እስራኤል ኳታር ውስጥ ዒላማ ያደረገችው የሐማስ ዋና ተደራዳሪ ማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል ማክሰኞ ዕለት በዶሃ በሐማስ ተደራዳሪ ቡድን ላይ ድንገተኛ የአየር ድብደባ ፈጽማለች። ቀዳሚ ዒላማዋ ደግሞ የታጣቂ ቡድኑ ዋና ተደራዳሪ ኻሊል አል-ሀያ ይመስላል።
የእስራኤል ባለስልጣን ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት የሐማስ አባላትን ዒላማ ያደረገው ጥቃት በዋነኛነት ዋና ተደራዳሪውን እና በግዞት የሚገኘውን የጋዛ መሪ ኻሊል አል-ሀያ እና በስደት ላይ የሚገኘውን የዌስት ባንክ መሪ ዛህር ጃባሪን ነው።
ሐማስ አምስት አባላቶቹ መገደላቸውን ገልጾ ነገር ግን ተደራዳሪ ቡድኑን ለመግደል የተደረገው ሙከራ "ከሽፏል" ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጥቃቱን "የኳታርን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን የሚጋፋ ነው" ማለታቸውን ጨምሮ ጥቃቱ ዓለም አቀፍ ውግዘት እያስተናገደ ሲሆን የኳታር መንግስት በቁጣ ምላሽ ሰጥቷል።
ጥቃቱን ግድ የለሽ፣ አሳፋሪ እና ሁሉንም ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጥስ ነው ብሎታል።
የባህረ ሰላጤዋ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አንድ የአገር ውስጥ ደህንነት አባል መገደሉን አስታውቋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንዳሉት ጥቃቱ መስከረም 26 ቀን 2016 በእስራኤል ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ባቀዱት የሐማስ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ያነጣጠረ "በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ተገቢ ነው" ብለዋል።
የሐማስ ዋና ተደራዳሪ
አሁኑ የጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ኻሊል አል-ሀያ በኳታር እና በግብጽ አሸማጋዮች በኩል ለእስራኤላውያን እና ለአሜሪካውያን መልዕክት እየላከ እና እየተቀበለ የሐማስ ዋና ተደራዳሪነት ሚናው እየተወጣ ነበር።
ኢስማኢል ሃኒዬ እና ያህያ ሲንዋር ባለፈው ዓመት ከተገደሉ በኋላ በሐማስ አመራር ውስጥ ዋናው ሰው እየሆነ መጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለመሆኑ ማን ነው?
"አቡ ኦሳማ" በመባልም የሚታወቀው ኻሊል ኢስማኢል ኢብራሂም አል-ሀያ እአአ ጥር 1960 በጋዛ ሰርጥ ተወለደ።
አል-ሀያ ከእስልምና ህግ ጋር በተያያዘ ትምህርት የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪውን የሠራ ሲሆን ሁሉም በ1980ዎቹ በፍልስጤም ማህበረሰብ ውስጥ በነበረው ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴው ይታወቅ ነበር።
እአአ በ1987 ከተቋቋመ ጀምሮ የሐማስ አባል ሲሆን በዚያው ዓመት በእስራኤል ላይ በተደረገው የመጀመሪያው የፍልስጤም ኢንቲፋዳ አመፅ ተሳትፏል። አልሀያ በ1990ዎቹ በእስራኤል እስር ቤት በሽብርተኝነት ተከሶ ሦስት ዓመታትን አሳልፏል።
እአአ በ2006 በጋዛ በተካሄደው የህግ አውጭ ምርጫ ተወዳድሮ በሃማስ ቡድን ውስጥ መቀመጫ አገኘ። በኋላም የህብረቱ ምክር ቤት መሪ ሆነ።
እአአ በ2007 እና በ2014 የግድያ ሙከራ በሚመስል መልኩ ቤቱ ሁለት ጊዜ በቦምብ ተደበደበ።
በሁለቱም ጥቃቶች ምክንያት በርካታ የቤተሰብ አባላቱን አጥቷል። የመስከረም 26ቱን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ጥቃት የቤተሰብ አባላቱን አጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል ግድያ ስጋት
እአአ ግንቦት 2025 የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትስ አል-ሀያን ለመግደል በይፋ ዝተዋል።
የሐማስ ተደራዳሪው ለቴህራን ቅርብ ነው ተብሎ ይታሰባል። እአአ በ2022 የሐማስ ልዑካንን መርቶ የወቅቱን ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድን ለመገናኘት ወደ ደማስቆ አቅንቶ ነበር።
ዓላማውም ከሶሪያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ ነበር።
በ2023 ወደ ሊባኖስ የልዑካን ቡድን በመምራት ከወቅቱ የሂዝቦላህ ዋና ጸሐፊ ሃሰን ናስራላህ ጋር ተገናኘ።
ከጥቅምት 2023 ጀምሮ ደግሞ አል-ሀያ ከእስራኤል ጋር ድርድርን መርቷል። ኳታር ከ2012 ጀምሮ የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ መቀመጫ ስትሆን ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድርን በማመቻቸት ቁልፍ ሚና ተጫውታለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሐማስ ተደራዳሪዎቹ ዒላማ እንደነበሩ ተናግሯል
በዶሃ የሚገኘው የቡድኑ ተደራዳሪዎች ማክሰኞ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ዒላማ ቢደረጉም በሕይወት ተርፈዋል ሲል ሐማስ አስታውቋል። የአል-ሀያ ልጅ ሁማም አልሀያ እና የአል-ሀያ ቢሮ ዳይሬክተር ጂሃድ ላባድን ጨምሮ ሌሎች 6 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
ሐማስ በመግለጫው "ጠላት የተደራዳሪ ቡድኑ ውስጥ ያሉትን ወንድሞቻችንን ለመግደል አለመቻሉን እናረጋግጣለን" ብሏል።
"ጥቃቱ ኔታንያሁ እና መንግስታቸው ምንም አይነት ስምምነት ላይ መድረስ እንደማይፈልጉ የበለጠ በላይ የሚያረጋግጥ ነው" ሲል አክሏል።















