በደቦ በደፈሯት ላይ ለማስፈረድ 32 ዓመታትን የጠበቀችው ህንዳዊት

በደቦ ይደፍሩ ከነበሩት ተከሳሾች መካከል የተወሰኑት

የፎቶው ባለመብት, Santosh Gupta

የምስሉ መግለጫ, በደቦ ይደፍሩ ከነበሩት ተከሳሾች መካከል የተወሰኑት

“ልቤ በከፍተኛ ኃዘን እንደተሞላ ነው። ዛሬም ቢሆን ይህንን ህይወቴን ያመሰቃቀለውን ሁነት ሳስብ አለቅሳለሁ” ስትል በደቦ በደፈሯት ላይ ፍትህን ለማግኘት 32 ዓመታትን የጠበቀችው ህንዳዊት ትናገራለች።

ወቅቱ በአውሮፓውያኑ 1992 ነበር።

በወቅቱ አስራ ስምንት ዓመት የነበረችው ሱሽማ አንድ የምታውቀው ግለሰብ ፊልም እንይ በሚል ሽፋን ብዙም ሰው ወደማያዘወትረው መጋዘን ወሰዳት። ስፍራው ላይ ስትደርስ ሰባት ወንዶች አስረው በደቦ ደፈሯት። ድርጊቱ ሲፈጸምም ፎቶ አነሱ።

እነዚህ ወንዶች በምዕራብ ህንድ ግዛት በምትገኘው አጅመር ከተማ አይነኬ፣ኃያል፣ሀብታም እና ስመጥር ግለሰቦች ናቸው።

“ከደፈሩኝ በኋላ አንዱ ሊፒስቲክ እንደገዛበት 200 ሩፒ (2 ዶላር) ሰጠኝ። ገንዘቡን አልወሰድኩም” ብላለች።

ባለፈው ሳምንት ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ ሱሽማን በደቦ የደፈሯት ግለሰቦች የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸዋል።

“አሁን 50 ዓመቴ ነው። በመጨረሻም ፍትህ ያገኘሁ መስሎ ይሰማኛል” ያለችው ሱሽማ አክላም” ነገር ግን ውሳኔው ያጣሁትን ሁሉ ሊተካው አይችልም” ብላለች።

ጥቃት የደረሰባቸውን በሚያሸማቅቅ ባህል ውስጥ ሱሽማም በተፈጸመባት ግፍ እንድታፍር ተደርጋለች። ከማህበረሰቡ ለዓመታት ዘለፋን አስተናግዳለች። የመሰረተቻቸው ሁለት ትዳሮች በደቦ መደፈሯን ሲያውቁ በፍቺ ተጠናቅቀዋል።

በዚያ ዓመት ሱሽማ ብቻ አይደለችም በደቦ የተደፈረችው። በዚህች አጅመር በተሰኘችው ከተማ እነዚህ አይነኬ፣ አድራጊ እና ፈጣሪ እንዲሁም ቱጃር የሆኑ ግለሰቦች በተሰባሰቡበት ቡድን ከተደፈሩ 16 ታዳጊዎች መካከል አንዷ ናት።

እነዚህ ግለሰቦች ታዳጊዎቹን ከመድፈር በተጨማሪ ፎቶዎችን በማንሳት ለማስፈራሪያነት ተጠቅመውበታል። ለወራት የቀጠለው የደቦ መድፈር በከተማዋ ከተከሰቱ ከባድ ቅሌቶች አንዱ ሲሆን ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶበታል።

ታዳጊዎቹን በመድፈር በአጠቃላይ ክስ የቀረበባቸው 18 ግለሰቦች ሲሆኑ ስድስቱ ሱሽማን በመድፈር ባለፈው ሳምንት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ግለሰቦቹ ወንጀሎቹን አልፈጸምንም ሲሉ የካዱ ሲሆን ብይኑንም በከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚሉ ተናግረዋል።

