ኢራን "በወራት ውስጥ" ቦምብ ለመስራት የሚያስችል ዩራኒየም ማበልፀግ ትችላለች -የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ኃላፊ

ራፋኤል ግሮሲ

የፎቶው ባለመብት, AP

የምስሉ መግለጫ, ራፋኤል ግሮሲ ኢራን ከኤጀንሲው ጋር ያላትን ግንኙነት ብታቋርጥም አሁንም ድርድሩ ሊካሄድ እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል

ኢራን ቦምብ ለመስራት የሚያስችል ዩራኒየምን እንደገና "በወራት ጊዜ ውስጥ" ማበልፀግ ለመጀመር የሚያስችል አቅም እንዳላት፣የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ኃላፊ ተናገሩ።

የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮስሲ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ አሜሪካ በሦስት የኢራን የሚሳዔል ተቋማት ላይ ያደረሰችው ድብደባ ከባድ ቢሆንም "አጠቃላይ" ጉዳት አለመድረሱን ተናግረዋል።

ይህ የኃላፊው ሃሳብ ዶናልድ ትራምፕ የኢራን የኒውክሌር ተቋማት "ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል" ሲሉ ከተናገሩት ጋር ይቃረናል።

"እውነቱን ለመናገር አንድ ሰው ሁሉም ነገር እንወደመ እና ምንም የቀረ የለም ብሎ መናገር አይችልም" ሲሉ ግሮሲ ቅዳሜ ዕለት ተናግረዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ13 ቀን እስራኤል ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመስራት ተቃርባ ነበር በማለት በኢራን የኒውክሌር እና ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት አድርሳለች።

በኋላ ላይም አሜሪካ ጥቃቱን በመቀላቀል በሦስቱ የኢራን የኒውክሌር ተቋማት፡ ፎርዶ፣ ናታንዝ እና እስፋሃን ላይ የከባድ ቦምብ ድብደባ አካሂዳለች

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በኒውክሌር ተቋማቱ ላይ የደረሰው ትክክለኛ የጉዳቱ መጠን ግልጽ አይደለም።

ቅዳሜ ዕለት ግሮሲ የቢቢሲ በአሜሪካ የሚዲያ አጋር ለሆነው ለሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት ቴህራን "በወራት ጊዜ ውስጥ... ጥቂት ሴንትሪፉጆችን (ማብላያዎችን) በማሽከርከር የበለፀገ ዩራኒየም ያመርታሉ" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አክለውም ኢራን አሁንም "የኢንዱስትሪ እና የቴክኖሎጂ አቅሞችን ይዘዋል... ስለዚህ ከፈለጉ ይህንን እንደገና መጀመር ይችላሉ" ብለዋል ።

የተባበሩት መንግሥታት የኢራን የኒውክሌር አቅም አሁንም ሊቀጥል እንደሚችል ሲጠቁም የመጀመሪያው ተቋም አይደለም።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የፔንታጎን የደህንነት ተቋም ግምገማ የአሜሪካ ጥቃቶች የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር በወራት ብቻ ወደ ኋላ እንዲመለሱ አድርጓልሲል ተናግሯል።

ትራምፕ የኢራን የኒውክሌር ተቀወማት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ሲሉ በቁጣ ምላሽ የሰጡ ሲሆን የመገናኛ ብዙሃንን "በታሪክ ውስጥ ስኬታማ ከሆኑ ወታደራዊ ጥቃቶች አንዱን ለማሳነስ ሙከራ አድርገዋል" ሲሉ ከስሰዋል።

ለጊዜው ኢራን እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምተዋል።

ትራምፕ ኢራን ዩራኒየሟን እንደገና እንደምታበለጽግ የሚያሳይ መረጃ ካገኙ ዳግም "ያለማቅማማት" ድብደባ ለመፈፀም እንደማያወላውሉ ተናግረዋል።

ኢራን በበኩሏ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰበት እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መልዕክቶችን አስተላልፋለች።

የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ ባለፈው ሐሙስ ዐዕለት ባደረጉት ንግግር ጥቃቱ ምንም ፋይዳ የለውም ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አባስ አራግቺ ግን "ከመጠን በላይ እና ከባድ" ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ኢራን ከመንግሥታቱ ድርጅት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ጋር ያላትን የሻከረ ግንኙነት ረቡዕ እለት ፓርላማው ከአቶሚክ ተቆጣጣሪው ጋር ያለውን ትብብር ለማቆም ሲወስን፣ ኤጀንሲው ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር ወግኗል ሲል ወንጅሎታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ወር ቴህራን ከ 20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባችውን ግዴታ ጥሳለች ማለቱን ተከትሎ ሁለቱ አገራት ኢራንን አጥቅተዋል።

ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሰላማዊ ጥቅም ብቻ እንደሚውል በተደጋጋሚ ትናገራለች።

ኢራናዊው ከመንግሥታቱ ድርጅት ጋር ለመስራት ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ ግሮሲ አሁንም ከቴህራን ጋር መደራደር እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

"ከኢራን ጋር ቁጭ ብዬ ይህን ጉዳይ ማየት አለብኝ። ምክንያቱም በስተመጨረሻ ላይ ይህ ሁሉ ነገር ከወታደራዊ ጥቃት በኋላ ዘላቂ መፍትሄ ሊኖረው ይገባል። ያ ደግሞ ያለ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ሊሆን አይችልም" ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ከዓለም ኃያላን አገራት ጋር በተደረገው የኒውክሌር ስምምነት ኢራን ከ 3.67 በመቶ በላይ ዩራኒየም እንድታበለጽግ አልተፈቀደላትም።

በዚህን ያህል መጠን የበለፀገ ዩራኒየም ለኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች ነዳጅ ለማቅረብ የሚያስፈልገውን ደረጃ ያሟላ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ለ15 ዓመታት በፎርዶ የኒውክሌር ተቋም ምንም ዓይነት ዩራኒየም ማበልጸግ አልተፈቀደላትም ።

ሆኖም ትራምፕ በመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው ስምምነቱን ኢራንን ቦምብ ለመስራት ከሚወስዳት መንገድ ለማስቆም በጣም ጥቂት ነገር ብቻ ነው ያከናወነው በማለት ማዕቀብ ጥለዋል።

ኢራን በምላሹ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ዩራኒየም ከማበልጸግ ጋር የገባችውን ስምምነት ጥሳለች።

እአአ በ 2021 በፎርዶ ዩራኒየም ማበልፀግ የጀመረች ሲሆን፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ተቆጣጣሪ ዘጠኝ የኒውክሌር ቦምቦችን መስራት የሚያስችል 60 በመቶ የበለፀገ ዩራኒየም አከማችታለች ሲል ሪፖርት አድርጓል።