አሜሪካ፡ የጋዛን ጦርነት የተቃወሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ታሰሩ

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞው እየተስፋፋ ነው

የጋዛን ጦርነት በመቃወም በአሜሪካ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተነሳው ተቃውሞ አሁንም ቀጥሏል።

ባለፉት ቀናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ተቃውሞው ይበልጥ የተስፋፋው ከሳምንታት በፊት በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የተፈጠረውን ክስተት ተከትሎ ነው።

የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ድንኳን በቅጥር ግቢው ተክለው ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ ፖሊስ በርካታ ተማሪዎችን በኃይል ካሰረ በኋላ ተቃውሞው ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ሊስፋፋ ችሏል።

በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ እንዲህ ዓይነት ተቃውሞ ሲካሄድና ተቃውሞውን ተከትሎም ፖሊስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በቁጥጥር ሥር ሲያደርግ ከ50 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነበር።

በዩኒቨርስቲው ለመጨረሻ ጊዜ ተማሪዎች እንዲህ ዓይነት ሰፊ ተቃውሞ አሰምተው የሚያውቁት የቬትናምን ጦርነት በመቃወም ነበር።

በሳምንቱ መጨረሻ በበርካታ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞው በርትቶ የታየ ሲሆን ፖሊስም በርካታ ተማሪዎችን አስሯል።

ለእስር ከተዳረጉት መካከል የግሪን ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ጂል ስቴይን ይገኙበታል።

እሳቸው የታሰሩት በሴንት ሉዊስ ዩኒቨርስቲ ሚዙሪ ካምፓስ ነው።

ተማሪዎቹ የሚጠይቁት እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን መጠነ ሰፊ የንጹሐን ጥቃት እንድታቆምና ከእስራኤል ጋር ንግድ የሚሠሩ ኩባንያዎች ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ ነው።

ተቃውሞው ተፋፍሞ በቀጠለበት ሁኔታ አንዳንድ ተማሪዎች ጸረ-ሴማዊነት ጥቃት በሰልፈኞች ደርሶብናል ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።

ተቃውሞው በካሊፎርኒያ ፖሊቴክኒክ ስቴት ዩኒቨርስቲም ተዛምቷል። ይህን ተከትሎ ትምህርት በርቀት እንዲሰጥ ተወስኗል።

ብዙ የገጽ ለገጽ አውደ ጥናት መርሐ ግብሮች እንዲሁም የምረቃ ሥነ ሥርዓቶችን ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፈዋል።

ተቃውሞው ኬኔቲኬት ግዛት በሚገኘው በዝነኛው የዬል ዩኒቨርስቲውም ተነስቷል።

በቦስተን ከተማ፣ ኖርዝ ኢስተርን ዩኒቨርስቲ ቅዳሜ ከመቶ በላይ ተማሪዎች የታሰሩ ሲሆን የማሳቹሴት ግዛት ፖሊስ እስሩን የፈጸምኩት ተማሪዎች የቀለሱትን የተቃውሞ ድንኳን ለማፍረስ ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ነው ብሏል።

ኖርዝኢስተርን ዩኒቨርስቲ በኤክስ ገጽ ባስተላለፈው መልእክት “ተቃውሞው የኛ ተማሪዎች ባልሆነ የተደራጁ ኃይሎች ተጠልፏል” ካለ በኋላ ጸረ-ሴማዊ የጥላቻ ንግግሮች በተቃዋሚዎች መሰማታቸውን አውስቷል። እንዲህ አይነቱን ተግባርም አልታገስም ብሏል።

የሰልፉ መሪዎችን ግን ዩኒቨርስቲው የሰጠውን አስተያት “ቅጥፈት ነው” ሲል አጣጥሎታል።

የሳውዝ ካሮላይና ዩኒቨርሰቲ ተቃውሞ በሳምንቱ መጨረሻ በረድ ብሎ የታየ ሲሆን በአመዛኙ ሰላማዊ ነበር። ዩኒቨርስቲው ግን በርካታ ንብረቶችን የማውደም ተግባር ተስተውሏል ሲል ድርጊቱን አውግዟል።

በኢንዲያና ዩኒቨርሰቲ ደግሞ 23 ሰልፈኞች ታስረዋል።

የጂርጂያው ኢሞሪ ዩኒቨርስቲና የተቃውሞው እምብርት የሚባለው ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ቅዳሜ ዕለት የተወሰነ መረጋጋት ታይቶባቸዋል።

ተቃውሞው በዋናነት እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለውን አሰቃቂ ወታደራዊ ጥቃት የሚቃወም ነው። መንፈቅ ባለፈው በዚህ ጥቃት 34ሺህ ሰዎች ሲገደሉ ብዙዎቹ ሕጻናት ናቸው ብሏል በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር።

የእስራኤል ጥቃት የተከፈተው ሐማስ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ፣ 1200 እስራኤላዊያንና የውጭ ዜጎችን ከገደለና 253 የሚሆኑትን አግቶ ከወሰደ በኋላ ነበር።