የተባለውን መሣሪያ ሰጥታለች።

ስታርስትሪክ ሚሳኤል
ፓትሪዮት ሚሳኤል

ሚሳኤል እና ከባድ መሣሪያ

ሩሲያ ከዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ ካፈገፈገች በኋላ ጦርነቱ በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል አትኩሯል። ሚሳኤሎች እና ሌሎች ከባድ የጦር መሣሪያዎች ከሁለቱም በኩል ተተኩሰዋል።

አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና አሜሪካ ኤም777 የተባለውን ከባድ የጦር መሣሪያ እና ተተኳሽ ለዩክሬን ሰጥተዋል።

ሆዊትዘር
የመድፍ ርቀት

በተጨማሪ አሜሪካ እና ዩኬ ሂማርስ እንዲሁም ኤም270 ኤምኤልአርኤስ የተባሉ የሚሳኤል ዓይነቶችን ለዩክሬን አበርክተዋል።

ረዥም ርቀት የሚጓዘውን ስካልፕ ፈረንሳይ ስትሰጥ፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ስቶርም ሻዶው የተባለውን ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ለዩክሬን አስታጥቀዋል።

ሐምሌ 2023 አሜሪካ ለዩክሬን ክላስተር ቦምብ መስጠቷ ይታወሳል። ክላስተር ቦምቦቹ የሩሲያን ምሽግ ለመሰባበር ጥቅም ላይ እንዲውሉ የታሰቡ ናቸው።

እነዚህ ከከባድ የጦር መሣሪያ የሚተኮሱ ቦምቦች ውስጣቸው የተለያዩ ትናንሽ ቦምቦችን የያዙ ሲሆን፣ ከ100 በላይ አገራት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት ስለሚያደርሱ በሚል ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አግደዋቸዋል።

ሂማርስ

ታንክ

በ2023 መባቻ ነው ምዕራባዊያን አገራት ለዩክሬን ታንኮችን ለመላክ የተስማሙት።

እነዚህ ታንኮች ዩክሬን የሩሲያ መከላከያ አጥርን ሰብራ እንድርትገባ ለማገዝ ነበር የተላኩት። ዩኬ በወቅቱ ቻሌንጀር 2 የተባለውን ዘመናዊ ታንክ ሰጥታለች።

ቻሌንጀር ታንክ 2

አሜሪካ 32 ኤብራምስ የተባሉትን ታንኮች ስትልክ የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ ጀርመን ሥሪት በርካታ ሊዮፓርድ 2 ታንኮችን ሰጥቷል።

አሜሪካ ሠራሹ ኤም1 ኤብራምስ ምድራችን ላይ ካሉ ታንኮች እጅግ ዘመናዊው ነው ይባልለታል።

ነገር ግን እነዚህ አዳዲስ የጦር መሣሪያዎች ዩክሬን በመልሶ ማጥቃቱ ድል እንድትጎናፀፍ ሊያግዟት አልቻሉም።

ኤብራምስ ታንክ

ድሮኖች

በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ድሮኖች በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ውለዋል። ከስለላ ጀምሮ እስኪ ዒላማ እና ሚሳኤል ማስወንጨፊያ እንዲሁም አጥፍቶ ጠፊ 'ካሚካዚ' ድሮኖች ሁለቱም አገራት ተጠቅመዋል።

ቱርክ ሚሳኤል የሚተኩሱ ባይራክታር ቲቢ2 የተባሉ ድሮኖችን በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ አቅርባለች። አሜሪካ ደግሞ “ስዊችብሌድ” አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖችን ስታቀርብ በርካታ አገራት የቻይናውን ለስለላ የሚያግዝ ዲጄአይ ማቪክ 3 የተባለውን ድሮንን ጨምሮ ሌሎች ድሮኖችን ልከዋል።

የካቲት 2024 የዩኬ መንግሥት ለዩክሬን በሺዎች የሚቆጠሩ ለስለላ እና ዒላማ ለመምታት የሚያግዙ ድሮኖችን የሚልኩ አገራትን መቀላቀሉን አስታውቋል።

ማቪክ 3

ተዋጊ ጄቶች

ዩክሬን፤ ሩሲያ በሰማይ ያላትን ኃያልነት ለመግታት በተደጋጋሚ አሜሪካ ተዋጊ ጄቶች እንድትሰጣት ጠይቃለች።

ግንቦት 2023 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሌሎች አገራት ለዩክሬን አሜሪካ ሠራሹን ኤፍ-16 ጄትን ለዩክሬን እንዲሰጡ ፈቀዱ። በወቅቱ ዴንማርክ እና ኔዘርላንድስ እርዳታ ለማድረግ ተስማምተው ነበር።

የዩክሬን አብራሪዎች እነዚህን የጦር ጄቶች ለማብረር የሚሆን ልምምድ በ11 ምዕራባውያን አገራት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ኤፍ-16 ተዋጊ ጄት