ቴሌግራም የአክራሪ ቡድኖችን መረጃ ለተጠቃሚዎች እንደሚያስተዋውቅ አንድ ጥናት አመላከተ

ቴሌግራም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቴሌግራም ጽንፈኛ ይዘትን የሚያስተዋውቅ አልጎሪዝም ይጠቀማል ሲል ለቢቢሲ ብቻ የተጋራ አዲስ ጥናት አመላከተ።

በቴሌግራም ባለፈው ዓመት የተዋወቀው "ተመሳሳይ ቻናሎች" የሚለው አሠራሩ ታዋቂ ሰዎችን ወይም እንደ ቴክኖሎጂ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን እንኳን ሳይቀር ለሚፈልጉ ሰዎች ጽንፈኛ ቻናሎችን እንደአማራጭ ያቀርባል ሲል የአሜሪካ የዜጎች መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው የሳውዘርላንድ ፖቨርቲ ሎው ሴንተር (ኤስፒኤልሲ) ጥናት ገልጿል።

ቴሌግራም ላይ በ850 ፓውንድ ተከፍሎት ኡዚ የተሰኘውን የጦር መሣሪያ ወደ እንግሊዝ ለመላክ የሚችል ሰው እንዴት እንዳገኘ አንድ ፕሮፌሰር ለቢቢሲ ፓኖራማ አሳይቷል።

ቴሌግራም በበኩሉ ተጠቃሚዎች "ለማግኘት የፈለጉት ይዘት ብቻ ነው የሚቀርብላቸው"፤ በየቀኑም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎጂ ይዘቶችን አስወግዳለሁ ብሏል።

የኩባንያው መስራች ሩሲያዊው ቢሊየነር ፓቬል ዱሮቭ በማኅበራዊ መድረኩ ላይ የወንጀል ድርጊቶችን ማስቆም ባለመቻሉ በፈረንሳይ ምርመራ እየተካሄደበት ነው። ዱሮቭ ክሱን አስተባብሏል።

ምስጢራዊ ባህሪያት እንዳለው ሆኖ ለገበያ የቀረበው ቴሌግራም ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎቹ አሉት። ተጠቃሚዎች በአንድ ጊዜ እስከ 200 ሺህ ሰዎች መልዕክት እና ቪዲዮዎችን የሚያስተላልፉባቸውን ቡድኖች (ግሩፕ) እንዲያቋቁሙ ያስችላቸዋል።

የኤስፒኤልሲ ተመራማሪዎች "የቴሌግራም መርዛማ ምክሮች" ለተሰኘው ሪፖርታቸው 28 ሺህ የሚሆኑ የቴሌግራም ቻናሎች ተመልክተዋል።

ተጠቃሚዎች መደበኛ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን ሲፈልጉ በርካታ ጽንፈኛ ይዘቶችን እንደሚመክር ታውቋል። ተጠቃሚዎች እንደ ጸረ-መንግስት ሴራዎች ያሉ ጽንፈኛ ይዘቶችን አንዴ ሲመለከቱ ደግሞ እንደ ጸረ-ሴማዊነት ወይም የነጭ ብሔርተኝነት ወደ መሳሰሉ ሌሎች ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ይገፋሉ።

የፈረንሳይ ባለስልጣናት ፓቬል ዱሮቭ አደንዛዥ እጽን በማዘዋወር፣ በተደራጀ ወንጀል እና በቴሌግራም ላይ የልጆች ጥቃት ምስሎችን በማጋራት ላይ ተባባሪ በመሆን ከሰውታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቡድኑ መሪ ተመራማሪ ሜጋን ስኩየር አዲስ በተዘጋጀ የቴሌግራም አካውንት አማካኝነት "ዶናልድ ትራምፕ" የሚለውን ጽፋ በመፈለግ የቴሌግራም አልጎሪዝሙ እንዴት እንደሚሠራ አሳይታለች።

"ተመሳሳይ ቻናሎች" በሚለው ዝርዝር ውስጥ ትራምፕ በመንግስት፣ በቢዝነስ እና በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ በሰይጣን አምላኪዎች ላይ ሚስጥራዊ ጦርነት እንደሚያካሂዱ የሚያሳይ የኪው-አነን ሴራን የሚያስተዋውቁ በርካታ ምሳሌዎች ይመጣሉ።

"የዩኬ ብጥብጥ" ሲፈለግ ደግሞ ስለአዶልፍ ሂትለር የተሠራ ሜም መጀመሪያ ላይ ብቅ ይላል። በመቀጠልም ደግሞ በአመጸኛ ቀኝ ዘመም ቡድኖች የሚመሩ ቻናሎች በተከታታይ ይቀመጣሉ።

ሜጋን ስኩየር

"ከእነዚህ ቡድኖች ውስጥ የተወሰኑት በጣም ንቁ ናቸው። በቴሌግራም ላይ ሜም እያገኙ ብቻ ሳይሆን ወደ ተጨባጭ ክስተቶች እየገቡ ነው። መሬት ላይ እየሆኑ ያሉ ክስተቶችን እያቀረቡ ነው" ሲሉ ስኩየር ተናግራለች።

