በጎርፍ ከ80 ሰዎች በላይ የሞቱባት ኬንያ የትምህርት ቤቶች መክፈቻ ዕለትን በሳምንት አዘገየች

የፎቶው ባለመብት, EPA
በጎርፍ ከ80 ሰዎች በላይ የሞቱባት ኬንያ የትምህርት ቤቶች መክፈቻ ዕለትን በሳምንት አዘገየች።
አውሎንፋስ በቀላቀለ ዝናብ ምክንያት በጎርፍ የተጥለቀለቀችው ኬንያ ትምህርት ቤቶችን መክፈት ለተማሪዎቹ እና ሰራተኞቹ ስጋት መሆኑን ገልጻለች።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመላው አገሪቷ ያሉ ትምህርት ቤቶች በጎርፍ ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ኤዚኪየን ማሾጉ እሁድ እለት ባወጡት መግለጫ አስፍረዋል።
“በከፍተኛ ሁኔታ እየጣለ ያለው ዝናብ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት እጅግ የከፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የጎርፍ አደጋን የመከላከል እርምጃ ከመውሰዱ በፊት የተማሪዎችን እና የሰራተኞችን ህይወት አደጋ ላይ መጣል የማይታሰብ ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ አክለዋል።
በኬንያ የሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ሚያዝያ 21/ 2016 ዓ.ም መከፈት ቢኖርባቸውም በጎርፍ ምክንያት የሚከፈቱበት ጊዜ ወደ ሚያዝያ 28 ተራዝሟል።
አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በጎርፍ ምክንያት ተፈናቅለው የሚገኙ ነዋሪዎች መጠለያ ሆነዋል።
ቅዳሜ ዕለት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች 13 አስከሬኖች መገኘታቸውን ተከትሎ በጎርፍ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 83 አድርሶታል። በቀጣዮቹ ቀናትም የከፋ ዝናብ እንደሚጥል ከመጠበቁ ጋር ተያይዞ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሏል።
ከሞቱት በተጨማሪ በጎርፍ አደጋ ከ130 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የሃገሪቱ ባለስልጣናት የገለጹ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ደብዛቸው ጠፍቷል ተብሏል።
ኬንያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ አገራት መነሻው ከፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በሆነው እና በአካባቢ በሚፈጠር የውኃ ሙቀት መጨመር በሚከሰተው ኤልኒኖ የአየር ክስተት ምክንያት በከፋ ዝናብ ተመትተዋል።
በዚህም ምክንያት ኬንያን ጨምሮ ጎረቤቶቿ ብሩንዲ እና ታንዛንያ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል።
በብሩንዲ ከ100 ሺህ ሰዎች በላይ ሲፈናቀሉ፣ በታንዛንያ ደግሞ ቢያንስ 150 ሰዎች ሞተዋል።












