ካማላ ሃሪስ በአፍሪካ፣ በቻይና፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሩሲያ ላይ የሚኖራቸው ፖሊሲ ምን ሊመስል ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጆ ባይደን ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ ካማላ ሃሪስ የዴሞክራቶች ፊታውራሪ ሆነው ብቅ ብለዋል።
ካማላ ሃሪስ ኅዳር 2017 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ ዕጩ ሆነው በመቅረብ ዶናልድ ትራምፕን ቢያሸንፉ አዲስ ታሪክ ይጽፋሉ።
በዚህም ሃሪስ የዩናይትድ ስቴትስ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በተጨማሪ ከስደተኛ ወላጆች የተገኙ ሁለተኛዋ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።
ለመሆኑ ሃሪስ ፕሬዝዳንት ቢሆኑ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በቻይና፣ በዩክሬን እና በሩሲያ እንዲሁም በኔቶ ጉዳዮች የሚኖራቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምን ሊመስል ይችላል?
አፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ
እአአ 2023 በተደረገ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት፤ ወደ አፍሪካ ከመጡ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት መካከል ሃሪስ ይገኙበታል።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ በአፍሪካ ጉብኝት ማድረጋቸው አሜሪካ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የማጠናከር ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ካማላ ከጥቂት ወራት በፊት በአህጉሪቱ 80 በመቶ ሕዝብ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል እሠራለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል።
የካማላ አስተዳደር ቻይና እና ሩሲያ በአፍሪካ ትልቅ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተከትሎ አሜሪካ እንዲሁ ከአህጉሪቱ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሠሩ ይገመታል።
አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ፖሊስ በካማላ ሃሪስ አስተዳደር ወቅት ዳግም መልሳ ልታጤነው ይችላል።
ሃሪስ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በየመን ሲያካሂድ የቆየውን ወታደራዊ ዘመቻ እንዲገታ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
ካማላ ሃሪስ ሴናተር ሳሉ አሜሪካ ለሳዑዲ አረቢያ የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዲገታ የሚያደርግ ሕግን ደግፈው ነበር።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ ሳዑዲ መራሹ ኃይል በየመን ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ እንዲሁም በጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ ምክንያት ሪያድን አጥብቀው ሲተቹ ይሰማሉ።
ይሁን እንጂ ሃሪስ አገራቸው ሽብርተኝነትን መዋጋትን በሚጨመር የጋራ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር አብራ እንደምትሠራ ተናግረው ነበር።
ሃሪስ የመንግሥታቱ ድርጅት አምስቱ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት እና ጀርመን ከኢራን ጋር የደረሱትን የኑክሌር አጠቃቀምን በተመለከተ የተደሰውን ስምምነት ደግፈው ነበር።
ይህ ስምምነት በኢራን የኑክሌር መሠረተ ልማቶች ላይ ክትትል እና ማዕቀብ የሚጥል እንዲሁም በኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን የሚያነሳ ነበር።
ይሁን እንጂ ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት መሆናቸውን ተከትሎ አሜሪካ ስምምነቱን አፍርሳ በመውጣት ኢራን ላይ ማዕቀቦችን ጥላለች።
ከዚህ በተጨማሪ በዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ እአአ በ2020 የተፈጸመውን የኢራኑን ከፍተኛ የጦር መኮንን፣ ጄኔራል ቃሲም ሱሌማኒ ግድያን ሃሪስ ተችተው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዩክሬን
ዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖች በወጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቻቸው ላይ ከሚለያዩባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የዩክሬን ጉዳይ ነው።
ካማላ ሃሪስ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ዩክሬን የጆ ባይደን አስተዳደር የሚያሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ እና የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ በይፋ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
ትራምፕ በሩሲያ ወረራ የተጀመረውን ጦርነት ለማስቆም ዩክሬንን ማስታጠቅ መፍትሄ ነው ብለው አያስቡም።
ዩክሬን የሩሲያን ወረራ መከላከል እንዲቻላት ወታደራዊ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ አገራት ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው ይመረጡ ይሆን ወይ? የሚለው ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል።
በተለይ በአውሮፓ የሚገኙ አገራት የትራምፕ መመረጥ ለዩክሬን የሚደረገውን ወታደራዊ ድጋፍ ሊያዳክም ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
