አሜሪካዊው የኢንሹራንስ ኩባንያ ኃላፊ እንዴት ተገደለ?

ከግድያው ጋር በተያያዘ ለጥያቄ የሚፈለገውን ግለሰብ በመጠቆም ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል

የፎቶው ባለመብት, NYPD

የኒውዮርክ ፖሊስ የጤና ኢንሹራንስ ዋና ስራ አስፈጻሚው ግድያ በተመለከተ ተጠርጣሪ ያለውን አንድ ጭምብል ያላደረገ ግለሰብ ሁለት ፎቶዎችን አውጥቷል።

የዩናይትድሄልዝኬር ኃላፊው ብሪያን ቶምፕሰን ረቡዕ ጥዋት፣ ህዳር 27/ 2017 ዓ.ም ማንሃተን ከሚገኘው ሂልተን ሆቴል ውጭ ጀርባው ላይ በጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፏል።

ገዳዩ የቶምፕሰንን ንብረት ሳይወስድ ከቦታው ሸሽቷል። ሟች አስቀድሞ በተደረገ ዕቅድ ዒላማ መሆኑን ፖሊስ ያምናል።

መርማሪዎች ተጠርጣሪውን ለመከታተል ፊትን ለይቶ የሚያሳውቅ ቴክኖሎጂ እና በጥይቶቹ ላይ በሚስጥር የተፃፉ መልዕክቶችን ተጠቅመው እየመረመሩ ነው። የግድያውን ምክንያት እስካሁን ይፋ አላደረጉም።

ግድያው እንዴት ተፈጸመ? ገዳይስ እንዴት አመለጠ?

ጥቃቱ የተፈፀመው ጠዋት 1፡00 ሰዓት ገደማ በታይምስ ስኩዌር እና በሴንትራል ፓርክ አቅራቢያ በሚገኘው ማንሃተን ውስጥ ነው። ቶምፕሰን በዕለቱ በባለሀብቶች ኮንፈረንስ ላይ ተገኝቶ ንግግር እንዲያደርግ ቀጠሮ ተይዞለት ነበር።

እንደ ፖሊስ ገለጻ ከሆነ ተጠርጣሪው ጥቁር የፊት ጭንብል እና ቡናማ ወይም ክሬም ቀለም ያለው ጃኬት ለብሶ ቶምፕሰን ንግግር ያደርግበታል ተብሎ በሚጠበቅበት ሂልተን ሆቴል ደጃፍ ለአምስት ደቂቃ ያህል የጠበቀው ይመስላል።

በእግሩ በቦታው የደረሰው ቶምፕሰን ጀርባው እና እግሩ በጥይት ተመትቶ በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል ከደረሰ ከግማሽ ሰዓት በኋላ ህይወቱ ማለፉ ተነግሯል።

የተጠርጣሪው መሳሪያ አልተኩስ ያለ ቢመስልም በፍጥነት አስተካክሎ መተኮስ መቀጠል መቻሉን የኒውዮርክ ፖሊስ ዲፓርትመንት (ኤንዋይፒዲ) የመርማሪዎች ዋና አዛዥ ጆሴፍ ኬኒ ገልጸዋል።

ከድንነት ካሜራ ቀረጻዎች እንደተገኘ ተንቀሳቃሽ ምስል ከሆነ ገዳዩ ሽጉጡ ላይ ድምጽ ማፈኛ እንደገጠመ የሚያሳይ ይመስላል ሲል ቢቢሲ ቬሪፋይ ገልጿል።

የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ ለኤምኤስኤንቢሲ እንደተናገሩት ድምጽ ማፈኛ መጠቀም ታይቶ የማይታወቅ ነገር ነው።

"ድምጽ ማፈኛ ከዚህ በፊት አይቼ አላውቅም። ይህ በእውነት ለሁላችንም አስደንጋጭ ነገር ነበር" ሲሉ የቀድሞው የኤንዋይፒዲ ባልደረባ ተናግረዋል።

