አሜሪካ የራፋህን ጥቃት እንድታስቆም የፍልስጤሙ መሪ ተማጸኑ

ከግማሽ በላይ የሚሆነው የጋዛ ነዋሪ ወደ ራፋህ ተፈናቅሎ ሸሽቷል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ እስራኤል ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በተጠለሉባት ደቡባዊ የጋዛ ከተማ ራፋህ ላይ ጥቃት ከማድረስ የምታስቆማት ብቸኛዋ አገር አሜሪካ ናት ብለዋል።

ከፊል ዌስት ባንክን የሚያስተዳድሩት አባስ ማንኛውም የእስራኤል ጥቃት ፍልስጤማውያን ከጋዛ እንዲሸሹ ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።

እስራኤል በራፋህ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ደጋግማ እየዛተች ትገኛለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እሑድ ዕለት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት “በራፋህ ላይ ያላቸውን ግልፅ አቋም” በድጋሚ አስታውቀዋል።

ሰላማዊ ዜጎችን ከጉዳት ለማዳን የሚያስችል አስተማማኝ ዕቅድ ካላየች በስተቀር አሜሪካ በራፋህ የሚካሄድን መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ መደገፍ እንደማትችል ደጋግማ ተናግራለች።

በሳዑዲ ርዕሰ መዲና ሪያድ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ጉባዔ (ደብሊውኢኤፍ) ላይ ንግግር ያደረጉት አባስ አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ አሳስበዋል ።

"እስራኤል ይህን ወንጀል እንዳትፈጽም ማድረግ የምትችለው አሜሪካ ብቻ ስለሆነች እስራኤል የራፋህ ዘመቻዋን እንድታቆም እንድትጠይቅ አሜሪካን እንማጸናለን። ራፋህ ላይ የሚደረግ "ትንሽ የሚባል ጥቃት" ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ለመሸሽ እንደሚያስገድድ ተናግረዋል።

"በፍልስጤም ህዝብ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ጥፋትም ያኔ ይከሰታል።" ብለዋል።

ከግማሽ በላይ የሚሆነው የጋዛ ህዝብ በራፋ የሚገኝ ሲሆን በከተማዋ ያለው ሁኔታም የከፋ የሚባል ነው። የተፈናቀሉ ሰዎች የምግብ፣ የውሃ እና የመድሃኒት እጥረት እንዳለባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዋይት ሃውስ በራፋህ የሚካሄደውን ዘመቻ በተመለከተ ባይደን ለኔታንያሁ የሰጡትን አስተያየት በተመለከተ በዝርዝር አልገለጸም። የብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ለኤቢሲ እንደተናገሩት እስራኤል ወደ አካባቢው ከመግባቷ በፊት የአሜሪካን ስጋቶች እና ሃሳቦችን ለማዳመጥ ተስማምታለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ሪያድ አቅንተው ከአባስ ጋር ሊነጋገሩ መሆኑም ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ ተስፋ እየፈነጠቀ የመጣው በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚደረገው ቀጥተኛ ያልሆነ የተኩስ አቁም ድርድር እና በጋዛ የቀሩትን ታጋቾች የማስለቀቅ ሂደት በእስራኤል ጥምር መንግሥት ውስጥ ያለውን መከፋፈል ይበልጥ እያጋለጠው ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጦር ካቢኔ አባል እና የተቃዋሚ ፓርቲ አባሉ ቤኒ ጋንትዝ እሑድ ዕለት እንደተናገሩት መንግስት ታጋቾቹን ለመመለስ ምክንያታዊ የሆነ ስምምነት እስካልተቀበለ ድረስ “በድርድሩ የመቀጠል መብት አይኖረውም” ብለዋል።

"ከሐማስ ጋር በሚደረገው የረዥም ጊዜ ትግል ውስጥ ራፋህ መግባት አስፈላጊ ነው። ታጋቾችን ማስመለስ አስቸኳይ እና እጅግ ወሳኝ ነው" ሲሉ ጋንትዝ ኤክስ ላይ አስፍረዋል።