ብጥብት ከቀሰቀሰው ከነሐሴው የሳውዝፖርት የቢላዋ ጥቃት በኋላ በነበሩት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ የቴሌግራም ተጠቃሚዎች የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪዎችን ለጥፈዋል። ምክነያት ያሉት ደግሞ ትቃት አድራሹ ጥገኝነት ጠያቂ ነው በሚል ሃሰተኛ መረጃ ጋር ነው።

ስኩየር ለቢቢሲ ፓኖራማ እንደተናገሩት ከሆነ ቴሌግራም "ዲጂታል ስጋት" መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል።

"[በዚህ ረገድ] ከአንድ እስከ 10 ባለው መዝኚው ብባል እኔ ለቴሌግራም የምሰጠው 11 ነጥብ ነው። እጅግ በጣም ብዙ የወንጀል እና ጽንፈኛ ይዘቶችን እያስተላለፈ ነው። በእኔ እምነት እጅግ አደገኛ ነው" ብላለች።

ለስድስት ዓመታት የቴሌግራም ባልደረባ የነበረው ኤሊያስ ካምፖ ለፓኖራማ እንደተናገረው እአአ በ2021 ስለ ጽንፈኛ መልዕክቶች ፓቬል ዱሮቭን ሞግቶ ነበር።

"የእሱ አቋም የነበረው ማን መናገር እንዳለበት ለመወሰን እንደ እኛ ያለ መድረክ አይደለም የሚወስነው። ተጨማሪ ሃብቶችን መስጠት እንደማይፈልግ ግልጽ ነበር" ብሏል ካምፖ።

"እኔ እንደማስበው ከሆነ እሱ መምረጥ ዕድል ቢሰጠው ምንም አለማድረግን በይበልጥ ይመርጣል።"

ቴሌግራም ላይ የሚገኙ ህገወጥ ይዘቶችን በማጥናት ስድስት ዓመታትን ያሳለፉት የጆርጂያ ስቴት ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ዴቪድ ማይሞን ከአጭበርባሪዎች መሣሪያ ከመሆን እስከየጦር መሣሪያ ያሉትን በሙሉ የሚያቀርቡ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ቻናሎች እንዳሉ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ዴቪድ ማይሞን በደቂቃዎች ውስጥ ኡዚ የሚሸጥለት ሰው አገኘ

"ቴሌግራም በእርግጠኝነት አሁን ወንጀለኞች ለወንጀል ከሚጠቀሙባቸው በጣም አስፈላጊ ስርዓቶች አንዱ ነው" ብለዋል።

እንዴት እንደሚሠራ ለማሳየትም "ኡዚ እና ሽጉጥ" ያስፈልገኛል የሚል መልዕክት በለጠፈ በደቂቃዎች ውስጥ አንድ ሻጭ የኡዚ ምስል ለጥፎ በሁለት ወይም ሶስት ቀናት ውስጥ ቤልፋስት በሚገኘው የፓኖራማ አድራሻ "በፍጥነት መላክ እችላለሁ" ብሏል።

የፈረንሳይ ባለስልጣናት ፓቬል ዱሮቭ አደንዛዥ እጽን በማዘዋወር፣ በተደራጀ ወንጀል እና በቴሌግራም ላይ የልጆች ጥቃት ምስሎችን በማጋራት ላይ ተባባሪ በመሆን ከሰውታል። በአሁኑ ጊዜ በዋስ ቢለቀቀም እና ከፈረንሳይ መውጣት አልተፈቀደለትም።

ቴሌግራም በበኩሉ አክራሪ እና ህገወጥ ይዘትን እንደሚቆጣጠር እና ተቆጣጣሪዎቹ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመጠቀም በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎጂ ይዘቶችን አስወግዳለሁ ብሏል።

ተጠቃሚዎቹ የተመዘገቡበትን ይዘት ብቻ ነው የሚቀበሉት ከማለት ባለፈ ቴሌግራም የትኛውንም "ይዘትን አያስተዋውቅም" ሲል አክሏል።

"'የቻናል ጥቆማዎች' ተጠቃሚው ከሚከተለው ጋር ተመሳሳይ ርዕስ ያላቸውን ዘርፎች ብቻ ያሳያል። አካሄዱ ተጠቃሚዎች ለመሳተፍ የመረጡት ይዘት ብቻ የሚያቀርብላቸው ነው። ይህ ሌሎች መድረኮች ጥቆማዎችን ከሚሰጡበት አካሄድ ፈጽሞ የተለየ ነው" ሲል ኩባንያው አክሏል።

ቴሌግራም "ይዘቶች ከማስተዋወቅ ይልው ከተጠቃሚ ምርጫዎች ጋር የተያያዙ ጥቆማዎችን ያሳያል" ብሏል።