ከፀረ-ዜሌንስኪ የካርቱን ፊልሞች ጀርባ ያለው ምሥጢር ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, ukraine-inc.info
ለዩክሬን የሚሰጠው ወታደራዊ እርዳታ አውሮፓውያንን የበለጠ እያደየኸ መሆኑን ከሚያሳዩ ፀረ-ዜሌንስኪ ካርቱኖች ጀርባ የፈረንሳውያን እጅ እንዳለበት የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን እየገለጹ ነው። ቢቢሲ ያገኛቸው መረጃዎች ግን ከካርቱኖቹ ጀርባ የሩሲያ እጅ የመኖሩ ዕድል ከፍተኛ መሆኑን ያሳያሉ።
ፓሪስ የገና ዋዜማ ዕለት። ልጆች የሚሰጣቸውን ስጦታ እያለሙ ወደ አልጋቸው እያቀኑ ነው። የዘንድሮው በዓል ግን ለየት ያለ ነበር። ስጦታ የሚሰጡት የገና አባት የተለመደውን ቀይ ልብስ ከመጎናጸፍ ቢጫና ሰማያዊ ቀልም ያለውን ልብስ መርጠዋል።
ከረዥሙ ነጭ ጢም ጀርባ ያሉት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪን መሆናቸውን በቀላሉ መለየት አያስቸግርም። ኮቴያቸው እንዳይሰማ ቀስ ብለው የገናን ዛፉ ሥር ወደ ተደረደሩት የልጆቹ ስጦታዎች ይጠጋሉ። መርጠውም የሚወዱትን ብቻ ለይተው ይሰርቃሉ - ወታደራዊ አውሮፕላኖችን። ልጆቹ ያለቅሳሉ።
እነዚህን የሚመስሉ ትዕይንቶች ፀረ-ዜሌንስኪ በሆነው “ዩክሬን ኢንክ” በተሰኘው ተከታታይ አኒሜሽን ላይ ይቀርባሉ። የመጀመሪያው ክፍል በ2023 ukraine-inc.info የተሰኘው ድረገጽ ላይ ታትሟል። ከዚያ ወዲህም አዳዲስ ክፍሎች በየጊዜው እየተለቀቁ ነው።
እጥር ምጥን ተደርገው ከ1.5 አስከ 3 ደቂቃ ይቀርባሉ። “ሪዶቭካ” የተሰኘ እና ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የቴሌግራም ተከታዮች ያሉት ቻናል የሩሲያ መንግሥትን በመደገፍ ይታወቃል። ይህ ቻናል ፊልሞቹን ማጋራቱን ተከትሎ ቪዲዮዎቹ ከፍተኛ ተመልካች ማግኘት ጀምረዋል።
“ሪዶቭካ” እና ሌሎች የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ከፊልሞቹ ጀርባ የፈረንሳውያን እጅ አለበት ይላሉ።
ይህንን የሚያረጋግጥ ነገር ግን ቪዲዮዎቹ ውስጥ የለም። ቢቢሲ እነዚህን ፊልሞች የሚሠራቸው ማን ነው የሚለውን ለማወቅ ሙከራ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Telegram channel "Readovka"
ቪዲዮዎቹን ማን ነው የሚያሰራጫቸው?
የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮዎቹ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሰራጩ የረዳው ማነው?
