ኤርትራውያን እንደ አምባሳደር የሚያዩት አሌክሳንደር በኒውካስትል ክለብ ለምን እንዲቆይ ይፈልጋሉ?

የኒውካስትል አጥቂው አሌክሳንደር ኢሳቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኒውካስትል አጥቂው አሌክሳንደር ኢሳቅ

በዩናይትድ ኪንግደም የኒውካስትል የእግር ኳስ ክለብን ስኬት ካጎናጸፉት መካከል አንዱ በስዊድን ከኤርትራዊ ቤተሰብ የተወለደው አሌክሳንደር ኢሳቅ ነው።

አሌክሳንደር ኢሳቅ እውቅናው ከሜዳ ያለፈ ነው፤ በተለይም በኒውካስትል ባሉ ዲያስፖራ ኤርትራውያን ዘንድ እንደ አርዓያ የሚታይ ነው።

ከኤርትራውያን መካከል አንዱ በእግር ኳሱ መድረክ ትልቅ ስፍራ ላይ መገኘቱ ለበርካቶች የመነሳሳት ስሜት የፈጠረ እንዲሁም በርካቶችን ያኮራ ነው።

ወጣት ኤርትራውያን የእሱን ፈለግ ተከትለው በአካባቢያቸው በሚገኙ ፓርኮች እና የሥልጠና ሜዳዎች ላይ እግር ኳስ መሠልጠን ከጀመሩ ከራርመዋል።

"በአሁኑ ወቅት እግር ኳስን የምወደው በአሌክሳንደር ምክንያት ነው" ሲል አንድ የ13 ዓመት ኤርትራዊ የዘር ሐረግ ያለው ታዳጊ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግሯል።

"እዚህ [ኒውካስትል] ሲጫወት ማየቴ ያኮራኛል። እሱ እንደኔ [ኤርትራዊ የዘር ሐረግ ያለው] ነው" ብሏል።

የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ያዕቆብ አካሌ በተለይም አንደኛው ልጃቸው የኒውካስትሉን አጥቂ በአርዓያነት እንደሚመለከተው ያስረዳሉ።

በስዊድን ነዋሪ ከሆኑ ኤርትራዊ ወላጆች የተገኘው አሌክሳንደር "በኒውካስትል ላሉ ልጆቻችን ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሯል" ይላሉ አቶ ያዕቆብ።

"በአሁኑ ወቅት ተግቶ በመሥራት ሁሉንም ነገር ማሳካት ይቻላል ብለው ያምናሉ። ከእነሱ አንዱ እንደሆነ ነው የሚያዩት" ሲሉ አባት ያስረዳሉ።

ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2022 የኒውካስትል ክለብን ከተቀላቀለ በኋላ በ109 ጨዋታዎች 62 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው አሌክሳንደር ወደ ሌላ ክለብ ይዘዋወራል የሚለው ዜና ለኤርትራውያን ስጋት መሆኑ አልቀረም።

የ25 ዓመቱ እግር ኳስ ተጫዋች ያለፈው የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ከሆነው ሊቨርፑል ጥያቄ የቀረበለት ሲሆን፣ ከቡድኑም ተለይቶ ልምምድ እያደረገ ይገኛል።

የኒውካስትል ክለብ ሥራ አስኪያጅ ኤዲ ሃው "ሁሉም ነገር ገና በሂደት ላይ ነው" ቢሉም፤ ቢቢሲ ስፖርት ግን አሌክሳንደር ክለቡን ለመልቀቅ መወሰኑን ተረድቷል።

በኒውካስትል ሜዳ ላይ የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኒውካስትል ሜዳ ላይ የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ

ግንቦት ወር ላይ የኒውካስትል ክለብ ለቻምፒዮንስ ሊግ ሲያልፍ ኤርትራውያንን ጨምሮ የበርካታ የቡድኑ ደጋፊዎች ደስታ ከመጠን ያለፈ ነበር።

ሆኖም የአሌክሳንደር ዝውውር እየተሰማ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ ስመ ጥር በሆነው ቻምፒዮንስ ሊግ ተፎካካሪ መሆን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

ኒውካስትል የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ሊቨርፑልን ፍላጎት ለመግታት በሚል የአሌክሳንደርን የዝውውር ገንዘብ 201 ሚሊዮን ዶላር አድርሶታል።

