የኢራን የሳይበር ጦር በአሜሪካ እና በእስራኤል ላይ ምን እርምጃ ይወስዳል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዓለም ኢራን አሜሪካ ለፈፀመችው የቦምብ ጥቃቶች የምትወስደውን የበቀል እርምጃ ትቀጥላለች በሚል አሁንም እየጠበቀ ነው።
የሳይበሩ ዓለም ከዚህ ቀደም አደገና የመረጃ ምዝበራ እና ምንተፋ በመፈፀም ታሪክ ካላት አገር ሊደረጉ የሚችሉ የመረጃ ጠለፋዎችን በንቃት እየተከታተለ ነው።
የኢራን መህር የዜና አገልግሎት "በአሜሪካ መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ የሆነ የሳይበር ጥቃት" በመፈጸም ምላሽ ለመስጠት ንግግር እየተደረገ መሆኑን ዘግቧል።
ኢራን በአሜሪካ፣ በእስራኤል ወይም በአጋሮቻቸው ላይ የሳይበር ጥቃት ዘመቻ ብትጀምር ምን ማድረግ ትችላለች?
መደበኛ በሆነ ውጊያ ቢሆን የሚኖረውን ወታደራዊ ምላሽ የአገሪቱን ተዋጊ ጄቶች፣ ታንኮች ወይም የሚሳኤል ክምችቶችን በመቁጠር የኢራንን አቅም መገምገም ይቻላል።
በሳይበር ዓለም ግን የሳይበር ጥቃት እስካልተፈፀመ ድረስ አገሪቱ ምን ማድረግ እንደምትችል ማወቅ ከባድ ነው።
የኢራን የሳይበር መረጃ መንታፊዎች 'ዋይፐር' የሚባል የጥቃት ዓይነት በመፈጸም ይታወቃሉ።
መረጃን ጠራርጎ ማጥፋት
የመረጃ ቀበኞች ወደ ድርጅት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሰብረው በመግባት እና ቫይረሶችን በመልቀቅ ያገኙትን መረጃን ጠራርገው ያጠፋሉ።
ሁሉም ኢሜሎች፣ ሰነዶች፣ ምስሎች እና ቪዲዮዎች እልም ብለው ይጠፋሉ።
መረጃን ጠራርጎ ማጥፋት ዓላማው ግልፅ ውድመት ማድረስ ነው። መረጃን መስረቅ ወይም ይዞ ገንዘብ መጠየቅ ዓላማቸው አይደለም።
ኢራን እንዲህ ዓይነት በርካታ ጥቃቶችን በመሰንዘር ትወነጀላለች።
በጣም የምትታወቅበት እአአ በ2012 በሳዑዲ አረቢያው የነዳጅ ዘይት ኩባንያ፣ አራምኮ ላይ የፈጸመችው ነው።
ኢራን የለቀቀችው ሻሙን የተሰኘ ቫይረስ 30,000 ኮምፒውተሮችን አጥቅቶ ያገኘውን መረጃ ሁሉ ካጠፋ በኋላ ለሳምንታት ኩባንያውን ቀውስ ውስጥ ከትቶት ቆይቷል።
ከሁለት ዓመት በኋላ የእስራኤል ጠንካራ ደጋፊ የሆነው አሜሪካዊው ቢሊየነር ሼልደን አዴልሰን በላስ ቬጋስ በሚገኘው ማቋመሪያው ላይ በኢራን የቫይረስ ጥቃት ማጋጠሙን ተናግሮ ነበር።
በቢሊየነሩ ላይ የደረሰው የቫይረስ ጥቃት 40 ሚሊዮን ዶላር አስወጥቶታል።
ከኢራን የተሰደዱ ዜጎችን ያስጠለለችው አልባኒያም በተደጋጋሚ የኢራን መረጃ መንታፊዎች ጥቃት ደርሶባታል።
አደገኛ የኢንዱስትሪ ጥቃት
ከምንም በላይ የሚያስጨንቀው ኢራን በወሳኝ ብሔራዊ መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ለማድረስ ሞክራለች የሚለው ውንጀላ ነው።
በአሜሪካ እና እስራኤል እንዲሁም በሳዑዲ የውሃ ማጣሪያ እና ግድቦች በስርዓታቸው ላይ የኢራን መረጃ መንታፊዎችን አገኘን ብለዋል።
የአሜሪካ ሳይበር ሴኩሪቲ እና የመሠረተ ልማት ደኅንነት ኤጀንሲ የቀድሞ ኃላፊ ጄን ኢስተርሊ ባለፈው እሁድ ሊከስት ከሚችል የኢራን የሳይበር ጥቃት አሜሪካ እና አጋር ኃይሎች "መከላከያቸውን ከፍ" እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
