በግሪክ የተከሰተው የሰደድ እሳት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን አፈናቀለ

ሮድስ ደሴት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በግሪክ ሮድስ ደሴት ላይ በተነሳው የሰደድ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው ሸሹ።

በርካቶቹንም ከቤታቸው እና ከሆቴላቸው ደህንታቸው ወደተጠበቁ ስፍራዎች ማዛወር መቻሉም ተገልጿል።

እሳቱም በበርካታዋ የደሴቷ ስፍራ ተዛምቷል ተብሏል።

የግሪክ የእሳት አደጋ መከላከያ ሚኒስቴር በደሴቲቱ ለደረሰው ችግር ይቅርታ ጠይቆ በአየር ሁኔታው ምክንያት ከዚህም ሊብስ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

እስካሁን ከ3ሺህ 500 በላይ ሰዎችን በየብስ እና ባህር ትራንስፖርቶች ማስወጣት እንደተቻለም ገልጿል።

በተጨማሪም 1 ሺህ 200 ነዋሪዎችን ፒፍኪ፣ ሊንዶስ እና ካላቶስ ከተሰኙ ሶስት መንደሮች እንዲወጡ ይደረጋል ተብሏል።

በግሪክ የአየር ንብረት ቀውስ እና የሲቪል ጥበቃ ሚኒስቴር ጉዳት ሪፖርት እንዳልተደረገለት ያለውን መረጃ አጋርቷል።

በተጨማሪም ደሴቲቷን ሊጎበኙ የመጡ ጎብኚዎችንም ወደ ሌሎች ሆቴሎች እየተዘዋወሩ ይገኛሉ።

የሄለኒክ የእሳት አደጋ ኮርፖሬሽን ቃለ አቀባይ ሌተናል ኮሎኔል ያኒስ አርቶፖዮስ በአሁኑ ወቅት የተነሳው የሰደድ እሳት ተቋሙን ካጋጠመው ፈታኙ ሊባል እንደሚችልም ተናግረዋል።

አውሮፓ በከፍተኛ የሙቀት ማዕበል እየታመሰች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ደሴቲቱ በአውሎ ንፋስ ምክንያት እየተዛመተ ካለው የሰደድ እሳት ጋርም እየታገለች ትገኛለች።

በአካባቢው የተነሳውንም እሳት ለመቆጣጠር አምስት ሄሊኮፕተሮች እና 173 የእሳት አደጋ ሰራተኞች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

በኪዮታሪ አካባቢ ሶስት ሆቴሎች በእሳት ተጎድዋል።

እንዲሁም ላየርማ፣ ላርዶስ እና አስክሊፒዮ የተሰኙትም ስፍራዎች እሳቱ ደርሶባቸዋል።

ከደሴቲቱ በስተምስራቅ በሚገኙ የባህር ዳርቻ የነበሩ ሰዎችንም ለማንሳት የግሪክ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎችና ጀልባዎች እየተባበሩ ይገኛሉ። በቱሪስቶች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያለው የግሪክ የባህር ኃይል መርኮቦችም ወደ ስፍራው አቅንተዋል።