የቀሩት 12 ተከሳሾችስ ምን ሆኑ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአውሮፓውያኑ 1998 ስምንቱ ተከሳሾች የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው። ከእነዚህም ውስጥ አራቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነጻ ያወጣቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ የእስር ቅጣታቸው ወደ 10 ዓመት ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

ከቀሪዎቹ ተከሳሾች አራቱ አንዱ ራሱን አጠፋ፣ አንደኛው በአውሮፓውያኑ 2007 የዕድሜ ልክ እስራት ቢፈረድበትም ከስድስት ዓመታት እስር በኋላ በነጻ ተፈታ።

ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ አንደኛው በተያያዘ ክስ ጥፋተኛ ተብሎ ቢፈረድበትም ነጻ ወጣ፤ እንዲሁም የመጨረሻው ግለሰብ ደግሞ በሽሽት ላይ ይገኛል።

“ይህንን እንዴት ፍትህ ልንለው እንችላለን? ብያኔ ፍትህ አይደለም” ሲል በፍርድ ሂደቱ ወቅት የአቃቤ ህግ ምስክር ሆኖ የቀረበው እና ስለ ጉዳዩ በርካታ ዘገባዎችን የሰራው ጋዜጠኛው ሳንቶሽ ጉፕታ ያስረዳል።

የጋዜጠኛውን ሀሳብ ያንጸባረቁት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ጠበቃ ሬቤካ ጆን በበኩላቸው “የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል” ብለዋል።

“ይህ የሚያመለክተው ችግሩ ከህግ ስርዓቱ እንደሚያልፍ ነው። አባታዊ (ፓትሪያርካል) ስርዓትን የሚከተለው ማህበረሰባችን መሰረታዊ ችግር አለበት። በዋነኝነት ማምጣት ያለበት የአስተሳሰብ ለውጥ ነው። ነገር ግን ይህንን ለውጥ ለማምጣት ምን ያህል ጊዜ ነው መጠበቅ ያለብን” ሲሉ የሕግ ባለሙያዋ ይጠይቃሉ።

ተከሳሾቹ ያላቸውን ስልጣን፣ ገንዘብ እና ተጽዕኗቸውን በመጠቀም ጥቃት እንደፈጸሙ፣ ታዳጊዎቹን እንዳታለሉ እንዲሁም እንዳስፈራሩ አቃቤ ሕግ ቪሬንድራ ሲንግ ራቶሬ ተናግረዋል።

የደፈሯቸውን ታዳጊዎች ዝም ለማሰኘት ሲደፈሩ ያነሷቸውን ፎቶዎች እንዲሁም የቀረጿቸውን ቪዲዮዎች ለማስፈራሪያነት ተጠቅመውበዋቸዋል ሲሉ አክለዋል።

በተጨማሪም አንዳንድ ወንዶችን ጥቃት የሚፈጸምባቸውን ታዳጊዎች እንዲያመጡም ፎቶዎችን ተጠቅመዋል ተብሏል።

በአንድ ወቅት እነዚህ ተከሳሾች አንድ ግለሰብን የአልኮል መጠጥ ጋብዘው ካሰከሩት በኋላ ያልተገባ ነገሮችን ሲፈጽም ፎቶዎችን አንስተው የሚደፈሩ ሴት ጓደኞቹን ካላቀረበ ፎቶዎቹን ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን ብለው እንዳስፈራሩ አቃቤ ህጉ አስረድተዋል። በዚሁ መልክ ደፋሪዎች ሴቶችን መድፈራቸውን መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

ተከሳሾቹ ጠንካራ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ግንኙት የመሰረቱ ነበሩ። በከተማዋ ውስጥ ስመ ጥር ከሆነው የእስልምና እምነት ቅዱስ ስፍራ ከሆነው ‘ዳርጋ’ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ነበራቸው።

