የቲክቶክ ዋና መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በምግብ መመረዝ ተጠቅተው ሆስፒታል ገቡ

የባይትዳንስ ዋና ቅርንጫ - ሲንጋፖር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጅምላ የሚቆጠሩ ሲንጋፖር የሚገኘው የቲክቶክ ዋና መስሪያ ቤት ሠራተኞች በምግብ መመረዝ ተጠቅተው ሆስፒታል ገቡ።

የከተማዋ የጤና እና ምግብ ደኅንነት ባለሥልጣናት የተከሰተው የምግብ መመረዝ እየመረመሩት እንደሆነ አስታወቀዋል።

ማክሰኞ ዕለት ከ60 በላይ ሰዎች የሆድ ቁርጥ መሰል በሽት የተስተዋለባቸው ሲሆን ሀምሳ ሰባቱ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል አምርተዋል።

ባይትዳንስ የተባለው የቲክቶክ እናት ኩባንያ ሠራተኞቹ በምን ምክንያት ሊታመሙ እንደቻሉ እየጣራ እንደሆነ ገልጧል።

ቢቢሲ እንደተገነዘበው በባይትዳንስ ዋና ቢሮ ምንም ዓይነት ምግብ የሚዘጋጅ ባይሆንም ሠራተኞች የሚመገቡት ከውጭ ተዘጋጅቶ የሚገባ ምግብ ነው።

የሀገሪቱ መገናኝ ብዙኃን እንደዘገቡት ሕንፃው ወደሚገኝበት የሲንጋፖር የቢዝነስ ማዕከል 7 አምቡላንሶች ተልከው ሕመም ላይ ለወደቁ ሰዎች እርዳታ ሲያደርጉ ነበር።

“የሠራተኞቻችን ጤና እና ደኅንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው። የታመሙ ሠራተኞችን ለመርዳት ጥረት እያደረግን ነው። ይህን ለማድረግ ከመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ሠራተኞች ጋር እየተባበርን ነው” ብሏል።

የሲንጋፖር ምግብ ኤጀንሲ እና የከተማዋ የጤና ሚኒስቴር በጋራ ባወጡት መግለጫ “የምግብ አቅራቢ ድርጅቶች የምግብ ደኅንነትን ለመጠበቅ ተጠንቅቀው ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል።

“የሲንጋፖር ምግብ ኤጀንሲ ምግብ አቅራቢ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ አያመነታም” ይላል መግለጫው።

በአውሮፓውያኑ 2012 በቻይናዊያን የተመሠረተው ባይትዳንስ ቻይና ውስጥ ዶዩን የተሰኘ የቪድዮ መተግበሪያ በመሥራት ነው እውቅና ያተረፈው።

ድርጅቱ ከአንድ ዓመት በኋላ ዶዩንን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በሚል ቲክቶክን ይፋ አደረገ።

ቻይና ውስጥ አገልግሎት የማይሰጠው ቲክቶክ በተቀረው ዓለም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች አሉት።

ቲክቶክ ምንም እንኳ አሁን ሎስ አንጀለስ እና ሲንጋፖር በሚገኙ ድርጅቶች ቢመራም ዋናው ባለቤቱ ባይትዳንስ ነው።