አሜሪካ ከኢራን ጋር ለንግግር ለመቀመጥ ተጨማሪ ጥቃት የመፈጸም ሀሳብን መተው እንዳለባት የአገሪቱ ሚኒስትር ተናገሩ

አሜሪካ ከኢራን ጋር የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ውይይት እንዲቀጥል የምትፈልግ ከሆነ በቴህራን ላይ ተጨማሪ ጥቃቶችን የመፈጸምን ሃሳብ መተው እንዳለባት የኢራን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ለቢቢሲ ተናገሩ።
ምክትል ሚኒስትሩ ማጂድ ታክት ራቫንቺ፤ የትራምፕ አስተዳደር ወደ ድርድር መመለስ እንደሚፈልግ በአደራዳሪዎች በኩል ለኢራን መግለጹን አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ "እጅግ ወሳኝ ጥያቄ" ሲሉ በጠቀሱት፤ ንግግር በሚካሄድበት ወቅት የሚፈጸሙ ተጨማሪ ጥቃቶችን በተመለከተ "አቋማቸውን ግልጽ አላደረጉም" ብለዋል።
ሰኔ 6/2017 ዓ.ም. የተጀመረው የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ከሁለት ቀናት በኋላ በሙስካት ሊካሄድ የታቀደውን ስድስተኛ ዙር በዋናነት ቀጥተኛ ያልሆኑ ንግግሮችን እንዳያካሄዱ አድርጓል።
አሜሪካ በሦስት የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የቦምብ ጥቃት በመፈጸም በእስራኤል እና በኢራን ጦርነት ውስጥ በቀጥታ ተሳትፋለች።
ኢራን ለሰላማዊ ዓላማዎች ስትል የምትገልጸውን ዩራኒየም የማበልጸግ እቅዷን በተመለከተ "በአቋሟ እንደምትጸና" የሚናገሩት ታክት ራቫንቺ፤ ቴህራን በድብቅ የኒውክሌር ቦምብ ለማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰች ነው የሚሉ ክሶችን ውድቅ አድርገዋል።
ኢራን ለምታካሂደው ምርምር መርሃ ግብር "የኑክሌር ቁሳቁስ እንዳታገኝ ተከልክላለች" ስለዚህ "በራሳችን [አቅም ላይ] መተማመን ነበረብን" ብለዋል።
"ደረጃው ውይይት ሊደረግበት ይችላል፣ አቅሙም ውይይት ሊደረግበት ይችላል፤ ነገር ግን ማበልፀግ የለባችሁም፣ የማበልፀግ ደረጃችሁ ዜሮ መሆን አለበት እና በዚህ ካልተስማማችሁ እናፈነዳችኋለን ብሎ መናገር፤ ይህ የጫካ ሕግ ነው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
እስራኤል ሰኔ 6 ላይ ጥቃቷን የጀመረችው የኢራንን የኒውክሌር እና ወታደራዊ ጣቢያዎችን ዒላማ በማድረግ እንዲሁም የሀገሪቱን ወታደራዊ አዛዦች እና ሳይንቲስቶችን በመግደል ሲሆን ለዚህ ድርጊቷ ያቀረበችው ምክንያት ቴህራን የኒውክሌር መሳሪያ ለመገንባት ተቃርባለች የሚል ነበር።
ኢራን ለዚህ ምላሽ ሰጠችው እስራኤል ላይ የሚሳኤል ጥቃት በመፈጸም ነበር። 12 ቀናት በቆየው በዚህ ግጭት አሜሪካ ፎርዶ፣ ናታንዝ እና ኢስፋሃን በተባሉት ሶስት የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ቦምብ ጥላለች።
የአሜሪካ ጥቃቶች በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሱ ግልጽ አይደለም። ታክት ራቫንቺም ይህንን በተመለከተ ትክክለኛውን ግምገማ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ በበኩላቸው ድብደባው ከፍተኛ ጉዳት ቢያስከትልም የደረሰው ጉዳይ "ሙሉ በሙሉ [ውድመት] አይደለም" ብለዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአንጻሩ የኢራን የኒውክሌር ተቋማት "ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
ግሮሲ፤ ኢራን "በወራት ውስጥ" እንደገና ዩራኒየምን ማበልፀግ የመጀመር አቅም እንዳላትም ገልጸዋል። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ለዚህ በሰጡት ምላሽ፤ ጉዳዩ እንደዛ መሆኑን እንደማያውቁ ጠቅሰዋል።
ኢራን ከዓለም አቀፉ የኒውክሌር ኃይል ኤጀንሲ ጋር ያላት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ መጥቷል። ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የኢራን ፓርላማ፤ ኤጀንሲው ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር ወግኗል በሚል ከተቋሙ ጋር የሚደረገውን ትብብር ለማቋረጥ እንቅስቃሴ አድርጓል።
ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ዩራኒየምን ማበልፀግ እንደምትችል መረጃዎች ካረጋገጡ በድጋሚ ኢራንን በቦምብ ማጥቃት "ሙሉ በሙሉ" እንደሚያስቡት ተናግረዋል።
ትራምፕ በዚህ ሳምንት ከኢራን ጋር ውይይት ሊካሄድ እንደሚችል ቢጠቁሙም፤ ታክት ራቫንቺ ግን ንግግር ሊደረግ የሚችልበትን ቀን በተመለከተ እንዳልተስማሙ እንዲሁም በአጀንዳው ምን ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር እንደማያውቁ ገልጸዋል።
የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ "በአሁኑ ወቅት፤ በውይይት ላይ እየተሳተፍን እያለ የጥቃት ድርጊትን በድጋሚ ልናይ እንችላለን ወይ ለሚለው ጥያቄ መልስ እየፈለግን ነው" ብለዋል።
አሜሪካ "በዚህ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ላይ በጣም ግልጽ መሆን አለባት" እንዲሁም "ለእንዲህ ዓይነቱ ውይይት አስፈላጊ የሆነውን መተማመን ለማምጣት ምን ሊያቀርቡልን እንደሚችሉ" መግለጽ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢራን፤ ከተጣለባት ማዕቀብ እፎይታ ለማግኘት እና በአገሪቱ ኢንቨስትመንት እንዲኖር ለማድረግ ሲባል የኒውክሌር ፕሮግራሟ የስምምነት አካል እንዲሆን የመፍቀድን ጉዳይ በድጋሚ ታጤነው እንደሆነ የተጠየቁት ታክት ራቫንቺ፤ "ለምን በእንዲህ ዓይነቱን ሃሳብ እንስማማለን?" ሲሉ መልሰው ጠይቀዋል።
ዩራኒየምን እስከ 60 በመቶ ማበልጸግን ጨምሮ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም "ለሰላማዊ ዓላማ" የሚከናወን እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
እ.አ.አ በ2015 ከዓለም ኃይሎች ጋር በተፈጸመው የኒውክሌር ስምምነት መሠረት ኢራን ዩራኒየምን ለንግድ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች ከሚያስፈልገው ከ3.67 በመቶ የንጹህነት ደረጃ በላይ ማበልፀግ አልተፈቀደላትም። በፎርዶ የኒውክሌር ተቋሟም ለ15 ዓመታት ማንኛውንም ማበልፀግ እንዳታከናውን ገደብ ተጥሎባታል።
ይሁን እንጂ ትራምፕ በ2018 በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ወቅት፤ ኢራን የኒውክሌር ቦንብ እንዳትገነባ ያለው አስተዋጾ እምብዛም ነው በማለት አገራቸውን ከስምምነቱ ያወጡ ሲሆን አሜሪካ ጥላቸው የነበሩ ማዕቀቦችን ወደ ነበሩበት መልሰዋል።
ኢራን ለዚህ ምላሽ የሰጠችው በተለይም ከማበልፀግ ጋር የተያያዙ ገደቦች ላይ የምትፈጽመው ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ነው።
በ2021 በፎርዶ የኒውክሌር ተቋም ማበልፀግን መልሳ የጀመረች ሲሆን ዘጠኝ የኑክሌር ቦምቦችን ለማምረት የሚያስችል የ60 በመቶ የበለጸገ ዩራኒየምም አከማችታለች።
የአውሮፓ እና የምዕራባውያን መሪዎች በኢራን ላይ እምነት እንደሌላቸው የተጠየቁት ታክት ራቫንቺ፤ አንዳንድ የአውሮፓ መሪዎች ለአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃቶችን "ረብ የለሽ" ድጋፍ አድርገዋል ሲሉ ከስሰዋል።
በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ ትችት የሚሰነዝሩ አካላት "እኛ የተስተናገድንበትንም መንገድ መተቸት አለባቸው" እንዲሁም አሜሪካ እና እስራኤልን ሊተቹ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም፤ "አሜሪካን ለመተቸት ድፍረት ከሌላቸው ዝም ማለት እንጂ ለጥቃቱ ምክንያት ለመስጠት መሞከር የለባቸውም" ብለዋል።
አሜሪካ የአገሪቱን ጠቅላይ መሪ አያቶላሕ አሊ ኻሜኒን ዒላማ በማድረግ "ኢራን ውስጥ የስርዓት ለውጥ ማድረግ እንደማትፈልግ" በአደራዳሪዎች አማካኝነት ለቴህራን እንደገለጸች አስረድተዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የኢራናውያንን ሃይማኖታዊውን የኻሚኔ አገዛዝን ለማስወገድ "ለነፃነታቸው እንዲነሱ" ጥሪ አቅርበው ነበር። ነገር ግን ባለፈው ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ትራምፕ ተመሳሳይ ነገር እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።
ታክት ራቫንቺ ይህ እንደማይፈጠር እና ሃሳቡም "ከንቱ ጥረት" መሆኑን አጥብቀው ተናግረዋል። ምንም እንኳን አንዳንድ ኢራናውያን "በመንግስት የተወሰኑ እርምጃዎች ላይ ትችት ሊኖራቸው ቢችልም የውጭ ወራሪነት ሲመጣ ግን እሱን ለመቋቋም አንድ ይሆናሉ" ብለዋል።
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከእስራኤል ጋር የተደረገው የተኩስ አቁም ዘላቂ መሆን አለመሆኑ "በደንብ ግልጽ አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል። ይሁን እንጂ "በእኛ ላይ ወታደራዊ ጥቃት እስካልተፈፀመ ድረስ" ኢራን ተኩስ አቁሙን ማክበሯን ትቀጥላለች በማለት ተናግረዋል።
በፋርስ ባህረ ሰላጤ የሚገኙ የኢራን አጋር አረብ ሀገራት "ለድርድር አስፈላጊውን ከባቢ ለማዘጋጀት የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው" እንደሆነ ገልጸዋል።
አክለውም "ጦርነት አንፈልግም። በውይይትና በዲፕሎማሲ መሳተፍ እንፈልጋለን፤ ነገር ግን ዳግመኛ እንዳንደነግጥ መዘጋጀት፣ መጠንቀቅ አለብን" ብለዋል።















