ለተሰንበት ግደይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10 ሺህ ሜትር አሸናፊ ሆነች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለተሰንበት ግደይ በአሜሪካ ኦሪገን እየተካሄደ ባለው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10 ሺህ ሜትር አሸናፊ ሆነች።
የ24 ዓመቷ አትሌት በዚህ ውድድር 30፡09፡94 ሰዓት በማስመዝገብ ነው የአንደኛነት ስፍራን በማግኘት የወርቅ ሜዳሊያዋን ያጠለቀችው።
ፍጻሜው ላይ ከፍተኛ ትንቅንቅ በታየበት በዚህ ውድድር፣ ለተሰንበትን ተከትለው ኬንያውያን አትሌቶች ሄለን ኦቢሪ በሁለተኝነት እና ማርጋሬት ቼሊሞ ኪምኬምቦይ በሦስተኛነት አጠናቀዋል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷና ለሆላንድ የምትወደዳረው ሲፋን ሐሰን በዚህ ውድድር ላይ በአራተኝነት አጠናቃለች።
በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶቹ እጅጋዬሁ ታዬ 6ኛ፣ ቦሰና ሙላቴ 8ኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን አጠናቀዋል።
ቀደም ሲል በ10 ሺህ ሜትር፣ በ5 ሺህ ሜትር እና በግማሽ ማራቶች ሦስት የዓለም ክብረ ወሰኖችን የያዘችው አትሌት ለተሰንበት በዚህ ዓለም አቀፍ ከፍተኛ ውድድር ላይ በመሳተፍም አሸናፊነቷን አስጠብቃለች።
ለተሰንበት በቶኪዮ ማራቶን የአሸናፊነት ቦታ ትልቅ ግምት የተሰጣት ሲሆን 3ኛ በመሆን የነሐስ ተሸላሚ ሆናለች። እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2019 በኳታር ዶሃ በነበረው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለተሰንበት በሁለተኝነት አጠናቃለች።
ለተሰንበት ከውድድሩ በኋላም ለመገናኛ ብዙኃ በሰጠችው አስተያየት “ይህንን ውድድር ማሸነፍ ትልቁ አላማዬ ነበር። ህልሜም እውን ሆነ። ይህ ድል ከዓለም ክብረ ወሰን በበለጠ ለእኔ ትልቁ ነው። በውድድሩ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብላለች።
አትሌቷ በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ስፔን ቫሌንሺያ በተካሄደው ግማሽ ማራቶን ሩጫ የዓለም ክብረ ወሰን መስበሯ ይታወሳል።
ለተሰንበት በኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲክ በ1 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ02 ሰኮንድ ተይዞ የነበረውን የግማሽ ማራቶን ክብረወሰን በማሻሻል 1 ሰዓት ከ02 ደቂቃ ከ52 ሰኮንዶች በመግባት ክብረ ወሰን ጨብጣለች።
በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር የሚካሄድ ሲሆን በሪሁ አረጋዊ፣ ሰለሞን ባረጋና ታደሰ ወርቁ እንደሚወዳደሩ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
ሰለሞን ባረጋ በጃፓን ቶኪዮ ኦሊምፒክ በ10 ሺህ ሜትር በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ ይታወሳል።
ሰለሞን በዚህ ውድድር ያስመዘገበው ሰዓት 27፡43፡22 ሲሆን የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነውንም ጆሹዋ ቼፕቴጊን አስከትሎ ነው የገባው።
በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ጉዳፍ ፀጋይ፣ ፍረወይኒ ኃይሉና ሂሩት መሸሻ ማጣሪያውን አልፈዋል።












