ሊቨርፑል ከአርሰናል እና የሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ግምት

ሞ ሳላህ እና ጊዮኬሬስ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሑድ ይከናወናሉ።

ለዋንጫው ትልቅ ግምት የተሰጣቸው ሊቨርፑል እና አርሰናል እሑድ የሚያከናውኑት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።

የጨዋታዎቹን ውጤት የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን እንደሚከተለው ገምቷል።

ቅዳሜ

ቼልሲ ከ ፉልሃም

ቼልሲ በመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታ ከፓላስ ጋር ጥሩ ባይጫወትም በሁለተኛው ሳምንት ዌስትሃምን 5 ለ 1 አሸንፏል።

ዌስትሃምን በማሸነፉ የቡድኑ የራስ መተማመን እንደጨመረ እገምታለሁ።

በማርኮ ሲልቫ ስር የሚሠለጥነው ፉልሃም ለሰማያዊዎቹ አደጋ እንደሚደቅን እገምታለሁ።

ሆኖም ጨዋታውን ቼልሲ ያሸንፋል።

ግምት፡ 2 - 1

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ በርንሌይ

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ በርንሌይ

ይህንን ጨዋታ ለመገመት ከባድ ሲሆን የትኛውም ውጤት ቢመዘገብ አስገራሚ አይሆንም።

ብዙ ግቦች የሚቆጠሩበት ጨዋታ ባይሆንም ዩናይትድ ወደ ድል መመለስ ይኖርበታል።

ሩበን አሞሪም ከግሪምስቢ ሽንፈት በኋላ ጫናው የበረታባቸው ይመስለኛል።

በርንሌይ ጫናን መቋቋም የሚችል ቡድን መሆኑን አሳይቷል።

ግምት፡ 1 - 0

ሰንደርላንድ ከ ብሬንትፎርድ

ሰንደርላንድ ዌስት ሃምን በማሸነፍ ድንቅ ውጤት ሲያስመዘግብ ከበርንሌይ ጋር ጥሩ ተፎካክሯል።

ብሬንትፎርድ በበኩሉ ከ አስቶን ቪላ ጋር ሲጫወት አሳማኝ በሆነ መልኩ አሸንፏል።

ብሬንትፎርድ በሊጉ ልምድ ያለው ሲሆን፣ ያለፈው ሳምንት ድልም ለዚህ ጨዋታ ያነሳሳቸዋል።

ግምት፡ 0 - 1

ቶተንሃም ከ በርንመዝ

በርንመዝ ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደርጋል።

የቶማስ ፍራንክ ቶተንሃም ደግሞ ሚዛኑን የጠበቀ ቡድን ነው።

በሜዳው ቶተንሃም እንደሚያሽንፍ እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 -1

ዎልቭስ ከ ኤቨርተን

ይህ ለዎልቭስ ትልቅ ጨዋታ ነው። አሠልጣኙ ቪቶር ፔሬራም ውጤት ይጠብቃሉ።

አሠልጣኙ ባለፈው ዓመት ጥሩ ቢሠሩም፤ ዘንድሮ በበርንመዝ እና በማንቸስተር ሲቲ ተሸንፈዋል።

የኤቨርተን የአጥቂ መስመር ክፍተት አለበት። አዲስ ፈራሚው ቲዬርኖ ባሪ ይህን ሊቀርፍ ይችላል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።

ግምት፡ 1 -1

ሊድስ ዩናይትድ ከ ኒውካስል

ኒውካስል ከሊቨርፑል ጋር ጥሩ ተንቀሳቅሷል። ሳንድሮ ቶናሊ እና ጆይሊንተን በጉዳት መውጣታቸው ቡድኑን ያሳሳዋል።

ሊድስ በበኩሉ በአርሰናል 5 ለምንም ተሸንፏል። ሆኖም ቡድኑ በሜዳው ጠንካራ መሆኑን አሳይቷል።

ቶናሊ እና ጆይሊንተን የሚሰለፉ ከሆነ ኒውካስል ያሸንፋል።

አንቶኒ ጎርደን በቅጣት የሚጫወት ባለመሆኑ ጨዋታው በአቻ ውጤት እንደሚጠናቀቅ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 - 1

እሑድ

ብራይተን ከ ማንቸስተር ሲቲ

ብራይተን ከ ማንቸስተር ሲቲ

የግብ ጠባቂው ጀምስ ትራፎርድ ጉዳይ ያሳስበኛል። ከኤደርሰን ቀድሞ ዕድል ሊሰጠው አይገባም።

ብራይተን በሁለቱም ሳምንት ጨዋታዎች በፉልሃም እና በኤቨርተን ተሸንፏል።

ይህ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ ያለበትን ሁኔታ የሚገልጥ ይሆናል።

ግምት፡ 1 - 2

ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ዌስት ሃም

ፎረስት ከሜዳ ውጪ ብዙ ጉዳዮች ቢነሱበትም ሜዳ ውስጥ ግን ውጤታማ እየሆኑ ነው። ብሬንትፎርድን አሸንፈዋል፤ ከፓላስ ጋር አቻ ተለያይተዋል።

ዌስት ሃም መጥፎ ጅምር ከማሳየቱም ሌላ በሳምንቱ አጋማሽ ከሊጉ ዋንጫ ውጪ ሆኗል።

የዌስት ሃም ጉዳይ ያሳስበኛል። አሠልጣኝ ግርሃም ፖተር ጫና ውስጥ ናቸው።

ግምት፡ 2 - 0

ሊቨርፑል ከ አርሰናል

ሊቨርፑል ከ አርሰናል

አርን ስሎት እንዳሉት ሁሉ የሊቨርፑል የተከላካይ መስመር አሳሳቢ ስለመሆኑ እኔም እስማማለሁ።

እስካሁን አራት ግቦችን ከማስተናገዳቸውም በላይ ኢብራሂማ ኮናቴ በጥሩ አቋም ላይ አይገኝም።

የሊቨርፑል ደጋፊዎች የሚጽናኑት ውጤታማ በመሆናቸው ነው።

ቡድኑ በኒውካስል ተፈትኗል። ይህን አርሰናል የማይደግምመበት ምክንያት አይኖርም።

ግምት፡ 1 - 2

አስቶን ቪላ ከ ክሪስታል ፓላስ

የአስቶን ቪላ ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ባለፈው ሳምንት ከ ብሬንትፎርድ ጋር የነበረው አቋም ጥሩ የሚባል አልነበረም።

ቪላ ኳስን ከኋላ በመመሥረት መጨወትን ይመርጣል። ፓላስ ደግሞ የተለያዩ አጨዋወቶችን ይጠቀማል።

ፓላስ ያለ ኤዜም ጠንካራ ነው።

ግምት፡ 3 - 1