በአማራ ክልል የሱዳን ስደተኞች 'በተቃውሞ' ሁለት መጠለያ ጣቢያዎችን ለቀው መውጣታቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, LUTHERANWORLD
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ከሚገኙ ሁለት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች (ሳይቶች) ከአንድ ሽህ በላይ የሚሆኑ ስደተኞች ‘በአገልግሎትና ደኅንነት ስጋት’ ምክንያት “በተቃውሞ” ለቀው መውጣታቸውን መንግሥት ተናገረ።
የሱዳንን ጦርነት ተከትለው በተመሠረቱት ኩመርና አውላላ በተባሉ መጠለያ ጣቢያዎች 8500 የሚሆኑ ስደተኞች እንደተጠለሉ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ለቢቢሲ ተናግሯል።
ይሁን እንጂ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ስደተኞቹ በደኅንነት ስጋት ምክንያት መጠለያ ጣቢያ ለቀው እየወጡ ነው የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
ስደተኞቹ በበኩላቸው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በታጣቂዎች ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው እና በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎች እንዲሁም ለገንዘብ የሚደረጉ እገታዎች ተደጋጋሚ እየሆኑ በመምጣታቸው መጠለያዎቹን ለቀው ለመውጣት እንደተገደዱ ገልጸዋል።
በአውላላ ጣቢያ ከስድስት ሺህ በላይና በኩመር ደግሞ ሁለት ሺህ 500 ገደማ የሚደርሱ ስደተኞች እንደተጠለሉ ለቢቢሲ የተናገሩት የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽንና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በአካል ንጉሴ፤ ከሰሞኑን የተፈጠረው ሁኔታ “የተቃውሞ እርምጃ” እንደሆነ ጠቁመዋል።
ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን አንስተዋል የተባሉት ስደተኞቹ፤ ‘በቂ አገልግሎት እያገኘን አይደለም እና የደኅንነት ስጋት አለብን’ በሚል ሚያዚያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ጣቢያዎችን ለቀው መውጣታቸው ተነግሯል።
“ ‘በቂ አገልግሎት እያገኘን አይደለም፤ በዚህ ምክንያት ተቸግረናል፤ በችግር ውስጥ ላይ ነን ያለነው፤ መኖር አልቻልንም’ ሚል ጥያቄ አላቸው። ሁለተኛ የተለያዩ ክስተቶች አሉ። በእነዛ ምክንያት የደኅንነት ስጋት ተሰምቶናል የሚል፤ ለምሳሌ አልፎ አልፎ የጥይት መተኮስ አለ፤ ስርቆቶች አሉ። ይሄ ይሄ ስጋት አሳድሮብናል የሚል መነሻ አላቸው” ሲሉ ስለተፈጠረው ሁኔታ ማብራሪያ ይሰጣሉ።
ስደተኞቹ “እንደ ተቃውሞ” በአንድ ቀን ጣቢያዉን ለቀው አንድ ኪ.ሜ ተኩል ገደማ ወደ ከተማ [ወደ ጎንደር] መሄዳቸውን አቶ በአካል ተናግረዋል።
ሚያዚያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ሌሊት ላይ “ተነጋግረው” የወጡት ስደተኞች ቁጥር ከአንድ ሽህ እንደሚበልጥ የተናገሩት ኃላፊው “የተወሰኑት” ከሚመለከታቸው አካላት ጋር “በንግግር” መመለሳቸውን ገልጸዋል።
“በአንድ ቀን እንደ ተቃውሞ ነው፤ ተነጋገሩ ‘ችግሮች አሉብን ለቀን እንወጣለን’ አሉ። ሌሊት ላይ ተነሱ አንድ ኪ.ሜ፤ አንድ ኪ.ሜ ተኩል አካባቢ የሚሆን ከሳይታቸው ወጥተው ሄዱ። ከዛ የሚመለከታቸው አካላት አናገሯቸው፤ ሲያናግሯቸው የተወሰኑት አምነውበት ተመለሱ” ሲሉ ስለሁኔታው አብራርተዋል።
“20 ቤተሰቦችና ስምንት ግለሰቦች” “ከንግግሩ” በኋላ መመለሳቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።
በአካባቢው 25 ሽህ የሚሆኑ ስደተኞች ተጠልለው እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ በአካል፤ ኢትዮጵያ ጥበቃና ከለላ ብቻ እንደምትሰጥ ገልጸዋል።
ምግብ፣ ጤናና ትምህርትን ጨምሮ ሰብዓዊ አቅርቦቶችን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደሚያቀርብ የተናገሩም ሲሆን ድጋፉ “መቀዛቀዙን” ተናግረዋል።
“የሚደረገው ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ አጠቃላይ የጥበቃ ሥራዎችን ለመሥራት ችግሮች ገጥመውናል። ያለው ፈንድ አነስተኛ በመሆኑ፤ በጀቱ አነስተኛ በመሆኑ በሙሉ አቅም የጥበቃ ሥራዎችን መሥራት አልተቻለም። በዚህ ምክንያት የሚከሰቱ ክስተቶች አሉ” ብለዋል።
ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚደረገው ድጋፍ “የለም” የሚባልበት ደረጃ ነው ያሉም ሲሆን፤ ይህም አጠቃላይ የከለላና ጥበቃ ሥራው ላይ ተጽዕኖ ስለማሳረፉ ገልጸዋል።
ሁለቱ መጠለያ ጣቢያዎቹ ባለመልማታቸው በአካባቢው መግቢያና ጊዜያዊ ማቆያዎች ላይ በሺዎች የሚሆኑ ስደተኞች እንደተጠለሉ ተናግረዋል።
የስደተኞቹ ጥያቄ ወደ ሌላ አገር መቋቋምን እንደሚጨምር ያነሱት የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የኮሙኒኬሽንና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በአካል ንጉሴ፤ ኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄዎቻቸውን ለመፍታት “ከአጋር አካላት ጋር እየተነጋረ ነው” ብለዋል።
የደኅንነት ስጋትን በሚመለከት በመንግሥት በኩል የፌደራል ፖሊስን ጨምሮ የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው እንዲሰማሩ በማድረግ ጥበቃ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በደረሱባቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት ከመጠለያ ጣቢያዎች ለቀው የወጡና ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሱዳናውያን ስደተኞች እርዳታ እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ተማጽነዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን፣ ስደተኞቹ ከመጠለያ ካምፖች ለቀው መውጣታቸው “እጅግ እንዳሳሰበው” ለቢቢሲ ገልጿል።
ከአውላላ ካምፕ “ወደ ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች ለቀው መውጣታቸውን” እንዲሁም ከኩመር ካምፕ “ቢያንስ 300 ገደማ ስደተኞች ለቀው መውጣታቸውን” ለቢቢሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
“በተደጋጋሚ የፀጥታ ችግሮች ማጋጠማቸው እንዲሁም ወንጀል፣ ዝርፊያ፣ በመሣሪያ የታገተ ዝርፊያ እና እገታ ሪፖርት መደረጉን ተከትሎ ነው ስደተኞቹ የወጡት” ሲልም አክሏል።












