ጎተይቶም ገ/ሥላሴ በሴቶች ማራቶን ለኢትዮጵያ ወርቅ አስገኘች

 ጎተይቶም ገብረ ሥላሴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያዊቷ ጎተይቶም ገብረ ሥላሴ በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በማራቶን ውድድር አንደኛ በመውጣት አሸነፈች።

በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሰኞ አመሻሽ ላይ በተካሄደው የሴቶች ማራቶን ውድድር አትሌት ጎተይቶም ገብረ ሥላሴ 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በመግባት አሸንፋ ነው ለአገሯ ሦስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች።

ጎተይቶም ገብረ ሥላሴ ከባዱን ውድድር ያሸነፈችው ከዚህ ቀደም በብሪታኒያዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ተይዞ የነበረውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ክብረ ወሰንን በማሻሻል ጭምር ነው።

ጎተይቶም ሁለተኛ ከወጣችው ኬንያዊት አትሌት ከባድ ፉክክር የገጠማት ቢሆንም የመጨረሻዎቹን ኪሎ ሜትሮች በብቃት በመሮጥ የነበራቸውን ልዩነት አስፍታ ድንቅ የበላይነትን በመያዝ ማሸነፍ ችላለች።

በዚህም እስካሁን ባለው ውድድር ኢትዮጵያ በሦስት የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያ ከውድድሩ አስተናጋጅ አሜሪካ በመቀጠል በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።

ሰኞ ሐምሌ 11/2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በተካሄደው የሴቶች የማራቶን ውድድር አባብል የሻነ፣ አሸቴ በከሪ፣ ጎተይቶም ገ/ሥላሴ የተሳተፉ ሲሆን፣ ጎተይቶም በአንደኝነት ማጠናቀቅ ስትችል ፣ አበባ የሻነ በውድድሩ መሃል በህመም ምክንያት አቋርጣ ወጥታለች።

ውድድሩ በስተመጨረሻ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ሲሆን፣ ጎተይቶም በሰፊ ልዩነት ኬንያዊቷን ጁዲት ኮሪርን ጥላ በመግባት አሸናፊ ሆናለች።

ኬንያዊቷ ጁዲት ሁለተኛ ደረጃ ይዛ በማጠናቀቅ ለአገሯ ብር ስታስገኝ እስራኤላዊቷ በ3ኛ ደረጃ አጠናቃለች።

ትናንት ዕሁድ ሐምሌ 10/2014 ዓ.ም በተካሄደው የወንዶች የማራቶን ውድድር ላይ ታምራት ቶላ እና ሞሰነት ገረመው አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ማሸነፋቸው ይታወሳል።

አትሌት ታምራት ሻምፒዮን ለመሆን የቻለው ተፎካካሪዎቹን በረዥም ርቀት ጥሎ በመውጣት 2:05:36 በሆነ ሰዓት ማጠናቀቅ ከቻለ በኋላ ነው።

በዚህም በአሜሪካ ኦሪገን እየተካሄደ ባለው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተለይ በማራቶን ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያ የበላይነቱን ይዛለች።

ባለፈው አርብ ምሽት በተጀመረው በዚህ ውድድር ላይ በ10 ሺህ ሜትር ውድድር አትሌት ለተሰንበት ግደይ በአስደናቂ አጨራረስ ኬንያውያን አትሌቶችን በማስከትል የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች።

በእስካሁኑ ውጤት ኢትዮጵያ በዚህ የዓለም ሻምፒዮና ሦስት የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 11/2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሌሎች ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

በቀጣይ የወንዶች 3 ሺህ ሜትር የመሰናክል ውድድር የሚካሄድ ሲሆን፤ በዚህም ለሜቻ ግርማ፣ ጌትነት ዋለ እና ኃይለማርያም አማረ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ናቸው።

ሌላኛው ተጠባቂ ውድድር የ1500 ሜትር የሴቶች የፍጻሜ ውድድር ነው። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉት አትሌቶች ጉዳፍ ፀጋዬ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ እና ሒሩት መሸሻ ናቸው።