“በዚያች አነስተኛ ከተማ ሞተር ሳይክል እየጋለቡ፣ መኪናዎቻቸውን እየነዱ ከተማዋን ያካልሉ ነበር” ይላል ጋዜጠኛው ጉፕታ።

“በከተማዋ የተደበላለቀ ስሜት ፈጥረው ነበር። በአንዳንዶች ይፈራሉ። የተወሰኑት ደግሞ ይህንን ቡድን መቅረብ ሌሎች ደግሞ እነሱን መሆን ይፈልጉ ነበር” ሲል ጋዜጠኛው ያስረዳል።

ለወራት ታዳጊ ሴቶችን በደቦ ሲደፍሩ፣ሲያስፈራሩ እና ሲያሸብሩ ዝም የተባሉትም ከነበራቸው አይነኬነት እና ግንኙነት ነበር ይላል።

ታዳጊዎቹ ሲደፈሩ የሚያሳዩትን ፎቶዎቹን የሚያሳትሙባቸው ፎቶ ቤቶች የሚሰሩ ግለሰቦች እንዲሁም አንዳንድ ፖሊሶች ምን እየተከናወነ እንደነበር ያውቁ እንደነበር ጋዜጠኛው ይገልጻል።

አንድ ቀን ታዳጊዎቹ ሲደፈሩ የሚያሳዩ ፎቶዎች ጋዜጠኛው ደረሰው። ጋዜጠኛው ደነገጠ፣ ሰቀጠጠው።

“የከተማዋ ኃያላን ወንዶች እነዚህ ታዳጊ ሴቶች ላይ አሰቃቂ እና ዘግናኝ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ነበሩ። ነገር ግን ፎቶዎቹ በህዝቡ ላይም ሆነ በፖሊስ ዘንድ የተፈለገውን ያህል ምላሽ አልተገኘባቸውም” ይላል።

ታዳጊዎቹ በእነዚህ ኃያላን ወንዶች በደቦ መደፈራቸውን የሚገልጹ ዘገባዎችን ቢሰራም ይህንን ያህል ትኩረት አላገኙም።

ስለ ታዳጊዎቹ በደቦ መደፈር በአውሮፓውያኑ 1992 የወጣ ዘገባ

የፎቶው ባለመብት, Santosh Gupta

የምስሉ መግለጫ, ስለ ታዳጊዎቹ በደቦ መደፈር በአውሮፓውያኑ 1992 የወጣ ዘገባ

ከዚያም ጋዜጣው በአንድ ወቅት ደፈር ባለ መልኩ ሪፖርቱን ለማውጣት ወሰነ።

እስከ ወገብዋ ድረስ እርቃኗን የነበረች አንዲት ታዳጊ ልጅን ሁለት ጎልማሳ ወንዶች መሃል ላይ አጣብቀዋት ጡቶቿን ሲያሻሹ የሚያሳይ ፎቶን ጋዜጣው ይዞ ወጣ።

አንደኛው ግለሰብ በፎቶው ላይ ፈገግ ብሎ ይታያል። ጋዜጣው ታዳጊዋ እንዳትለይ ፊቷን በማደብዘዝ ነበር ፎቶውን ያተመው።

የፎቶው መውጣት የከተማዋን ነዋሪ በከፍተኛ ሁኔታ አስደነገጠ፣ እንዲሁም አስቆጣ። የተቆጣው ህዝብ ሆ ብሎ ወጥቶ ከተማዋን በተቃውሞ ለቀናት ዘጋት። ቁጣው ከከተማዋ አልፏ ራጃስታን በተሰኘችው ግዛት ተቀጣጠለ።