ቀያዮቹ [ሊቨርፑል] ከጀርመኑ አይንትራክት ፍራንክፈርት ሁጎ ኤኪቲኬን ቢያስመጡም አሌክሳንደርን ወደ ቡድናቸው ለመቀላቀል አሁንም እንደቋመጡ ናቸው።

አሌክሳንደርን ለማዘዋወር 147.5 ሚሊዮን ዶላር ለኒውካስትል ቢያቀርቡም ውድቅ የተደረባቸው ሊቨርፑሎች፣ ዳርዊን ኑኔዝ የተባለውን ተጫዋቻቸውን ሸጠው የገንዘብ አቅማቸውን በአሁኑ ወቅት አጠናክረዋል።

ሊቨርፑል ተጫዋቹን የማስፈረም ፍላጎት መነሻ የሆነው ምናልባትም ባለፈው የውድድር ዓመት በካራባኦ ካፕ ፍጻሜ ከኒውካስትል ጋር በነበረው ጨዋታ አሌክሳንደር ክለቡን አሸናፊ ያደረገችውን ግብ ከማስቆጠሩ ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል።

አሌክሳንደር በዚህች ግብ ኒውካስትልን ከሰባ ዓመት በኋላ የመጀመሪያውን ዋንጫ እንዲያነሳ አስችሏል።

ሆኖም በሐምሌ አጋማሽ ላይ ኒውካስትል ከግጥሚያዎች በፊት በነበረው የእስያ ጉብኝት አሌክሳንደር ሳይሳተፍ ቀርቷል። ሌሎች አማራጮችን እያማተረ እንደሆነም ተጫዋቹ አስታውቋል።

ሆኖም በዩናይትድ ኪንግደም ሰሜናዊ ምሥራቅ ነዋሪ የሆኑት ኤርትራውያን ከተማቸውን ለቆ እንዲሄድ አይፈልጉም።

የኤርትራ አምባሳደር

በስዊድን መዲና ስቶክሆልም የተወለደው አሌክሳንደር ቀደም ሲል ስለ ኤርትራ የዘር ሐረጉ ሲያወራ በኩራት ነው።

"ስዊድን ውስጥ ባድግም ትልቅ የኤርትራ ማኅበረሰሰብ አለ። ያደግኩትም በዚያ ዓይነት አካባቢና ባህል ነው" ሲል ከፕሪሚየር ሊግ ዝነኛው እና የኒውካስትል የቀድሞ ተጫዋች አለን ሺረር ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።

አሌክሳንደር በእግር ኳሱ ዓለም የኤርትራ የዘር ሐረግ ኖሮት ስመ ጥር መሆን የቻለ የመጀመሪያው ነው። ለዚያም ነው ዲያስፖራም ሆነ በአገራቸው ባሉ ኤርትራውያን ዘንድ እንደ አምባሳደር የሚታየው።

"እንደ አሌክሳንደር ያለ ታዋቂ ሰው እዚህ [ኒውካስትል] ሲመጣ ማየት በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው" ይላል በአሁኑ ወቅት በኒውካስትል ነዋሪ የሆነውና በኤርትራ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች እና የብሔራዊ ታዳጊዎች ቡድን የቀድሞ አሠልጣኝ የሆነው መሐሪ እስጢፋኖስ።

"የአካባቢው ነዋሪዎች ስለ ኤርትራ ብዙም እውቀት አልነበራቸውም፤ ነገር ግን አሌክሳንደር ወደ ኒውካስትል ከመጣ በኋላ ብዙዎች ኤርትራ የት እንደምትገኝ እንዲሁም ስለ ባህሏ ያውቃሉ" ብሏል።

እስጢፋኖስ እንደሚለው አሌክሳንደር በዲያስፖራ ያሉ ኤርትራውያን ታዳጊዎች ወደ እግር ኳሱ ዘርፍ እንዲቀላቀሉ አነሳስቷቸዋል፤ አንዳንዶቹም በዩናይትድ ኪንግደም እና በአውሮፓ ውሰጥ ያሉ አካዳሚዎች ገብተዋል።

መሐሪ እስጢፋኖስ
የምስሉ መግለጫ, በኤርትራ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች እና የብሔራዊ ታዳጊዎች ቡድን የቀድሞ አሠልጣኝ የሆነው መሐሪ እስጢፋኖስ