ukraine-inc.info የሚለውን ድረገጽ ማን እንዳስመዘገበው የሚገልጽ መረጃ የለም።
የመጀመሪያውን ክፍል በድረ-ገጹ ላይ በተለቀቀበት ዕለት በፍጥነት ያስተዋወቀው የክሬምሊን የሚዲያ ተቋም ሆነው አርአርኤን ነበር። አርአርኤን ወይም “ረሊያብል ሪሰንት ኒውስ" ቀደም ሲል “ረሊያብል ሩሲያን ኒውስ” በመባል ይታወቅ ነበር።
በአሥር የተለያዩ ቋንቋዎች መረጃዎችን ያቀርባል። “ገለልተኛ” መገናኛ ብዙኃን እንደሆነ ይገልጻል። በውጭ አገር በሚገኙ የሩሲያ ኤምባሲዎችም በተደጋጋሚ ይጠቀሳል።
ድረ-ገጹ ይፋ ከሆነ በኋላ በንቃት ካስተዋወቁት ሚዲያዎች መካከል በሩሲያ መንግሥት የሚተዳደረው “ራዲዮ ስፑትኒክ”፣ በ12 ቋንቋዎች የሚሰራጨው እና ክሬምሊንን የሚደግፈው “ኒውስ ፍሮንት” እና በደርዘን የሚቆጠሩ የሩሲያኛ ተናጋሪ የቴሌግራም ቻናሎች ይገኙበታል።
ቢያንስ ዘጠኝ በሚሆኑ የሩሲያ ምክር ቤቶች ኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገጾች ላይም ተጋርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, ukraine-inc.info
በ‘ፈረንሳይ’ እና ሩሲያን በሚደግፉ ፊልሞች መካከል ያለው መመሳሰል
“ዩክሬን ኢንክ” የተሰኘው ተከታታይ ፊልም ሴራ የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን የፕሮፓጋንዳ ትረካዎችን የሚያስተጋባ ይመስላል።
በዚህም ዩክሬን “በናዚዎች" ቁጥጥር ሥር መሆኗን እና ዜሌንስኪ ደግሞ “የምዕራባውያን አሻንጉሊት” እና ለግል ትርፋቸው ሲሉ ዩክሬናውያንን ወደ ጦር ግንባር የሚልኩ ተደርገው ይሳላሉ።
ቢቢሲ እያንዳንዱን የፊልሙን ክፍል ተንትኗል። በአንዳንዶቹ ላይ የፓሪስ ጎዳናዎች ተደበላልቀው ጥቅም ላይ ውለዋል ወይም ሙሉ ለሙሉ የፈጠራ ስሞች ናቸው። የፈረንሳይኛ ቃላትም በተሳሳተ መንገድ ተጽፈው የተገኙበት አጋጣሚዎች አሉ።
በአንዱ ክፍል ደግሞ የኔቶ አባል አገራት በአይጥ ተመስለዋል። ከአባልነታቸው መውጣታቸውን ለማሳየትም ከሚሰምጥ መርከብ ሲሸሹ ይታያሉ።
አይጦቹ የተለመዱ ይመስላሉ።
በ2022 በምዕራብ አፍሪካ በስፋት በተሰራጨ ሌላ የካርቱን ቪዲዮ ላይ ተመሳሳይ አይጦች መታየታቸውን ቢቢሲ ተመልክቷል። በእነዚያ ቪዲዮዎች ላይ አይጦች ፈረንሳዮችን የወከሉ ሲሆን፣ ከአካባቢው ሰዎች ሲሰርቁ እና ትርምስ ሲፈጥሩ ይታያል።
ቪዲዮው በቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች በበርካታ ግጭቶች ውስጥ የተሳተፈውን የሩሲያ ቫግነር ቅጥረኛ ቡድንን ለማስተዋወቅ የተሠራ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Anonymous
ፕሮፓጋንዳውን ቪዲዮ እንዲያነጻጽሩ ሦስት ፕሮፌሽናል አኒሜተሮችን ቢቢሲ ጠይቋል።
“በዩክሬን ኢንክ” እና ቫግነርን በመደገፍ በተሠሩት ቪዲዮዎች ውስጥ አይጦቹን ለመሥራት ተመሳሳይ አካሄድ ጥቅም ላይ መዋሉን ሁሉም ተስማምተዋል።
መቀመጫቸውን በለንደን ያደረጉት አኒሜተሩ ፖል ስቶን “በሁለቱም ቪዲዮዎች ትንሽ የንድፍ ማስተካከያ አድርገዋል” ብለዋል። ስቱዲዮው አጭር ጊዜ እና አነስተኛ በጀት ሲኖረው ይህ የተለመደ አሠራር መሆኑንም አክለዋል።
ቢቢሲ የአይጦቹን የመጀመሪያ ምስል በሽያጭ ከሚቀርቡባቸው ድረገጾች ላይ አግኝቷል። ንድፉን የሠራው ለቢቢሲ ጥያቄ ምላሽ ባልሰጠ ሩሲያዊ ግራፊክ ዲዛይነር ነው።
