ኔይማር በማጭበርበር ተከሶ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታዋቂው ብራዚላዊ እግር ኳስ ተጫዋች ኔይማር ጁኒየር በዝውውሩ ወቅት ተፈጽመዋል ከተባሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ በማጭበርበር ተከሶ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነው።
አሁን ለፈረንሳዩ ፓሪ ሴን ዠርመን (ፒኤስጂ) የሚጫወተው ኔይማር፤ ለዓመታት በዘለቀ የፍርድ ቤት ጉዳይ በማጭበርበር እና በሙስና ክስ ቀርቦበታል።
የኔይማር ጉዳይ በፍርድ ቤት የሚታየው ለሁለት ሳምንታት በመጪው ጥቅምት ወር የዓለም ዋንጫ ውድድር ኳታር ውስጥ መካሄድ ከመጀመሩ በፊት ነው።
ከኔይማር በተጨማሪ ሌሎች ታዋቂ ሰዎችም ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
ሁለት የቀድሞዎቹ የባርሴሎና እግር ኳስ ቡድን ፕሬዝዳንቶች ጆሴፍ ማሪያ ባርቶሙ እና ሳንድሮ ሮሴል እንዲሁም የኔይማር ወላጆች በተመሳሳይ ክስ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ የስፔን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በዚህ ክስ ውስጥ ስማቸው የተነሳው ግለሰቦች በሙሉ የቀረበባቸውን ውንጀላ አስተባብለዋል። ክሱን ያቀረበው ተቋም ኔይማር ከዓመታት በፊት ከብራዚሉ ሳንቶስ ክለብ ሲዘዋወር 40 በመቶ ገንዘብ ይገባኛል ብሏል።
ኔይማር የተዘዋወረበት የገንዘብ መጠን እንዳይገለጽ በመደረጉ ከሳሽ ከዝውውሩ ሊያገኝ ከሚገባው ገንዘብ ያነሰ መቀበሉን ጠቅሷል።
በጣም ከፍተኛ ነው የሚባለው የኔይማር የዝውውር ገንዘብ መጠን በሕጋዊ ውዝግብ የተከበበ እንደሆነ ይነገራል።
ባርሴሎናን የተሰናበተው ኔይማር ከፍርድ ቤት ውጪ በሆነ ስምምነት በ222 ሚሊዮን ዩሮ ወደ ፒኤስጂ ነበር ያቀናው።
ከዚህ ቀደም በነበረ የፍርድ ቤት ክርክር ባርሴሎና ኔይማርን ከሳንቶስ ባዘዋወረበት ሂደት ሕጋዊ ጉዳዮች ተጥሰዋል በሚል ባርሴሎና 5.5 ሚሊዮን ዩሮ እንዲከፍል ተፈርዶበት ነበር።












