ሴሊና ጎሜዝ ስሟ ከዝነኛ ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ተካተተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሴሊና ጎሜዝ ወደ ዝና ማማ የመጣችው ገና ታዳጊ እያለች በባርኒ እና ዲዝኒ ቻናል በኩል ነበር።
አሁን ደግሞ ብዙዎች ስሟን የሚያነሱት ከድምጻዊነቷ ባሻገር ቢሊየነር በመሆኗ ይሆናል።
ሴሊና በደምጻዊነት፣ በተዋናይነት እና በሥራ ፈጣሪነቷ ባስመዘገበቻቸው ስኬቶች የተነሳ ወጣት ቢሊየነር መሆኗ ተዘግቧል።
እንደ ብሉም በርግ ዘገባ ከሆነ የ32 ዓመቷ ተዋናይት እና ድምጻዊት 1.3 ቢሊዮን ዶላር ሀብት በማካበት የዝነኛ ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ስሟ ከአርብ ዕለት ጀምሮ ተካትቷል።
የሀብት ምንጯን ሲገልጽም ከአምስት ዓመት በፊት ያቋቋመችው የመዋቢያ ዕቃዎችን ከሚያመርተው ኩባንያ ጋር የተያያዘ መሆኑ ተጠቅሷል።
ይህ ድርጅትም የ1 ቢሊዮን የአክስዮን ድርሻ አግኝቷል ሲል መጽሔቱ ገምቷል።
ይህ የመዋብያ ቁሳቁሶችን የሚያመርተው ኩባንያዋ ልክ እንደ ቴይለር ስዊፍት እና ሪሃና ሁሉ “በራሳቸው ጥረት ለስኬት ከበቁ ወጣት ሴቶች” መካከል አንዷ አድርጓታል።
'ሬር ቢውቲ' የተሰኘው ይህ ብራንድ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከፍተኛ ስኬትን ያስመዘገቡ የመዋብያ ምርቶችን ያቀርባል።
እስከ የካቲት ወር ባሉት 12 ወራት ብቻ 400 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ሽያጭ ማስመዝገቡም ተጠቅሷል።
ጎሜዝ ከትልልቆቹ ብራንዶች ሊዊ ቫቶን እና ኮች ኤንድ ፑማ ጋር ባላት ስምምነትም በአስር ሺህ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች አስገብታለች ሲል ብሉምበርግ ዘግቧል።
ሴሊና፣ ሁሉ በተሰኘው የፊልም መመልከቻ መተግበርያ ላይ አራት ተከታታይ ምዕራፍ የታየ “ኦንሊ መርደር ኢን ዘ ቢውልዲንግ” በተሰኘው እና ለኤሚ አዋርድ በታጨው ተከታታይ ፊልም “በትንሹ” 6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች።
ብሉምበርግ አክሎም ሴሊና በትወናና እና በሙዚቃ ያላት ስኬት፣ ኤሚና ግራሚ ሽልማቶችን መታጨት ብቻ ሳይሆን ሀብቷም ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል ብሏል።
ቴክሳስ የተወለደችው ሴሊና ላለፉት ሦስት አስርታት በአድናቂዎቿ ዘንድ እንደተወደደች ቆይታለች።
ሴሊና የባይፖላር ዲዝኦርደር እንዲሁም የመከላከል አቅምን በሚያጠቃው “ሉፐስ’ በተሰኙ ሕመሞች ተጠቅታ ነበር።
ቤተሰቦቿ ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ ተሰድደው የመጡት ሴሊና ሙዚቃን በስፓኒሽኛ መስራት የጀመረችው ከአክስቷ ጋር ከመኪና ጀርባ ተደብቀው ነበር።
ድምጻዊቷ ባለፈው ዓመት በኢንስታግራም በርካታ ቁጥር ተከታይ ካላቸው ሴቶች መካከል ቀዳሚዋ ሆና ነበር።
ሴሊና በኢንስታግራም ብቻ 424 ሚሊዮን አድናቂዎች ያሏት ሲሆን ይህም ከቴይለር ስዊፍት እና ከካይሊ ጄነር ቀዳሚ ያደርጋታል።
በኢንስታግራም ባላት የተከታይ ብዛት ከክርስትያኖ ሮናልዶ (638 ሚሊዮን) እና ከሊኦኔል ሜሲ (504 ሚሊዮን) በመቀጠል ሦስተኛዋ ዝነኛ ነች።
ከዓመታት በፊት ከቢቢሲ1 ጋር በነበራት ቆይታ ወጣት ብትሆንም በሙያዋ ላይ ረዥም ጊዜ ስለመቆየት ተናግራ ነበር።
በወቅቱ “ይደንቃል ሁለት አስርታትን ቆየሁ. . . አረጀሁ ማለት ነው” ስትል ነበር የቀለደችው ።
አክላም በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደምትፈልግ ጠቅሳ “ ምን እንደሚገርም ታውቃለህ? . . . ብዙ ጊዜ ገና የጀመርኩ ያህል እንኳ አይሰማኝም” ብላለች።