በኤርትራ የእግር ኳስ ማሽቆልቆሉ ጋር ተያይዞ ፊፋ የአገሪቱን ብሔራዊ ቡድን ከደረጃ ዝርዝሩ ባለፈው ዓመት አውጥቷታል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኤርትራውያን ተጫዋቾች ወደ ተለያዩ አገራት ለጨዋታ ሄደው ሳይመለሱ መቅረታቸው በተደጋጋሚ ዜና ሆኗል።

በታይኔሳይድ እና በአካባቢው የሚኖሩ ኤርትራውያን አሌክሳንደርን መደገፍ ኃላፊነታቸው እንደሆነ ነው የሚሰማቸው።

የኤርትራ ቀይ፣ አረንጓዴ እና ሰማያዊ ቀለማትን የያዘው ሰንደቅ ዓላማ ኒውካስትል በሚጫወትበት ጊዜ ደምቆ ከሚውለበለቡት መካከል አንዱ ነው።

"አሌክሳንደር የኤርትራ አምባሳደር ነው፤ ልክ እንደ ታዋቂዎቹ ብስክሌተኞች ቢንያም ግርማይ እና ዳንኤል ተክለሃይማኖት" ይላሉ አቶ ያዕቆብ።

አቶ ያዕቆብ እንደሚሉት "ሁላችንም በእሱ እንኮራለን። ጫማዎቹ ላይ የስዊድን እና የኤርትራ ሰንደቅ አላማዎች አሉ።"

በደጋፊዎች ዘንድ እየታወቀ ያለው የኤርትራ ባህል

አሌክሳንደር በኒውካስትል ቆይታው የክለቡን ስኬት ከማሻሻሉም በተጨማሪ የክለቡ ደጋፊዎች የተጫዋቹን የዘር ሐረግ እንዲጠይቁ አነሳስቷል።

ከኒውካስትል ክለብ ሴይንት ጄምስ ፓርክ ስታዲየም አቅራቢያ የሚገኝ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሬስቶራንት አንደኛው ባለቤት የሆነው በረከት ክፍሉ ቢዝነሳቸው ጥሩ እንደሆነ ይናገራል።

በተለይም አሌክሳንደር የካራባኦ ዋንጫ ድል ደስታው ላይ የሬስቶራንቱን ፎቶ አንስቶ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከለጠፈ በኋላ ደንበኞች መምጣት መጀመራቸውን በረከት ያስረዳል።

በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች እንጀራ ለመቅመስ ብቅ ይላሉ።

"አሌክሳንደር በርካታ ተጫዋቾችን ወደዚህ ሬስቶራንት እንደሚያመጣ ሰምቻለሁ" ሲል ኮሜድያን እና ባለ ፖድካስቱ አንት ያንግ ለቢቢሲ ትግርኛ አስረድቷል።

"ከዚህ ቀደም የኤርትራ ምግብ ቀምሼ አላውቅም፤ አሁን ግን ልሞክር ነው" ብሏል።

"በኢንስታግራም ላይ [ የእንጀራ] ልጥፎችን አይቻለሁ። የሚያስጎመጅ ይመስላል" ይላል።

ደጋፊዎቹ አሌክሳንደር ከኒውካስትል (ማግፒዎች) ጋር እንዲቆይ እና በክለቡም ዝነኛነቱንም እንዲያጠናክር ፍላጎታቸው ነው።

"አንድ ቀን እንደ ቦቢ ሮብሰን እና አለን ሺረር ያሉ [የቀድሞ የኒውካሰትል ተጫዋቾች] ሐውልታቸው እንደቆመው ሁሉ የእሱም [የአሌክሳንደር] አንድ ቀን ይቆምለታል" ሲል አንድ የአካባቢው ነዋሪ የሆነ ደጋፊው ተናግሯል።

በኒውካስትልም ሆነ በሌሎች ስፍራዎች ያሉ ደጋፊዎች የአጥቂው መጻኢ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል በጉጉት እየተከታተሉ ይገኛሉ።

ለበርካታ ክለቦች የአሌክሳንደር የዝውውር ዋጋ በጣም ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ለኤርትራውያን ታዳጊዎች አሌክሳንደር ያለው ዋጋ በገንዘብ የሚተመን አይደለም።