"በቅርብ የእስራኤል ጥቃቶች [የኢራን] ሳይበር አቅም ጉዳት ደርሶበት እንደሆነ ግልፅ ባይሆንም ኢራን የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ አፀፋዊ እርምጃ የመውሰድ ታሪክ አላት። የውሃ ስርዓት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የኃይል መስመሮች፣ የመንግሥት አውታሮች እና ከዚህ በላይ አላት" ብለዋል።
በእንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች ኢራን ከሩሲያ፣ ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ ጋር የምዕራቡ የሳይበር ስጋት ተደርጋ ትታያላች።
እንደ ዓለም አቀፍ የስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ኢራን በዓለም ደረጃ ሦስተኛ የሳይበር ኃይል ያላት አገር ናት።
በ2021 የወጣው ይህ ግምገማ ጥቃት ለመፈፀም፣ ለስለላ እና ለመከላከያ ሳይበር መሳሪያዎችን ለማዋል ያላት አቅም ከሰሜን ኮሪያ እና ከጃፓን ጋር የሚመሳሰል ነው።
የቤልፍ ብሔራዊ የሳይበር ኃይል ደረጃ ተመራማሪዎች በ2022 ባወጡት ዓለም አቀፍ ደረጃ ኢራንን 10ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጠዋታል።
ኢራን በሳይበር ኃይል ከአሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ እስራኤል ወይንም ከዩናይትድ ኪንግደም ግን ወደ ኋላ ያለች ናት።
ከአንድ ሳምንት በፊት እስራኤል በኢራን ላይ ከጀመረችው ዘመቻ በኋላ የኢራን የሳይበር እንቅስቃሴ አነስተኛ ነው።
በአሜሪካ እና እስራኤል ኩባንያዎች የበላይነት የሚመራው የሳይበር ደኅንነት ኢንዱስትሪው ሊደርስ የሚችል የሳይበር ጥቃትን እያስጠነቀቀ ነው።
አዳኙ ወፍ?
ይሁን እንጂ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የታየው ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አለው ከሚባለው ቡድን ነው።
ስመ ገናና የሆነው ቡድን ለበርካታ ዓመታት በኢራን ላይ በጣም የተራቀቀ ጥቃት በመፈፀም ባለፈው ሳምንት የኢራን ባንክ እንዲስተጓጎል እና ከኢራን ግዙፍ የክሪፕቶ ከረንሲ ኩባንያ 90 ሚሊዮን ዶላር በመስረቅ ማውደሙ ተነግሯል።
በግርድፉ አዳኙ ወፍ ሚባለው ቡድኑ እ.አ.አ በ2022 የሰው ሕይወት አደጋ ላይ የጣለ የኢራንን የብረታ ብረት ስራ በመመንተፍ ግዙፍ ጉዳት አድርሷል።
ኢራን የሳይበር ኃይል ለመሆን ወደ ልማት የገባቸው እ.አ.አ በ2010 በእስራኤል እና አሜሪካ በደረሰባት የሳይበር ጥቃት የአገሪቱ ኒውክሌር ማበልፀጊያ ጣቢያ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ነው።
ከዚህን ጊዜ በኋላ ኢራን አቅሟን ያሳደገች ሲሆን፤ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነች በቅርቡ ልታሳይ ትችላለች።