ቁጣውን ተከትሎ ነበር የአገሪቱ መንግሥት እርምጃ ለመውሰድ የተነሳው።

ፖሊስ በግለሰቦቹ ላይ የመድፈር እና የማስፈራራት ክሶችን እንደመሰረተ አቃቤ ሕጉ ራቶሬ ያስረዳሉ።

ሆኖም የፍርድ ሂደቱ 32 ዓመታትን ያህል ፈጅቷል።

ለዚህም ምክንያቶቹ ተከሳሾቹን በእስር ለማዋል የነበሩ መዘግየቶች፣ የተከሳሾቹ ጠበቆች የፈጠሯቸው የማጉላላት ስልቶች፣ አቃቤ ህግ የገጠመው የገንዘብ እጥረት እንዲሁም በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ የነበሩ መዋቅራዊ ችግሮች እንደሆኑ አቃቤ ሕግ ራቶሬ ይገልጻሉ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ክሱ በቀረበበት በአውሮፓውያኑ 1992 ባለፈው ሳምንት የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው ስድስቱ ሸሽተው ስለነበር አልተከሰሱም።

ይህ ስህተት እንደነበር የሚናገሩት አቃቤ ህጉ ፖሊስ በመጨረሻ በነዚህ ግለሰቦች ላይ ክስ በመሰረተበት በአውሮፓውያኑ 2002ም በሽሸት ላይ ነበሩ።

በመጨረሻም ሁለቱ በአውሮፓውያኑ 2003፣ አንደኛው በ2005፣ ሁለት ተከሳሾች በ2012 እንዲሁም የመጨረሻው ተከሳሽ በ2018 ተይዘዋል።

ከነዚህ ተከሳሾች አንዱ በተያዘ ቁጥር ችሎቱ እንደ አዲስ እየተጀመረ አቃቤ ሕግ ያመጣቸውን ምስክሮች እንደገና የተከሳሽ ጠበቆች ለምስክርነት በድጋሚ ይጠሯቸው ነበር።

“በህጉ መሰረት ምስክሮች በችሎት ላይ ቀርበው ምስክርነታቸውን በሚሰጡበት ወቅት ተከሳሾች በፍርድ ቤት የመቅረብ እንዲሁም ጠበቆቻቸው የመጠየቅ መብት አላቸው” ይላሉ አቃቤ ህጉ ።

ይህም ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሴቶች ካለፉበት መከራ እንዳያገግሙ እና ስቃያቸውን በተደጋጋሚ ለመናገር ተገደዋል።

በአሁኑ ወቅት በ40ዎቹ እና በ50ዎቹ ዕድሜ የሚገኙት ሴቶች ከተደፈሩ ከዓመታት በኋላ ወደ ፍርድ ቤት ለምን ተጠራን በማለት ዳኛው ላይ የሚጮሁ እንደነበሩ አቃቤ ሕግ ራቶሬ ያስታውሳሉ።

ጊዜው እየጨመረ ሲሄድም ፖሊስ ምስክሮችን ለማግኘት ፈታኝ ሆነበት።

አንዳንዶቹም ህይወትን በአዲስ መልኩ ስለጀመሩ ከዚያ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንዳልፈለጉ ያስረዳሉ።

“አሁንም ቢሆን ከተከሳሾቹ አንዱ ሽሽት ላይ ነው። ድንገት በቁጥጥር ስር ከዋለ ወይም በተከሳሾቹ በተሰጠው ብይን ላይ ይግባኝ ቢጠየቅ የተደፈሩት ሴቶች ምስክርነታቸውን እንደገና መስጠት ይጠበቅባቸዋል” ይላሉ።

በስድስቱ ተከሳሾች ላይ የምስክርነት ቃሏን በመስጠት በብያኔው ላይ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት ሶስት ሴቶች መካከል አንዷ ሱሽማ ናት።

“ታዳጊ እና ምንም የማላውቅ ነበርኩኝ። ያለኝን ነገር ነው የነጠቁኝ። አሁን ምንም የማጣው ነገር የለም” ብላለች።

*የህንድ ህግ የተደፈሩ ሰዎችን ማንነት እንዲገለጽ ስለማይፈቅድ ቢቢሲ የተጠቀመው ስም የተቀየረ ነው።