“ሁሉም ነገር ሰላም ሆኖ እኔ እንደተደሰትኩት አባትና እናቴም ይደሰታሉ ብዬ አምናለሁ” ጎተይቶም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሴቶች ማራቶን ውድድር አሸናፊ የሆነችው አትሌት ጎተይቶም ገ/ሥላሴ "ሁሉም ነገር ሰላም ሆኖ እኔ እንደተደሰትኩት አባትና እናቴም ይደሰታሉ ብዬ አምናለሁ” በማለት ተናገረች።
ጎተይቶም ይህንን ያለችው በአሜሪካ፣ ኦሪገን ግዛት እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት አመሻሽ ላይ በተካሄደው የሴቶች የማራቶን ውድድር ክብረ ወሰን አሻሽላ ወርቅ ካገኘች በኋላ ነው።
ይህንንም ስትናገር በእንባ ተሞልታ ሲሆን ከዚያ በኋላም እንባዋን በሰንደቅ አላማ ስትጠርግና የስራ ባልደረቦቿም አቅፈው ሲያባብሏት ታይተዋል።
የ27 ዓመቷ ጎተይቶም፣ 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ፣ከ11 ሰከንድ በመግባት ነበር በከፍተኛ ሁኔታ ስትፎካከራት የነበረችውን ኬንያዊቷን አትሌት ጁዲት ኮሪርን ማሸነፍ የቻለችው።
አትሌቷ ከዚህ ቀደም በብሪታናኒያዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ተይዞ የነበረውን የዓለም ሻምፒዮና ክብረ ወሰንም በማሻሻልም አዲስ የክብረ ወሰን ሰዓት አስመዝግባለች።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
በዚህ ዓመትም ከሱዳን ጋር በሚዋሰነው የአማራ ክልል አካባቢ አለመረጋጋት ተፈጥሮ ነበር።
ጎተይቶም ከውድድሩ በኋላ በአለም ሻምፒዮና ለአንቺ መገኘት ማለት ምንድን ነው? ተብላ በተጠየቀች ጊዜ
“ለኔ በጣም ትልቅ ነገር ነው። እግዚአብሔር ይመስገን። ለኔ መግለፅ ከምችለው በላይ ነው” በላይ ነው ስትል ምላሽ ሰጥታለች።
ትንሽ ቆይታም በእንባ ታጅባ “ሁሉም ነገር ሰላም ሆኖ እኔ እንደተደሰትኩት አባትና እናቴም ይደሰታሉ ብዬ አምናለሁ” በማለት ተናግራለች።
ትግራይ ክልል፣ ከመቀለ ወጣ ብላ በምትገኘው አዲ ጉዶም በሚባል ስፍራ የተወለደችው ጎተይቶም መስፍን ኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ የአትሌቲክስ ቡድን አባል ነበረች።
ባለፈው አመት የተነሳውን ጦርነት ተከትሎ ስልክን ጨምሮ በርካታ መሰረተ ልማት በመቋረጣቸው የትግራይ ክልል ከአለም ተቆራርጣ ትገኛለች።
የትግራይ ተወላጆች መሰረታዊ አገልግሎቶች በሌሉበት ሁኔታ ያሉ ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ሁኔታ አለማወቃቸው ፈታኝ እንዳደረገባቸው ይናገራሉ።
በትናንትናው ዕለት ሐምሌ 11፣ 2014 ዓ.ም በተካሄደው የሴቶች ማራቶን ውድድር ሲፎካከሩ የነበሩት ኢትዮጵያዊቷ ጎተይቶም እና ኬንያዊቷ ጁዲት የየራሳቸውን ምርጥ ሰዓት ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ጎተይቶም ለኢትዮጵያ ሦስተኛውን ወርቅ ያስገኘችው ከጁዲት ዘጠኝ ሰከንድ ቀድማ በመግባት ነበር።
ሌላኛዋ ትውልደ ኬንያዊት እስራኤላዊት ሎናህ ሳልፕተር 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ በመግባት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።
በውጤቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደተደሰተችና ውድድሩም በጣም ጥሩ እንደነበር አስረድታለች።
ጎተይቶም አሸናፊ ያደረጋት ምስጢር ስትናገርም “ 40ኛው ኪሎሜትር ላይ ስደርስ አፈትልኬ ለመውጣት አቅጄ ነበር። ያንን ስልት በመጠቀሜም ወርቅ ማምጣት ችያለሁ” ብላለች።
በተለይም ኬንያውን አትሌቶች በማራቶን የሩጫ ውድድር ውጤታማ የሚባሉ ሲሆን እንዴት ልታሸንፊ ቻልሽ የሚል ጥያቄ ቀርቦላት ነበር።
“ ዋናው ነገር ጠንክሮ መስራት ነው ። ጠንክሮ ከተሰራ ማንንም ቢሆን ማሸነፍ ይቻላል። አገሬ እያለሁ ጠንክሬ ሰርቻለሁ። በእርግጥ ኬንያውያን ከባድ እንደሆኑ አውቃለሁ። " ያለችው አትሌቷ
" ፍጥነት የመቀየር አላማ ይዤ ነው የገባሁት እናም በመጨረሻው ሰዓት ከፍተኛ ፍጥነት ስለነበረኝና ያንን መጠቀም ስለቻልኩ አሸንፌያለሁ” ብላለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኤርትራዊቷ ናዝሬት ወልዱም 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ29 ሰከንድ በመግባት አራተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ አዲስ ብሔራዊ ክብረ ወሰን አስመዝግባለች።
ዕሁድ እለት ሐምሌ 10/ 2014 ዓ.ም በተካሄደው የወንዶች የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው ታምራት ቶላ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ በማጠናቀቅ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወሳል።
ባለፈው አርብ ምሽት በተጀመረው በዚህ ውድድር ላይ በ10 ሺህ ሜትር ውድድር አትሌት ለተሰንበት ግደይ በአስደናቂ አጨራረስ ኬንያውያን አትሌቶችን በማስከትል የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች።
ዛሬ ንጋት ላይ በተካሄደው የሴቶች 1500 ሜትር ውድድርም አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ 3 ደቂቃ፣ከ54 ሰከንድ፣ከ52 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች።
በወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክልም አትሌት ለሜቻ ግርማ 8 ደቂቃ፣ከ26 ሰከንድ፣ ከ01 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።
በዚህም ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ሦስት ወርቅ እና ሦስት ብርን ጨምሮ ስድስት ሜዳሊያ በማግኘት በሜዳሊያ ሰንጠረዡ አሜሪካን በመከተል ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።












