ሱዳናውያን ስደተኞች በተፈጸሙባቸው ጥቃቶች በአማራ ክልል ከሚገኘው የተመድ መጠለያ ጣቢያ ለቀው መውጣታቸው ተነገረ

ኩመር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, lutheranworld

ቢያንስ 1 ሺህ የሚሆኑ ሱዳናውያን ስደተኞች በተፈጸሙባቸው ተከታታይ ጥቃቶች የተነሳ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ከሚገኘው ኩመር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለቀው መውጣታቸው ተነገረ።

ስደተኞቹ በተደጋጋሚም እንደተዘረፉ፣ መታገት እና ሌሎች ጥቃቶችን እንዳስተናገዱ ሮይተርስ ሶስት ስደተኞችን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽንን ዋቢ አደርጎ ዘግቧል።

ስደተኞቹ እንደተናገሩት በአካባቢው ሚሊሻዎች ጥቃት እና ዝርፊያ ከተፈጸመባቸው በኋላ በመጠለያው ከነበሩት 8 ሺህ ስደተኞች መካከል 7 ሺህ የሚሆኑት ረቡዕ ማለዳ ካምፑን ለቀው በእግራቸው መሸሻቸውን ተናግረዋል።

ከሱዳን ድንበር በ70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የስደተኞች መጠለያ ለቀው እንደሸሹ በፖሊስ መያዛቸውን መናገራቸውን ሮይተርስ በዘገባው አስፍሯል። ስደተኞች ይደርስብናል ያሉትን የአጸፋ ምላሽ በመፍራት ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን በበኩሉ ከተደጋጋሚ የጸጥታ ችግሮች በኋላ ስጋት የተሰማቸው 1 ሺህ ስደተኞች ከኩመር ካምፕ ሸሽተው መሄዳቸውን እንደሚያውቅ መናገሩን ሮይተርስ ጠቅሷል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የአማራ ክልል አስተዳደር፣ የፌደራል ፖሊስ እና የስደተኞች ኤጀንሲ ቃለ አቀባዮችን ለማድረግ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳከለትም ሮይተርስ በዚህ ዘገባው አስነብቧል።

ስለ ጉዳዩ ቢቢሲ ማብራሪያ የጠየቃቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ ጌቱ ስደተኞች ከመጠለያ ጣቢያ አለመውጣታቸውን ተናግረዋል።

አቶ አንዳርጌ የወጣውን ዘገባ አስተባብለው “ወጥቶ የሄደ ስደተኛ የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ከበዓል በፊት ወደ ጎንደር እንሄዳለን የሚል አዝማሚያ ነበራቸው። የፀጥታ መዋቅሩ ሄዶ አነጋገሯቸው ችግሩ ተፈቶላቸዋል” ሲሉም ገልጸዋል።

ስደተኞቹ ጥያቄያቸው የነበረው “ከረጂ ድርጅቶች የምግብ አቅርቦትና ስርጭት እንዲሁም ከውሃ ጋር ተያይዞ ችግር አለ የሚል እንጂ በፀጥታ ጉዳይ አይለም” ብለዋል።

በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር ሁሉም አካባቢ ቢሆንም መጠለያ ካምፑ “በልዩ ሁኔታ በተቻለው መጠን ከፌደራል ፖሊስም በአካባቢው ሚሊሻም ደኅንነቱ ይጠበቃል” ብለዋል።

ሆኖም ግን ከካምፕ ወጥተው “ለሕገ ወጥ የሰው ዝውውር የሚጋለጡ” ባሏቸው ስደተኞች ላይ “እገታና ዘረፋ ሊኖር ይችላል” ብለዋል።

አያይዘውም “ካምፕ ላይ ሄዶ ግን የሰፈረውን ስደተኛ የሚረብሽ የፀጥታ ሁኔታ የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“በተለይ ኤርትራውያን በካምፕ መኖር አይፈልጉም” ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው፣ “ከካምፕ ወጥተው ከሕገ ወጥ የሰው ዝውውር ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ ደላላዎች ወደተለያየ አካባቢ ለመሸኘት ሲሞክሩ በዚያ መሃል ማገት ይኖራል” ብለዋል።

ጨምረውም “እንደማንኛውም የዘረፋና እገታ ወንጀል የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው። እነሱን ዒላማ ያደረገ ልዩ እገታና ዘረፋ ካምፕ ላይ ያን ያህል የለም” ብለዋል።

የኩመር መጠለያ ጣቢያ በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን ከመተማ በ70 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ወደ 10 ሺህ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አሉበት።

መተማ ከሱዳን ለሚመጡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ዋና መዳረሻ ከተማ ስትሆን የኩመር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከአቅሙ በላይ ተጨናንቆ እንደሚገኝ ከጥቂት ወራት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ( ዩኤን ኦቻ) ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።

ስደተኞቹን አውላላ ወደተሰኘ ስፍራ ለማዛወር እየተሰራ እንደሆነ ዩኤን ኦቻ ሆኖም በከልሉ ያለው የጸጥታ ችግር በማዘዋወር ስራው ላይ ከፍተኛ ተግዳሮቶችን መፍጠሩ ተነግሯል።

በኩመር መኖሪያቸውን ያደረጉ ሱዳናውያን ስደተኞች ገንዘብ ክፈሉ በሚል መታገት፣ ግድያ እና በትጥቅ የታገዙ ዘረፋዎችን የመሳሰሉ ለወራት ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ችግር እንደገጠማቸው ለተባበሩት መንግሥታት በቅርቡ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ሮይተርስ ገልጿል።

በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች እና መከላከያ እያደረጉት ባለው ግጭት የስደተኞቹ ህይወት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።

“ከእንግዲህ በዚህ መጠለያ መቆየት አንችልም። በሰኔ ወር እዚህ ከመጣን ጀምሮ ታግተናል፣ ተገድለናል በተደጋጋሚም ጥቃቶች ደርሰውብናል። ጦርነት ቢኖርም ወደ ሱዳን ለመመለስ ወስነናል” ሲል ሮይተርስ ያናገረው አንድ ስደተኛ ተናግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመጠለያው ውስጥ ያለውን ሁኔታ “በጣም አስቸጋሪ” ሲል የገለጸው ሲሆን ስደተኞቹ የየሸሹትም ደህንነት ስላልተሰማቸው ነው ማለቱን ሮይተርስ የተመድን መግለጫ ዋቢ በማድረግ አስፍሯል።

“ወንጀሎች፣ በትጥቅ የታገዙ ዝርፊያዎች፣ ተኩስ እና እገታዎችን ጨምሮ በርካታ የጸጥታ ጉዳዮች ሪፖርቶችን ተከትሎ ነው ስደተኞቹ ጥለው የሸሹት” ብሏል የተባበሩት መንግሥታት።

በሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በጦሩ መሪ መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከ1.6 ሚሊዮን ሱዳናውያን መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

ከነዚህም ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው ገብተዋል።