በጥቃቶች ምክንያት ከአማራ ክልል የተመድ መጠለያ ጣቢያዎች ለቀው የወጡ የሱዳን ስደተኞች እርዳታ እንዲደረግላቸው ተማጸኑ

የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, Fana Broadcasting Corporation

በደረሱባቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ከሚገኙ ሁለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መጠለያ ጣቢያዎች ለቀው የወጡ ሱዳናውያን ስደተኞች እርዳታ እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ተማጸኑ።

ኩመር እና አውላላ ከተሰኙት የተመድ መጠለያ ጣቢያዎች ለቀው የወጡ ስደተኞች ቁጥር 7 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ቢቢሲ ዛሬ ሚያዝያ 30/ 2016 ዓ.ም በስልክ ያናገራቸው ሶስት ስደተኞች ተናግረዋል።

ቢቢሲ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ በገለልተኝነት ማረጋገጥ አልቻለም።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ክስተቱን አስመልክቶ ለቢቢሲ ምላሽ ባይሰጥም ከተደጋጋሚ የጸጥታ ችግሮች በኋላ ስጋት የተሰማቸው 1 ሺህ ስደተኞች ከኩመር ካምፕ ሸሽተው መሄዳቸውን እንደሚያውቅ መናገሩን ሮይተርስ ጠቅሷል።

ስደተኞቹ በአካባቢው ሚሊሻዎች ጥቃት እና ዝርፊያ ከተፈጸመባቸው በኋላ በመጠለያው ከነበሩት 8 ሺህ ስደተኞች መካከል 7 ሺህ የሚሆኑት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ማለዳ ካምፑን ለቀው በእግራቸው መሸሻቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ስደተኞቹ ሸሽተው ከለላ ለማግኘት ከመጠለያ ጣቢያዎቹ ውጭ በዋና ጎዳና ላይ ላይ እና በአቅራቢያዎቹ በሚገኝ ትንሽ ከተማ ፓሊስ ጣቢያ አጠገብ ለቀናት ማደራቸውን ተናግረዋል።

እርዳታ እንዲደረግላቸው እየተማጸኑ ያሉት ስደተኞች ከመንግሥት እና ከተባበሩት መንግሥታት ምንም አይነት ዘላቂ መፍትሄ አለማግኘታቸውን አንድ ስደተኛ ዛሬ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

“እርዳታ እንፈልጋለን። የመጣነው ችግርን ሸሽተን ነው። አሁን ደግሞ ሌላ ችግር እየገጠመን ነው” ሲሉም ተማጽነዋል።

ስደተኞቹ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በታጣቂዎች ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው እና በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎች እንዲሁም ለገንዘብ የሚደረጉ እገታዎች ተደጋጋሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

የመጠለያ ጣቢያዎቹን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ሌሊት ላይ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር አንድ ስደተኛ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

“በድንኳኔ [መጠለያዬ] ብቆይ ምናልባት መጥተው በጥይት ሊመቱኝ ይችላሉ። አደጋ እንደተጋረጠብኝ ስለተሰማኝ እንቅልፍ መተኛት አልቻልኩም። ስፍራው ሌሊት ላይ በጣም አደገኛ ስለሆነ እዚያ መቆየት አይቻልም” ብለዋል።

ስለ ጉዳዩ ቢቢሲ ማብራሪያ የጠየቃቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ ጌቱ ስደተኞች ከመጠለያ ጣቢያ አለመውጣታቸውን ሰኞ ዕለት ተናግረው ነበር።

አቶ አንዳርጌ የወጣውን ዘገባ አስተባብለው “ወጥቶ የሄደ ስደተኛ የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“ከበዓል በፊት ወደ ጎንደር እንሄዳለን የሚል አዝማሚያ ነበራቸው። የፀጥታ መዋቅሩ ሄዶ አነጋገሯቸው ችግሩ ተፈቶላቸዋል” ሲሉም ገልጸዋል።

ስደተኞቹ ጥያቄያቸው የነበረው “ከረጂ ድርጅቶች የምግብ አቅርቦትና ስርጭት እንዲሁም ከውሃ ጋር ተያይዞ ችግር አለ የሚል እንጂ በፀጥታ ጉዳይ አይለም” ብለዋል።

በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር ሁሉም አካባቢ ቢሆንም መጠለያ ካምፑ “በልዩ ሁኔታ በተቻለው መጠን ከፌደራል ፖሊስም በአካባቢው ሚሊሻም ደኅንነቱ ይጠበቃል” ብለዋል።

ሆኖም ግን ከካምፕ ወጥተው “ለሕገ ወጥ የሰው ዝውውር የሚጋለጡ” ባሏቸው ስደተኞች ላይ “እገታና ዘረፋ ሊኖር ይችላል” ብለዋል።

አያይዘውም “ካምፕ ላይ ሄዶ ግን የሰፈረውን ስደተኛ የሚረብሽ የፀጥታ ሁኔታ የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በኩመር መኖሪያቸውን ያደረጉ ሱዳናውያን ስደተኞች ገንዘብ ክፈሉ በሚል መታገት፣ ግድያ እና በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎችን የመሳሰሉ ለወራት ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ችግር እንደገጠማቸው ለተባበሩት መንግሥታት በቅርቡ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ሮይተርስ ገልጿል።

“ወንጀሎች፣ በትጥቅ የታገዙ ዝርፊያዎች፣ ተኩስ እና እገታዎችን ጨምሮ በርካታ የጸጥታ ጉዳዮች ሪፖርቶችን ተከትሎ ነው ስደተኞቹ ጥለው የሸሹት” ብሏል የተባበሩት መንግሥታት።

የኩመር እና አውላላ መጠለያ ጣቢያዎች በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን ከመተማ በ70 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አሉበት።

መተማ ከሱዳን ለሚመጡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ዋና መዳረሻ ከተማ ስትሆን የኩመር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከአቅሙ በላይ ተጨናንቆ እንደሚገኝ ከጥቂት ወራት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ( ዩኤን ኦቻ) ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።

በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች እና መከላከያ እያደረጉት ባለው ግጭት የስደተኞቹ ህይወት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።

በሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በጦሩ መሪ መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከ1.6 ሚሊዮን ሱዳናውያን መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

ከነዚህም ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው ገብተዋል።