ታዋቂው ተዋናይ ጄሚ ፎክስ "በቤተሰብ እርዳታ ከሕመሙ እያገገመ እንደሆነ" ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ ጄሚ ፎክስ ከሕመሙ እያገገመ እንደሆነና በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚመለስ ገልጿል።
ፎክስ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መባቻ በገጠመው ሕመም ምክንያት ሆስፒታል ገብቶ ነበር።
ባለፈው ሚያዝያ ልጆ ኮሪን ፎክስ አባቷ “ሕመም ላይ እንዳለ” ብትናገርም ቤተሰቡ ምን እንዳመመው ይፋ ሊያደርግ አልፈቀደም።
ፎክስ ቅዳሜ በኢንስታግራም ገፁ በለጠፈው መልዕክት ቤተሰቡ የበሽታውን ጉዳይ “ሸሽገው” በመያዛቸው ምስጋና አቅርቧል።
ከሆስፒታል ከወጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊቱ የታየው ጄሚ ፎክስ የማሕበራዊ ሚድያ ተከታዮቹ ለሰጡት ብርታት ምስጋና ለግሷል።
ምንም እንኳ በርካታ አድናቂዎቹ ስለገጠመው ሕመም ማወቅተ ቢሹም “ቱቦዎች ተገጥመውብኝ ልሙት ልኑር ሳላውቀው እንድታዩኝ አልሻትኩም” ሲል ለምን ጉዳዩን እንደሸሸገው ተናግሯል።
“እኔ ስስቅ እንድታዩኝ ነው የምሻው። ስጨፍር፣ ስደሰት፣ ስቀልድ፣ ፊልም ሥሠራ” ብሏል ፎክስ።
“ሕይወቴን ያዳኑልኝ እሕቴ ዴይድራ ዲክሰን እና ልጄ ኮሪን ናቸው” ያለው የ55 ዓመቱ ተዋናይ ለቤተሰቡ፣ ለፈጣሪ፣ ለሕክምና ሰዎች ከፍ ያለ ምስጋና አቅርቧል።
ባለፈው ግንቦት ልጁ ኮሪን አባቷ ከሆስፒታል ከወጣ ሳምንታት እንዳለፉት ገልጣ ጥሩ ማገገም ላይ እንዳለ ተናግራ ነበር።
ተዋናዩ በጆርጂያ ግዛት አትላንታ ከተማ ለኔትፍሊክስ ‘ባክ ኢን አክሽን’ የተሰኘ ፊልም ከሙያ አጋሩ ካሜረን ዲያዝ ጋር እየሠራ ሳለ ነው ሆስፒታል እንደገባ የተነገረው።
ለወዳጁ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ በለለቀው ቪድዮ “ሲዖል ደርሶ እንደተመለሰ” የሚናገረው ፎክስ “ከሕመም ማገገም ቀላል እንዳልሆነ” ያስረዳል።
ቢሆንም “እየተመለስኩ ነው። አሁን ሥራ መሥራት እችላለሁ” ብሏል።
በርካታ ታዋቂ ሰዎች ጄሚ ፎክስ ከሕመሙ በማገገሙ የተሰማቸውን ደስታ እየገለጡ ይገኛሉ።
ከእነዚህ መካከል “በእውነት ስላየሁህ ደስ ብሎኛል” ያለው ኢድሪስ ኤልባ እና “ፈጣሪ ይመስገን’ ስትል የኮመተችው ቫዮላ ዴቪስ ይገኙበታል።
ጆን ቦየጋ እና ትሬሲ ኤሊስ ሮስ የተሰኙት ጥቁር የሆሊውድ ፈርጦችም በሙያ አጋራቸው ማገገም የተሰማችን ደስታ አሳውቀዋል።
ዘይ ክሎንድ ታይሮን የተሰኘው ጄሚ ፎክስ የተሳተፈበት አዲስ ፊልም በኔትፍሊክስ ተለቋል።
በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ከ29 ዓመቷ ተዋናይት፣ ሞዴልና ማሕበረሰብ አንቂ ልጁ ኮሪን ጋር በመጣመር ሙዚቃ ላይ ያተኮረ የቲቪ ፕሮግራም እንደሚያዘጋጅ ይጠበቃል።
የኦስካር አሸናፊው ጄሚ ፎክስ በሆሊውድ አሉ ከሚባሉ ጥቁር አሜሪካዊያን ተዋናዮች አንዱ ነው።












