የዓለም ሻምፒዮናው ታምራት፡ ውስጤን አሳምኜ የመጣሁበትን ነው ያደረኩት

አትሌት ታምራት ቶላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ታምራት ቶላ

ትናንት እሁድ ሐምሌ 10/2014 ዓ.ም. በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ውድድር ላይ ባለድል የሆነው አትሌት ታምራት ቶላ “ውስጤን አሳምኜ የመጣሁበትን ነው ያደረኩት” ሲል ከውድድሩ በኋላ አስተያየቱን ሰጠ።

አትሌት ታምራት፤ ወደ ውድድሩ ከመግባቱ በፊት የመጨረሻዎቹን 10 ኪሎ ሜትሮች ከፊት ወጥቶ ለብቻው ሮጦ ለማሸነፍ አቅዶ እንደነበረ ተናግሯል።

“እስከ 1 ሰዓት ከ 40 ደቂቃ ድረስ ከቡድኑ ጋር ነበረኩኝ። የመጨረሻዎቹን 10 ኪሎ ሜትሮች ፈጣን ሩጫ ለመሮጥ ውስጤን አሳምኜ ስለመጣሁ ያንን ለማድረግ ነው የሄድኩት። አደረኩት” ሲል ተናግሯል።

አትሌት ታምራት ሻምፒዮን ለመሆን የቻለው ተፎካካሪዎቹን በረዥም ርቀት ጥሎ በመውጣት 2:05:36 በሆነ ሰዓት ማጠናቀቅ ከቻለ በኋላ ነው።

አትሌት ታምራት ቶላ ኦሪገን ላይ እየተካሄደ በሚገኘው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ውድድር ማሸነፍ ብቻም ሳይሆን የውድድሩን ክብረ ወሰን አሻሽሏል።

አትሌት ታምራትን ተከትሎ በመግባት የብር ሜዳሊያ ለአገሩ ያስገኘው አትሌት ሞሰነት ገረመው በበኩሉ እርሱ እና አትሌት ታምራት ያስገኙት ድል ኢትዮጵያ የበላይነቱን እንድትይዝ አድርጓል ብሏል።

“. . . ወርቅ እና ብር አግኝተናል። ይህም የማራቶን የበላይነቱን እንድንይዝ አድርጎናል ብዬ አስባለሁ። በዚህም ደስተኛ ነኝ’’ ብሏል።

በአሜሪካዋ ኦሪጎን ግዛት እየተካሄደ ባለው የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አስደናቂ ድልን እያስመዘገቡ ይገኛሉ።

አትሌት ለተሰንበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያውያን በዓለም ሻምፒዮናው ላይ

አሜሪካ ኦሪገን ግዛት ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንጸባራቂ ድሎችን እያስመዘገቡ ይገኛሉ።

ቅዳሜ ሐምሌ 09/2014 ዓ.ም. በተካሄደው የ10 ሺህ ሜትር ውድድር አትሌት ለተሰንበት ግደይ በአስደናቂ አጨራረስ ኬንያውያን አትሌቶችን በማስከትል የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች።

የ24 ዓመቷ አትሌት በዚህ ውድድር 30፡09፡94 ሰዓት በማስመዝገብ ነው የአንደኛነት ስፍራን በማግኘት ነው የወርቅ ሜዳሊያዋን ያጠለቀችው።

ኢትዮጵያ በሁለት ወርቅ እና በአንድ ብር ስድስት ወርቅ ከሰበሰበችው አሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የአሜሪካዋ ኦሪገኦን ዕሁድ ዕለት የወንዶች የ10ሺህ ሜትር ፍጻሜን አስተናግዳለች። ኢትዮጵያ በውድድሩ እንደ ሰለሞን ባረጋ ባሉ ጠንካራ አትሌቶች ተወክላ የነበረ ቢሆንም ኡጋንዳ የበላይነቱን ይዛ አጠናቃለች።

ከፍተኛ ፉክክር በታየበት በዚህ ውድድር ጆሱ ቼፕቴጊ 27.27.43 በሆነ ሰዓት ወርቁን ሲወስድ፣ ኬንያዊው ስታንሊ ኡምቡሩ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ሌላኛው ኡጋንዳዊ ጃኮብ ኪፕሊሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።

በዚህ ውድድር ከወርቅ እስከ ነሐስ አሸናፊ የሆኑት አትሌቶች በሙሉ በመድረኩ የዓመቱን ምርጥ ሰዓታት ማስመዝገባቸው የውድድሩን ጠንካራነት ያስመሰከረ ነው ተብሏል።

በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ይገባል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው እና በቶኪዮ ኦሊምፒክ በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው ሰለሞን ባረጋ 5ኛ ሆኖ ሲያጠናቀቅ፣ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ የቆው በሪሁ አረጋዊ 7ኛ ሆኖ ውድድሩን ጨርሷል።

ዛሬ የሚጠበቁ ውድድሮች

ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 11/2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሦስት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

ቀድሞ የሚካሄደው የሴቶች ማራቶን ነው። በዚህ እልህ አስጨራሽ ውድድር ኢትዮጵያ በአሼቴ በከሬ፣ በጎትይቶም ገብረ ሥላሴ እና በአባበል የሻነህ ትወከላለች።

በመቀጠል የወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል የሚካሄድ ሲሆን፤ በዚህም ለሜቻ ግርማ፣ ጌትነት ዋለ እና ኃይለማርያም አማረ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ናቸው።

ሌላኛው ተጠባቂ ውድድር የ1500 ሜትር የሴቶች ፍጻሜ ነው። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉት አትሌቶች ጉዳፍ ፀጋዬ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ እና ሒሩት መሸሻ ናቸው።