ለ43 ዓመታት ኢኳቶሪያል ጊኒን የመሩት ፕሬዚዳንት ለስድስተኛ ጊዜ አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም ላይ በመሪነት ለረዥም ዓመታት በስልጣን ላይ በመቆየት የቁንጮነቱን ስፍራ የተቆናጠጡት የኢኳቶሪያል ጊኒው ፕሬዝደንት አምባገነናዊ አገዛዛቸውን ማስቀጠል የሚያስችላቸውን ምርጫ አሸንፉ።
የ80 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማ ምባሶጎ 95 በመቶ የሚጠጋ ድምጽ ማግኘታቸውን ባለስልጣናቱ ከምርጫው ከስድስት ቀናት በኋላ አስታውቀዋል።
የፕሬዚዳንቱ ልጅ እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ቴዎዶሮ ንጉዌማ ኦቢያንግ ማንጉ "ውጤቱ ትክክል መሆናችንን ያረጋግጣል። ትልቅ ፓርቲ ሆነን እንቀጥላለን" ብለዋል።
አንዳንድ የተቃዋሚ ዕጩዎች በምርጫው ቢሳተፉም አንዳቸውም ያሸንፋሉ ተብሎ አልተጠበቀም።
ፕሬዚደንት ኦቢያንግ በነዳጅ በበለጸገችው የመካከለኛው አፍሪካዊት ሃገር ላይ ጠንካራ ቁጥጥር አላቸው። የቤተሰባቸው አባላትም ቁልፍ የመንግስት ኃላፊነቶችን ይዘዋል።
በአውሮፓውያኑ 1979 ወታደሩ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ መሪነት የመጡ ሲሆን ከበርካታ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች አምልጠዋል።
ከአጎታቸው ፍራንሲስኮ ማኪያስ ንጉሜ ቢሮውን ሲረከቡ አንዳንድ ማሻሻያዎችን ቢያደርጉም የንጉዌማን ፍጹማዊ የበላይነት በሃገሪቱ ላይ አስቀጥለዋል።
ተቃዋሚዎችን የማይታገሱ ሲሆን ሁሉም መገናኛ ብዙሃን በመንግስት ባለቤትነት የተያዙ ወይም በአጋሮቻቸው ቁጥጥር ስር ያሉ በመሆናቸው የነጻ ፕሬስ እጦት ክፉኛ በሃገሪቱ ተስፋፍቷል።
ከዚህ ቀደም በሰብዓዊ መብት ረገጣ እና በምርጫ መጭበርበር የቀረቡባቸውን ውንጀላዎች ውድቅ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ኦቢያንግ ስድስተኛ የስልጣን ዘመናቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ የጠለሸ ስማቸውን ለማጥራት እንደሚጠቀሙበት ተገምቷል።
መስከረም ወር ላይ መንግሥት የሞት ቅጣት መሰረዙ በተባሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ ተችሮታል።
ተቺዎች እንደሚሉት ኢኳቶሪያል ጊኒ የተጭበረበረ የምርጫ ውጤት ታሪክ አላት።












