የሶሪያ አማፂያን መሪ ፀጉሯን ካልሸፈነች ሴት ጋር ፎቶ አልነሳም ማለታቸው አወዛገበ

አል-ሻራ እና አብራው ፎቶ የተነሳችው ሊያ

የፎቶው ባለመብት, X

የሶሪያ አማፂያን መሪ አሕመድ አል-ሻራ ፀጉሯን ካልሸፈነች ሴት ጋር ፎቶ አልነሳም የሚል ምልክት ማሳየቱ አወዛጋቢ ሆኗል።

አል-ሻራ ባለፈው ሳምንት ከአንዲት ወጣት ሴት ጋር ፎቶ ከመነሳቱ በፊት ፀጉሯን እንድትሸፍን ሲጠቁም የሚያሳይ ቪድዮ በማኅበራዊ ሚድያ ተሰራጭቷል።

የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች በሁለት ጎራ ተከፍለው ሲወዛገቡ ተስተውለዋል።

ሊበራሎች እና ወግ አጥባቂዎች የአል-ሻራን ድርጊት ተከትሎ ሶሪያ ወደፊት ምን አይነት አቅጣጫ ልትከተል ትችላለች የሚል ክርክር አንስተዋል።

የሱኒ ኢስላማዊው ሀያት ታሕሪር አል-ሻም (ኤችቲኤስ) ቡድን መሪ ይህን ማድረጉ ወደፊት ኢስላማዊ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ ሊያስገድድ ይችላል ሲሉ ሊበራሎች ወቅሰዋል።

ወግ አጥባቂዎች ደግሞ መጀመሪያውን ከሴት ጋር ፎቶ መነሳት አልነበረበትም ሲሉ አል-ሻራን ተችተዋል።

"እኔ አላስገደድኳትም። ነገር ግን ይህ ግላዊ ነፃነቴ ነው። ፎቶ ስነሳ እኔ በምፈልገው መንገድ መሆን አለበት" ሲል ከቢቢሲው ዠረሚ ቦዌን ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ ተናግሯል።

ሊያ ኼራላሕ የተባለችው ቪድዮው ላይ የምትታየው ሴት ፀጉሯን እንድትሸፍን በመጠየቋ ቅር እንዳልተሰኘች ትናገራለች።

እሷ እንደምትለው አል-ሻራ "ትሁት እና አባታዊ በሆነ መንገድ ነው" የጠየቃት፤ አልፎም መሪው "ራሱን እንዴት ማቅረብ እንዳለበት የመወሰን መብት አለው።"

ነገር ግን ሁኔታው በኃይማኖታዊ ጉዳይ እጅግ የተከፋፈለችውን ሶሪያ ማስተዳደር ወደፊት ለሚመጡ መሪዎች እጅግ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ያሳየ ነው።

ከሶሪያ ሕዝብ አብዛኛው የሱኒ ሙስሊሞች ናቸው። የተቀሩት ደግሞ ክርስቲያኖች፣ አላዋይት እና ኢስማይሊ ናቸው።

የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝደንት ባሽር አል-አሳድን ከሚቃወሙ ሰዎች መካከል ግማሹ ኃይማኖታዊ ያልሆነ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲቋቋም የሚፈልጉ ሲሆን ግማሹ ደግሞ ሀገሪቱ በኢስላማዊ መንገድ እንድትመራ ይሻሉ።

ኤችቲኤስ የተባለው ቡድን በቀደመው ጊዜ ከአል-ቃኢዳ ጋር ግንኙነት የነበረው ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2017 ኢድሊብን ሲቆጣጠር ጠንከር ያለ የሥነ-ምግባር እና የአለባበስ ሕግ አውጥቶ ነበር።

ነገር ግን በተለይ በቅርብ ዓመታት ከሕዝቡ የሚቀርበውን ትችት ተከትሎ እኒህ ሕግጋት እየላሉ መጥተዋል።

በትግል ስሙ አቡ ሞሐመድ አል-ጆላኒ እየተባለ ይጠራ የነበረው አል-ሻራ ባለፈው ሳምንት ደማስቆ አካባቢ ሲዘዋወር ነው ሊያን ያገኛት።

ፎቶ ከመነሳታቸው በፊት ፀጉሯን እንድትሸፍን የሚጠቁም ምልክት ሲያሳያት እሷምት ስትስማማ ይታያል። ቀጥላ የለበሰችው ሹራብን ቆብ አጥልቃ ፎቶ ትነሳለች።

ይህ በማኅበራዊ ሚድያ የተሰራጨው ቪድዮ እና ፎቶ ብዙ ውዝግብ ፈጥሯል።

ወግ አጥባቂ ያልሆኑ ሊበራሎች የአል-ሻራ አገዛዝ ወደፊት ሴቶች ሂጃብ አሊያም ፀጉር የሚሸፍን ስካርፍ እንዲያደደርጉ ሊያስገድድ ይችላል የሚል ትችት ያሰማሉ።

የፍራንስ24 የአረብኛ ጣቢያ ጉዳዩን በተለመከተ ባዘጋጀው ውይይት ላይ "ሶሪያ ወደ ኢስላሚክ አገዛዝ እያመራች ነው ወይ?" ሲል ጠይቋል።

አንድ ሶሪያዊ ጋዜጠኛ "አንድ አምባገነን አባረን ሌላ አምባገነን አመጣን" ሲል ተሰምቷል።

ወግ አጥባቂዎች ደግሞ በቴሌግራም እና በሌሎች ማኅበራዊ ሚድያዎች አል-ሻራ ከአንዲት ሴት አጠገብ ቆሞ ፎቶ ለመነሳት ፈቃደኛ መሆን አልነበረትም ሲሉ ተችተዋል።