የቀኝ አክራሪው የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች በበኩላቸው መንግስት በራፋህ ሊካሄድ የታቀደውን ጥቃት እንዲሰረዝ ከፈቀደ አስተዳደሩ መልቀቅ አለበት ብለዋል።

ባለስልጣናቱ አስተያየታቸውን የሰጡት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገሪቱ ታጋቾችን ለማስመለስ ከተስማማች ወረራውን ልታቆም ትችላለች ካሉ በኋላ ነው።

የእስራኤል ጦር አዛዥ ሄርዚ ሃሌቪ በበኩላቸው ጦርነቱን ለመቀጠል ዕቅዶች መጽደቃቸውን ተናግረዋል። ይህም የራፋህን ዘመቻ እንደሚያጠቃልል የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

በግብጽ እና በኳታር ሸምጋይነት ሲካሄድ የቆየው ድርድር በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ባለው አለመግባባት ቢቆምም ሐማስ እሑድ እንዳስታወቀው አዲስ ለቀረበው ሃሳብ ምላሽ ለመስጠት ተወካዮቹን ወደ ካይሮ እንደሚልክ ገልጿል።

የአሜሪካ ሚዲያ ስማቸው ያልተጠቀሱ የግብጽ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ለሐማስ የተሰጠው የድርድር መነሻ 20 ታጋቾችን በመልቀቅ በረዥም ሳምንታት መረጋጋት ጦርነቱን የማስቆም ሃሳብ ነው።

ሐማስ ጦርነቱ በዘላቂነት እንዲቆም እና ሁሉም የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ እንዲወጡ ይፈልጋል። እስራኤል በበኩሏ ሐማስን ከጋዛ ማጥፋት እና ሁሉም ታጋቾች መፈታት አለባቸው ብላለች።

ግብጽ እና ሌሎች የአረብ አገራት ጦርነቱ የሚሸሹ ፍልስጤማውያን ስደተኞችን ከመሬታቸው ማፈናቀል በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው መናገራቸው ይታወሳል።

የሳተላይት ምስሎች በጋዛ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ፣ ከራፋህ በስተ ምዕራብ እና ከዃን ዮኒስ ከተማ ሰሜን አቅጣጫ እየተገነቡ ያሉ አዳዲስ ድንኳኖችን ያሳያሉ። ድንኳኖቹ ከራፋህ የተፈናቀሉ ሰዎችን ለማስተናገድ ነው ሲሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የአሁኑ ጦርነት የተጀመረው ሐማስ በጋዛ አቅራቢያ እስራኤል ላይ ጥቃት በማድረስ ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ገድሎ 250 የሚጠጉ ታጋቾችን ከወሰደ በኋላ ነው። በህዳር ወር በተደረገ አጭር የተኩስ አቁም ስምምነት የተወሰኑ ታጋቾች ከተለቀቁ በኋላ 133 የሚሆኑ ታጋቾች አሁንም በጋዛ ውስጥ እንዳሉ የሚታመን ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 30 ያህሉ ሞተዋል ተብሏል።

በዚህ ሳምንት የሐማስ ታጣቂ ክንፍ ባሰራጫቸው ሁለት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ባለፈው መስከረም ከታገቱ ሰዎች ሦስት መኖራቸውን አሳይቷል።

እስራኤል በሰነዘረችው ጥቃት አብዛኛዎቹ ህጻናት እና እናቶች የሆኑ 34 ሺህ 454 ሰዎችን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

እየተካሄደ ባለው ጦርነት የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት የጋዛ ከተማን ጨምሮ ሁሉንም ሰሜናዊ ጋዛን እና ዃን ዮኒስን ጨምሮ አብዛኛው ማዕከላዊ እና ደቡባዊ ጋዛ ተቆጣጥሯል።

ጦሩ ከሞላ ጎደል ከአካባቢዎቹ ለቆ ቢወጣም እስራኤል በገነባችው እና ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ጋዛን በሚለየው መንገድ ላይ የተወሰኑ ወታደሮች እንዲቆዩ ተደርጓል።