በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሞተው ጥቁር አሜሪካዊ አሟሟትን የሚያሳይ ቪዲዮ ወጣ

የፎቶው ባለመብት, BEN CRUMP LAW
በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት በአንድ የአዕምሮ ህክምና ሆስፒታል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆኖ እየታከመ የነበረ ታራሚን አሟሟት የሚያሳይ ቪዲዮ ይፋ ሆኗል።
ይህንን ቪዲዮ ለህዝብ ይፋ እንዲሆን ያደረጉት የግዛቲቷ አቃብያነ ህግ ሲሆኑ ፖሊሶችና የሆስፒታሉ ሰራተኞች እስረኛውን መሬት ላይ አጣብቀውትና ላዩ ላይ ተጭነውትም ያሳያል።
ኢርቮ ኦቲኖ ከማረሚያ ቤት ወደ ህክምና ማዕከሉ የተወሰደው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር።
በኢርቮ ሞት ሰባት ፖሊሶች እና ሶስት የሆስፒታሉ ሰራተኞች በሁለተኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ በአስር ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱንም አስታውቋል።
አን ካቤል የተሰኙት አቃቤ ህግ ማክሰኞ እለት ነው የኢርቮን አሟሟት የሚያሳየውን ቪዲዮ ለህዝብ ይፋ ያደረጉት።
ኢርቮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው በስርቆት ተጠርጥሮ ሲሆን ይህም ከሶስት ሳምንታት በፊት መሆኑንም ፖሊስ አስታውቋል።
ኢርቮ በድንገተኛ ቁጥጥር ስር እንዲሆን ተደርጎ ነበር ተብሏል፤ ይህም አንድ ግለሰብ በአዕምሮ ህመም ምክንያት ራሱንም ሆነ ሌሎችንም ሊጎዳ ይችላል ተብሎ በሚታመንበት ወቅት ተግባራዊ የሚሆን ነው።
ድምጽ በሌለው በዚህ ቪዲዮ ላይ በአራት አመቱ ከኬንያ ወደ አሜሪካ የተሰደደው የ28 ዓመቱ ኢርቮ በበርካታ ፖሊሶች ታጅቦ እጁና እግሩ በካቴና እና በእግር ብረት ታስሮ ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ ያሳያል።
የሆስፒታሉ ሰራተኞችም ከኋላ ሲከተሉት ነበር።
ፖሊሶች ኢርቮን መሬት ላይ አስተኝተውት ሲጫኑት የሚያሳዪት ሲሆን መጀመሪያ ሲመለከቱ የነበሩ የህክምና ሰራተኞችም ከፖሊሶቹ ጋር ተደምረው አብረው ተጭነውትም ታይቷል።
ቢያንስ ስምንት ሰዎችም ኢርቮ ላይ ተጭነውት ታይተዋል። አንዳንዶቹ እግሩን የያዙት ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ከወገቡ በላይ መሬት ላይ አጣብቀውት ነበር።
በኋላ ላይ አስር የሚደርሱ ፖሊሶችና የህክምና ሰራተኞች እርቃኑን የነበረውና እጁና እግሩ የታሰረውን ኢርቮን መሬት ላይ አጣብቀው ተጭነውት ያሳያል። ኢርቮን መሬት ላይ አጣብቀውት የነበረው ለአስራ አንድ ያህል ደቂቃዎች ነበር።
ኢርቮ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን፤ ሰውነቱ በድን ሲሆንባቸውም ፖሊሶች ከላዩ ላይ ተነስተዋል። በክፍሉ ውስጥ ያሉ የህክምና ባለሙያዎችም የአደጋ ጊዜ እርዳታ ለመስጠት ሲሞክሩ ታይተዋል።