በአንጻሩ ካማላ ሃሪስ፤ “ገንዘብ ለዩክሬን እና ለእስራኤል መስጠት አለብን። የምናደርገው ድጋፍ እጅግ ወሳኝ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ካማላ ሃሪስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዩክሬን ጉዳይ በመከረው እና በስዊትዘርላንድ በተካሄደው ስብሰባ አሜሪካን ወክለው መሳተፋቸው ይታወሳል።
በተቃራኒው የትራምፕ እና የጄዲ ቫንስ “ቅድሚያ ለአሜሪካ” በሚለው ፖሊሲያቸው ዩክሬን የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ፍላጎት እና ጥያቄዎች ምላሽ እንድትሰጠ ጫና ሊያሳድር ይችላል ይላሉ።
ይህ ደግሞ በተለይ የአውሮፓ መንግሥታት የትራምፕ አስተዳደር ዩክሬን ግዛቷን አሳልፋ በመስጠት የተኩስ አቁም ስምምነት እንድትፈርም ያስገድዳል የሚል ስጋት አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኔቶ እና ሩሲያ
ካማላ ሃሪስ አገራቸው አሜሪካ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) ለመደገፍ የተቻላትን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
በአንጻሩ ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስን ከኔቶ ስብስብ አስወጣለሁ እስከ ማለት የደረሰ ማስፈራሪያ መሰንዘራቸው ይታወሳል።
ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው አሜሪካ በኔቶ ስም ብዙ እየተበዘበች ነው የሚል ነው።
የኔቶ አባል አገራት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርትታቸው 2 በመቶውን ለድርጅቱ ማዋጣት ይኖርባቸዋል።
ትራምፕ የሚጠብቅባቸውን ይህንን የኔቶ መዋጫ ማዋጣት የማይችሉ አባል አገራት “እንዲወረሩ ሩሲያን አበረታታለሁ” ሲሉ ጭምር ተሰምተዋል።
ለዚህ የትራምፕ አስተያየት ካማለ ሃሪስ ምላሽ ሲሰጡ፤ “ጨቋኝ መሪ አጋሮቻችን የሆኑ አገራትን እንዲወር ማብረታታት ለሩሲያው አምባገነን መሪ ማጎንበስ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
እስራኤል እና የጋዛ ጦርነት
ካማላ ሃሪስ እስራኤል ከሚደርስባት ጥቃት እራሷን የመከላከል መብት አላት ሲሉ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ባለችው ጦርነት የደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚያሳስባቸው በይፋ ተናግረዋል።
ከቀናት በፊት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ዋሽንግተን በተገኙ ወቅት ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጠይቀዋቸዋል።
ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለዘብተኛ ንግግር በተለየ መልኩ ሃሪስ በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እያደረሰ ያለው ጉዳት “እጅጉን ያስስበኛል” ሲሉም ተናግረዋል።
ትራምፕ በሥልጣን ዘመናቸው፤ ከጋዛው ጦርነት በፊት ለእስራኤል ጠንካራ ድጋፋቸውን ይሰጡ ነበር። ወደ እስራኤል በተጓዙበት ወቅትም የእስራኤል መዲና እየሩሳሌም ነች ብለው ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም ትራምፕ ለሥራ ጉብኝት ወደ እስራኤል ሄደው፤ የአሜሪካን ኤምባሲን ወደ ኢየሩሳሌም አዘዋውረው ብዙ አወዛግበው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የስደተኞች ጉዳይ
ሃሪስ በባይደን አስተዳደር ውስጥ ተሰጥተዋቸው ከነበሩ ኃላፊነቶች መካከል በሜክሲኮ ድንበር ላይ ያለውን የስደተኞች ቀውስ መከታተል አንዱ ነው።
ይሁን እንጂ ሃሪስ የተሰጣቸውን ኃላፊነት መወጠት አልቻሉም በሚል በትራምፕ እና በሌሎች የአገሪቱ ፖለቲከኞች ተወቅሰዋል።
የባይደን እና የሃሪስ አስተዳደር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ድንበር አቋርጠው እንዲገቡ እየፈዱላቸው ነው በሚል ይተቻሉ።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2023 ብቻ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ ለመግባት የሞከሩ 2.5 ሚሊዮን ስደተኞች በሕግ አስከባሪዎች ተይዘዋል።
ሃሪስ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ወደ አሜሪካ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከየትኛውም ጊዜ በላይ ከፍተኛው ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ስደተኞችን በተመለከተ ሃሪስ ጠንከር ያለ አስተያየት ሲሰጡ እየተሰሙ ነው።
በአንድ መድረክ ላይም ስደተኞች “እንዳትመጡ” ሲሉ አሳስበዋል።
“እንዳትመጡ። እንዳትመጡ። የደንበር ደኅንነታችንን ለማረጋገጥ ሕጎችን ተግባራዊ እናደርጋለን። ወደ ድንበራችን ብትመጡ ወደመጣችሁበት ትመለሳለችሁ” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቻይና
ልክ እንደ ትራምፕ ሁሉ፤ ካማላ ሃሪስ ቻይናን አጥብቀው ሲተቹ ይሰማሉ።
ትራምፕ የማይስማማቸው የቻይና ጉዳይ የንግድ ግንኙነት ነው። ትራምፕ ቻይና ላይ ታሪፍ በመጨመር ይታወቃሉ። የካማላ ትኩረት ግን ከንግድ ይልቅ በቀጠናው ያለ ጂኦ-ፖለቲካካዊ ጉዳይ ነው።
ሃሪስ ቻይና በደቡብ ቻይና ባሕር ላይ የምታነሳውን የባለቤትነት መብት ጥያቄ ውድቅ ያደርጋሉ።
በምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው ዘመን እንዲሁ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ደቡብ ኮሪያ አቅንተው ነበር። ቻይና በሰሜን ኮሪያ ያላትን ተጽእኖ ለመግታት ጥረቶችን አድርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በካማል የምክትል ፕሬዝዳንትነት ዘመን አሜሪካ እና ቻይና በታይዋን ጉዳይ ሲወዛገቡ ቆይተዋል።
ቻይና ታይዋንን እንደ አንድ ግዛቷ የምትመለከታት ሲሆን፣ አስፈላጊ ከሆነ በኃይል መልሳ ልትጠቀልላት እንደምትችል በተደጋጋሚ ትገልጻለች።
ራሷን የምታስተዳድረው ታይዋን በበኩሏ ይህን አትቀበለውም። አሜሪካም እንዲሁ ታይናዋ ከቻይና የሚደርስባትን ጫና መቋቋም እንዲቻላት ወታደራዊ ድጋፍ ጭምር ስታደርግ ቆይታለች።












