የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ ከእስራኤል ጥቃት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ታዩ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የኢራን እና እስራኤል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ መታየታቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያው ባሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል ቅዳሜ ዕለት አሹራ ከተባለው ክብረ በዓል በፊት በመስጊድ ለምዕመናን ሰላምታ ሲያቀርቡ ታይተዋል።
አያቶላህ ኻሜኒ ሰኔ 6/2017 ዓ.ም. የኢራን ከፍተኛ የወታደራዊ አዛዦች እና የኒውክሌር ተመራማሪዎች መገደላቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰው የአገራቱ ግጭት ወቅት ለመጨረሻ ጊዜ ታይተዋል።
እስራኤል በኒውክሌር እና ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ኢራን አፀፋዊ የአየር ጥቃት ፈፅማለች።
ከእስራኤል ጋር በተደረገው የ12ቱ ቀናት ጦርነት ኻሜኒ በሦስት የተቀረፁ መልዕክቶች በቴሌቪዥን መስኮት የቀረቡ ሲሆን፤ተደብቀዋል የሚል አሉባልታዎች ተከትለዋቸዋል።
ቅዳሜ ዕለት የኢራን መገናኛ ብዙኃን ሽፋን ያተኮረው በኻሜኒ ዳግም መታየት እና በቴሌቭዥን መስኮት ሲታዩ የተሰበሰቡ ሰዎች ደስታቸውን ሲገልፁ በማሳየት ላይ ነበር።
ኻሜኒ ከፍተኛ የኃይማኖት አባት የሆኑት መሐመድ ካሪሚ የኢራንን ብሔራዊ መዝሙር እንዲዘምሩ ሲጋብዙ ታይተዋል።
ይህ የአርበኝነት መዝሙር በቅርቡ በተቀሰቀሰው የእስራኤል ግጭት ተወዳጅነትን አትርፏል።
ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያው ቀረፃው በቴህራን የእስላሚክ ሪፐብሊክ መስራች በሆኑት ኢማም ኾሜኒ መስጊድ እንደተካሄደ ገልጿል።
ጣቢያው ኢራናዊያን በታላቁ መሪ አደባባይ መታየት የተሰማቸውን ስሜት የሚገልፅ ተንቀሳቃሽ ምስል እንዲያጋሩት ጋብዟል።
ኻሜኒ ዳግም በአደባባይ የታዩት በአብዛኛው ሺዓ ሙስሊም በሆነው አገር በሀዘን በሚታሰበው የሙህራም ወር እና ታላቁ መሪ አዘውትረው በሚታደሙበት በዓል ወቅት ነው።
አሹራ የተባለው ክብረ በዓል በሙህራም 10ኛ ቀን የነብዩ መሐመድ የልጅ ልጅ ሁሴን ህልፈት የሚታሰብበት በዓል ነው።
ከሁለት ሳምንት በፊት ተቀርፆ በተላለፈ መልዕክት ኻሜኒ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥሪ ቢያቀርቡም ኢራን ለእስራኤል መቼም ቢሆን እጅ አትሰጥም ብለዋል።
ይህን ያሉት አሜሪካ በኢራንን የሚሳኤል ተቋማትን በመደብደብ ጦርነቱን ከተቀላቀለች ከቀናት በኋላ ነው።
ዘመቻው 125 የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖችን ያሳተፈ እና ፎርዶ፣ ናታንዝ እና እስፋሃን የተባሉ ሦስት የኒውክሌር ተቋማትን ዒላማ ያደረገ ነበር።
በ12 ቀናት ጦርነት ከ900 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢራን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።