መርማሪዎች ሽጉጡ ቢቲ ስቴሽን ስድስት 9 ነው ብለው እንደሚያምኑ ተዘግቧል። ይህ መሳሪያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዘመን የልዩ ዘመቻ ኃይሎች ይጠቀሙበት የነበረው የሽጉጥ አይነት ነው።

ፖሊስ መሳሪያው የት እንደተገዛ ለማወቅ በኮነቲከት የሚገኙ የመሣሪያ መደብሮችን ጎብኝቷል ተብሏል።

ከተኩሱ በኋላ ተጠርጣሪው በእግር ሲሸሽ በቪዲዮ ላይ ታይቷል። ተጠርጣሪው የሊፍት ንብረት የሆነውን ኤሌክትሪክ ብስክሌት ተጠቅሟል የሚል እምነት ባለስልጣናት መጀመሪያ ላይ ነበራቸው።

ምርመራው

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስካሁን በቶምፕሰን ግድያ ዙሪያ የሚደረገው ምርመራ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመለየት ጥቂት ፍንጮች ላይ ብቻ ያተኮረ ሆኗል።

ሐሙስ ዕለት ጭንብል ያላደረገ ግለሰብ ሁለት ፎቶዎችን ይፋ ያደረጉት ባለስልጠናት ኤንዋይፒዲ ከግድያው ጋር በተያያዘ "ለጥያቄ ይፈልገዋል" ብሏል።

የህግ አስከባሪ ምንጮች ለሲቢኤስ እንደተናገሩት ከሆነ ግለሰቡ በአካባቢው በሚገኝ ሆስቴል ውስጥ ለመግባት የሃሰተኛ መታወቂያ ተጠቅሟል ተብሎ ይታመናል። ጥቅም ላይ የዋለው ስም የእውነተኛ ሰው ነው ተብሎ አይታመንም።

መርማሪዎች እንደሚያምኑት ግለሰቡ ከጥቃቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ከአትላንታ፣ ጆርጂያ ወደ ኒውዮርክ በአውቶቡስ እንደተጓዘ ስለምርመራው አጭር መግለጫ ያገኙ ግለሰብን ጠቅሶ ሲቢኤስ ዘግቧል። ግለሰቡ የአውቶቡስ ጉዞ መነሻው አትላንታ ይሁን መንገድ ላይ ይሳፈር ለጊዜው ግልጽ አይደለም።

ከተጠርጣሪው ጋር ተመሳሳይ አይነት ሰው ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።

ተጠርጣሪው ጥቃት ከማድረሱ ከደቂቃዎች በፊት በአቅራቢያው በሚገኝ ስታርባክስ ፎቶ መነሳቱን ፖሊስ ገልጿል።

በምስሉ ላይ በጭንብል ቢሸፈንም ጭምብሉ በበቂ ሁኔታ ወደ ታች በመጎተቱ ዓይኖቹ እና የአፍንጫው ክፍል እንደሚታዩ የፖሊስ ምንጮች ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

ምስሉን ተጠቅመው መርማሪዎች በፊት መለያ ሶፍትዌር ማንነቱን ለመለየት እየሞከሩ ነው።

ምንም እንኳን ገዳዩ የቶምፕሰንን ንብረት ሳይወስድ ቢሸሽም መርማሪዎች እስካሁን ስለ ግድያው ምክንያት አላወቁም።

ፖሊስ በቦታው የተገኙ ሦስት የጥይት ቀለሃዎችን እና ሦስት ጥይቶች ላይ ዲኤንኤ ምርመራ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

"መካድ"፣ "መከላከል" እና "ማስቀመጥ" የሚሉት ቃላት በቀለሃዎቹ ላይ ተገኝተዋል ሲሉ ሁለት የህግ አስከባሪ ምንጮች ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

