ኢራን በሳልማን ሩሽዲ ጥቃት ውስጥ ‘እጄ የለበትም’ አለች

ሳልማን ሩሽዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢራን ሳልማን ሩሽዲ ባለፈው ሳምንት አርብ አሜሪካ ውስጥ በተፈጸመበት የስለት ጥቃት ውስጥ “እጄ የለበትም” አለች።

ለጥቃቱ ተጠያቂው ደራሲው ሳልማን እና ደጋፊዎቹ ናቸው ብላለች ኢራን።

የ75 ዓመቱ ደራሲ ኒው ዮርክ ውስጥ መድረክ ላይ ሳለ በስለት መወጋቱ ይታወሳል። ከተደረገለት ህክምና በኋላ አሁን ያለ ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ ድጋፍ መተንፈስ ጀምሯል።

ደራሲው ‘ዘ ሳታኒክ ቨርስ’ የተባለውን መጽሐፉን እአአ በ1988 ካወጣ በኋላ የግድያ ዛቻ ሲደርስበት ቆይቷል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢራን መገናኛ ብዙኃን በደራሲው በስለት መወጋት ደስታቸውን ማንጸባረቃቸው “አሳፋሪ ነው” ብለዋል።

'ደይሊ ጃሚ ጃም' የተባለው የኢራን ቲቪ ደራሲው ከጥቃቱ በኋላ ዐይኑን ሊያጣ ይችላል በማለት “ሰይጣኑ ዐይኑ ጠፍቷል” ሲል ዘግቧል።

ደራሲው ባለፈው አርብ በስለት ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ብዙዎች በድርጊቱ ኢራንን ጠርጥረዋታል።

ከ30 ዓመት በፊት ደራሲው እንዲገደል የኢራን መንፈሳዊ መሪ ጥሪ ማቅረባቸውና ገንዘብ ሽልማት መቅረቡ አይዘነጋም።

ሆኖም ግን የኢራን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ “ከጥቃቱ ጋር የሚያስገናኘን ነገር የለም። ማንም ኢራንን መውቀስ አይችልም” ብለዋል።

“ለዚህ ጥቃት ተጠያቂው ራሱ ሳልማን ሩሺዲ እና ደጋፊዎቹ ናቸው። የተቀደሱ የእስልምና አስተምህሮዎችን በማንቋሸሽ ቀዩን መስመር አልፏል። 1.5 ቢሊዮን የሃይማኖቱን ተከታዮችም አስቀይሟል። ራሱን ለሕዝብ ቁጣ ያጋለጠው ራሱ ነው” ሲሉም አክለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሳልማን ሩሽዲን ለተፈጸመበት ጥቃት ተጠያቂ ማድረግ “ረብ የለሽ” ነው ብለዋል።

“ጥቃቱ በደራሲው ላይ ብቻ ሳይሆን በነጻ ንግግር ላይ ያነጣጠረ ነው” ሲሉም አክለዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እንዳሉት፣ ደራሲው የዓለም አቀፍ የንግግር ነጻነት ተምሳሌት ነው።

“ለንግግር ነጻነት ታግሏል። ለሃይማኖት፣ ለእምነትና ለመገናኛ ብዙኃን ነጻነትም ታግሏል። ኢራን ለዓመታት ደራሲው ላይ ጥቃት እንዲደርስ አነሳስታለች” ብለዋል።

“አሜሪካ እና አጋሮቿ ይህንን ለመቅረፍ ይሠራሉ” ሲሉም አክለዋል።

የደራሲው ልጅ እንዳለው፣ ሩሺዲ ጤናው ትንሽ ቢሻሻልም ጉዳቱ አስጊ ነው።

ያለ አጋዥ መሣሪያ በራሱ መተንፈስ መቻሉ መልካም ዜና እንደሆነም ቤተሰቡ ገልጿል።

“ጥቂት መናገር ችሏል” ብሏል ልጁ።

የደራሲው ወኪል እንዳሉት፣ ጉዳት የደረሰበት በአንድ ክንዱ ነርቭ ላይ ሲሆን፣ ጉበቱም ተጎድቷል። ዐይኑን ሊያጣ እንደሚችልም ተሰግቷል።

 የ24 ዓመቱ ሃዲ ማቴር ደራሲውን በስለት በመውጋት ተጠርጥሮ በግድያ ሙከራ ክስ ቀርቦበታል።