በቀን 7,000 እርምጃዎች መራመድ የጤና አደጋዎችን ይቀንሳል- ጥናት

በተራራማ የባሕር ዳርቻ አካባቢ ውሻቸውን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሁለት ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቀን 7 ሺህ እርምጃዎችን መራመድ የአዕምሮ ጉልበትን ለመጨመር እና ከተለያዩ በሽታዎች ለመከላከል በቂ ሊሆን እንደሚችል አንድ ጥናት አመለከተ።

ከ10 ሺህ እርምጃዎች በላይ መራመድ የበለጠ ጠቃሚ ሊሆን አንደሚችል ያመለከተው ጥህ ጥናት ይህም ብዙ ጊዜ እንደ ግብ ሊታይ እንደሚችል ገልጿል።

በላንሴት የሕዝብ ጤና ጆርናል ላይ የታተመው ምርምር ይህ ቁጥር ካንሰርን፣ የመርሳት በሽታን እና የልብ ሕመምን ጨምሮ ለከባድ የጤና ችግሮች የመጋለጥ ዕድልን ከመቀነስ ጋር እንደሚያያዝ አረጋግጧል።

ተመራማሪዎቹ ግኝቱ ብዙ ሰዎች ጤንነታቸውን ለማሻሻል የእግር ጉዟቸውን እንዲከታተሉ ሊያበረታታ ይችላል ብለዋል።

ጥናቱን በበላይነት የመሩት ዶ/ር ሜሎዲ ዲንግ "በቀን 10 ሺህ እርምጃዎችን መጓዝ አለብን የሚለው ግንዛቤ አለን" ብለዋል፤ "ግን በማስረጃ ላይ የተመሠረተ አልነበረም።"

10 ሺህ እርምጃዎች የሚለው ቁጥር በ1960ዎቹ በጃፓን ከነበረው የገበያ ዘመቻ ጀምሮ የነበረ ነው።

እአአ በ1964ቱ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ፔዶሜትር የተባለ ድርጅት ማንፖ ኬይ የሚባል እንቅስቃሴ ጀመረ፤ ይህም ሲተረጎም "የ10 ሺህ ደረጃ ሜትር" ማለት ነው።

ዶ/ር ዲንግ ይህ ቁጥር "ከዐውዱ ውጭ የተወሰደ" እና ብዙ የአካል ብቃት መከታተያዎች እና መተግበርያዎች እየመከሩት ያለ መደበኛ ያልሆነ መመሪያ ነው ብለዋል።

የላንሴት ጥናት በዓለም ዙሪያ ከ160 ሺህ በላይ ጎልማሶች ጤና እና እንቅስቃሴ በተመለከተ ከዚህ በፊት የተደረጉ ምርምሮችን እና መረጃዎችን ተንትኗል።

በቀን 2,000 እርምጃዎችን ከሚራመዱ ጋር ሲነጻጸር፣ 7 ሺህ እርምጃዎች የሚራመዱ ለሚከተሉት ሕመሞች የመጋለጥ ዕድላቸው መቀነሱ በጥናቱ ላይ ተመልክቷል።

  • የልብ ሕመም - 25 በመቶ ቀንሷል
  • ካንሰር - 6 በመቶ ቀንሷል
  • የመርሳት ችግር - 38 በመቶ ቀንሷል
  • እና የመንፈስ ጭንቀት - 22 በመቶ ቀንሷል

ይኹን እንጂ ተመራማሪዎቹ አንዳንድ ቁጥሮች ከጥቂት ጥናቶች የተወሰዱ በመሆናቸው ትክክለኛነታቸው ከሌሎቹ ያነሰ ሊሆን ይችላል።

በአጠቃላይ በተመራማሪዎቹ ግምገማ መሰረት በቀን ወደ 4 ሺህ የሚጠጉ እርምጃዎች የሚራመዱ 2 ሺህ ከሚራመዱ ጋር ሲነጻጸሩ የተሻለ ጤናማነት ተስተውሎባቸዋል።

ለአብዛኛዎቹ የጤና ሁኔታዎች፣ ከ7 ሺህ እርምጃዎች በላይ በየዕለቱ መራመድ ተጨማሪ ጥቅም ያለው ሲሆን፤ ተጨማሪ የእግር ጉዞ ማድረግ ደግሞ ለልብ ጤና ጥቅሞች አሉት።

እርምጃዎቹን በስልኩ በመታገዝ የሚቆትር ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አብዛኛዎቹ የአካል ብቃት መመሪያዎች ከእርምጃ ቆጠራዎች በላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በመስራት የሚጠፋው ጊዜ ላይ ያተኩራሉ።

ለምሳሌ የዓለም ጤና ድርጅት አዋቂዎች በየሳምንቱ ቢያንስ 150 ደቂቃ መጠነኛ የኤሮቢክ እንቅስቃሴ ወይም 75 ደቂቃ ከበድ ያለ የኤሮቢክ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው ብሏል።

ዶክተር ዲንግ ይህ ምክር አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ለመረዳት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ነገር ግን አሁን ያሉት መመሪያዎች ጠቃሚ ዓላማ እንዳላቸው አልሸሸጉም።

"የግድ የእግር ጉዞ ማድረግ የማይጠበቅባቸው የሚዋኙ፣ ብስክሌት የሚጋልቡ ወይም የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች አሉ" ብለዋል።

ነገር ግን ሰዎች ምን ያህል የእግር ጉዞ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያሳስበው ቁጥር ላይ የቀረበው ምክር "ሰዎች ቀኑን ሙሉ የአካል እንቅስቃሴዎቻቸውን ስለመጨመር ንዲያስቡ የሚገፋፋ" እንደ "ተጨማሪ" ሊካተት እንደሚችል ተናግረዋል።

በብሩኔል ዩኒቨርሲቲ የጤና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ዳንኤል ቤይሊ፣ ጥናቱ በቀን 10 ሺህ እርምጃዎች የማድረግ አስፈላጊነት ላይ የኖረውን "አፈ ታሪክ" ይፈትነዋል።

10 ሺህ እርምጃዎች የበለጠ ንቁ ለሆኑ ሰዎች ተስማሚ ግብ ቢሆንም ከ 5 ሺህ እስከ 7 ሺህ ማቀድ ለሌሎች "የበለጠ ተጨባጭ እና ሊደረስበት የሚችል ዒላማ" ሊሆን ይችላል ብለዋል።

በፖርትስማውዝ ዩኒቨርሲቲ የክሊኒካል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፊዚዮሎጂ ከፍተኛ መምህር የሆኑት ዶክተር አንድሪው ስኮት ትክክለኛው ቁጥር አስፈላጊ እንዳልሆነ ይስማማሉ።

እሱ "ብዙ መራመድ ሁልጊዜ የተሻለ ነው" ካሉ በኋላ፣ ሰዎች አንድን የተወሰነ ዒላማ ለመምታት ብዙ መጨነቅ የለባቸውም፤ በተለይም እንቅስቃሴያቸው በተገደቡባቸው ቀናት ብለዋል።