መርማሪዎች ይህ "የኢንሹራንስ ሦስቱ ዲዎች" ማጣቀሻ ሊሆን ይችላል ብለው ያምናሉ። ማጣቀሻዎቹ በኢንዱስትሪው ተቃዋሚዎች የኢንሹራንስ ድርጅቶችን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላል።

ደንቦቹ በውስብስቡ የአሜሪካ በተለይም በአብዛኛው በግል የሚተዳደር የጤና አጠባበቅ ስርዓት ውስጥ ታካሚዎች የሚያቀርቡትን የክፍያ መጠየቂያ ለመከልከል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚጠቀሙባቸውን ስልቶች ያመለክታሉ።

ቃላቱ ቢመሳሰሉም ግን 'ዲሌይ፣ ዲናይ፣ ዲፌንድ፡ ዋይ ኢንሹራንስ ካምፓኒስ ዶንት ፔይ ክሌይምስ ኤንድ ዋት ዩ ካን ዱ አባውት ኢት' ከሚለው የመጽሐፍ ርዕስ ጋር ተመሳሳይ አይደሉም።

እአአ በ 2010 የታተመው መጽሐፍ በኒው ጀርሲ ሩትገርስ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሁር በሆኑት በጄይ ፌይንማን የተጻፈ ነው። የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ለማጋለጥ እና ለአሜሪካውያን ደግሞ ስርዓቱን እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ የሚያሳይ ሆኖ ቀርቧል።

የፕሮፌሰር ፌይንማን አስተያየት ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በተጠርጣሪው ማምለጫ መንገድ ላይ ተንቀሳቃሽ ስልክ ተገኝቷል። ፖሊስ ስልኩን "እየመረመርኩ ነው" ብሏል።

በተጠርጣሪው ተጥሏል ተብሎ የሚታመን የቡና ኩባያም ለጣት አሻራዎች ምርመራ በሚል ወደ ኤንዋይፒዲ ወንጀል ላብራቶሪ ተልኳል።

ቀደም ሲል ግለሰቡ ሲገባበት በነበረው በማንሃታን አፐር ዌስት ሳይድ በሚገኝ ቦታ ላይ ፍተሻ መደረጉን መርማሪዎቹ ገልጸዋል።

ቦታው በፍሬድሪክ ዳግላስ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክት አቅራቢያ ሲሆን ተጠርጣሪውን ወንጀሉ በተፈጸመበት ዕለት ጠዋት 11፡00 ሰዓት ላይ ከቤት ውጭ በደህነነት ካሜራዎች ታይቷል ተብሏል።

ግድያው የተፈጸመበት ጎዳና አቅራቢያው በሚገኘው ማሪዮት ሆቴል የሚገኘውን የቶምፕሰን ክፍል እንደሚፈትሽ ፖሊስ ተናግሯል።

ቶምፕሰን በአውሮፓውያኑ 2004 ከፕራይስዋተርሃውስኮፐርስ የአካውንቲንግ ድርጅት የአሜሪካን ትልቁን የግል መድን ተቋም ወደ ሆነው ዩናይትድሄልዝ ተቀላቅሏል።

በየጊዜው በማደግም በ 2021 ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከመሆን ባለፈ በእሱ ስር ኩባንያውን በጣም ትርፋማ ዓመታትን አሳልፏል።

የቶምፕሰን ባለቤት ከኤምኤስኤንቢሲ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ቀደም ሲል አንዳንድ ዛቻዎች እንደነበሩ ተናግራለች። ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥባለች።

"እሱ ሲያስፈራሩት የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንዳሉ መናገሩን አውቃለሁ" ብላለች።

በቶምፕሰን የትውልድ ከተማ ማፕል ግሮቭ፣ ሚኒሶታ በ2018 በቤቱ አንድ አጠራጣሪ ክስተት ነበር ሲል ፖሊስ ገልጿል።

ክስተቱ ምንም አይነት የወንጀል ድርጊት ሳይገኝበት ተትቷል። ምንም ተጨማሪ መረጃዎችም አልተሰጡም።