በሲድኒ የአኒሜሽን ስቱዲዮ ባለቤት የሆኑት ቤን ማርዮት ደግሞ “ተመሳሳዩን ንድፍ እንደ መነሻ መጠቀማቸው የማይካድ ነገር ነው” ብለዋል።
አይጦቹ አንድ ዓይነት አይመስሉም። ምክንያቱም ጅራታቸው እና የታችኛው መንጋጋቸው ለእንቅስቃሴ እንዲመች ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል።
ነገር ግን በእነዚህ ሁለት ቪዲዮዎች ውስጥ ያሉ ሌሎች ገጽታዎች አይመሳሰሉም። መነሻው ምሥል በቀላሉ የሚገኝ በመሆኑ ሁለቱም ካርቱኖች በአንድ አርቲስት ወይም ስቱዲዮ ተሠርተዋል ማለት አይቻልም ብለዋል።
ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ ገለልተኛ ሩሲያዊ የካርቶን ቪዲዮዎች ባለሙያ ሌሎች ተመሳሳይነቶች እንዳሉም ያምናል።
“መስመሮች የሚሠሩበት መንገድ፣ የክፍሎቹ ሁኔታ እና ሌሎችም ግልጽ ያልሆኑ ቴክኒኮች ናቸው። ይህ አዘጋጁ ዘይቤ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው። ይህንን ግን በፍጹም እርግጠኛነት መናገር አንችልም” ብለዋል።

ለምን ፈረንሳይ?
ክሬምሊን የፕሮፓጋንዳ ሥራዎችን ከፈረንሳይ ጋር ስታገናኝ የመጀመሪያዋ አይደለም። እአአ በ2022 የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሆነው ቻናል አንድ “ስቶፕ ናዚ ጌምስ [የናዚ ጨዋታዎችን አቁም]” በሚል ርዕስ ሌላ ፀረ-ዜሌንስኪ ቪዲዮ አቅርቧል። ቪዲዮው “ባራራኩዳስ” በተባለ ገለልተኛ የፈረንሳይ ስቱዲዮ የተሠራ ነው በሚል በተለያዩ ድረ-ገጾችም ተሰራጭቷል።
ይህ ስቱዲዮ በበይነ መረብ ላይ ስለመኖሩ ግን ምንም መረጃ ሊገኝ አልተቻለም።
ቪዲዮው የፈረንሳይ ከመሆን ይልቅ የአርመን ሥሪት ሊሆን ይችላል። ከአርሜኒያ አኒሜሽን ስቱዲዮ ጋር ከተገናኘው እና ፀረ-አዘርባጃን ከሆነው “ኪል ዲም 2020” ጋር ተመሳሳይ የታሪክ አካሄድ እና ዘይቤ አለው።

በፈረንሳይ የጂኦፖሊቲክስ ኢንስቲትዩት የሩሲያ ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኬቨን ሊሞኒየር “ዩክሬን ኢንክ” እና “ስቶፕ ናዚ ጌምስ” የመሳሰሉ የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮች መነሻቸው ፈረንሳይ ነው የሚለው የክሬምሊን አባባል ብዙም አላስገረማቸውም።
ፈረንሳይ ለዩክሬን የምታደርገው ድጋፍ እየጨመረ እና ግልጽ የሆነ አጋርነት ማሳየቷ ለሩሲያ የሐሰት መረጃ ሥራዎች ዋነኛ ዒላማ ሆናለች ብለዋል።
“ማክሮን ወታደሮችን ወደ ዩክሬን ስለመላክ ያደረጓቸው ንግግሮች በሞስኮ እንደ ስጋት ታይተዋል። ከብሬግዚት ወዲህ ፈረንሳይ በአውሮፓ ውስጥ ብቸኛዋ የኑክሌር ባለቤት ነች። ለዚህም ነው ሩሲያ ፈረንሳይ ላይ እያነጣጠረች ያለችው” ሲሉ ሊሞኒየር አስታውቀዋል።
ሩሲያ “አሁንም ለሩሲያ ጥቅም የሚሠሩ ፈረንሳውያን እንዳሉ ለማሳመን ትፈልጋለች” ሲሉ አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, ukraine-inc.info
መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው “ዘ ግሎባል ዲስንፎርሜሽን ኢንዴክስ” ባልደረባ እንደሆኑት ዞኢ ፉሬል ደግሞ የቪዲዮዎቹ ዋና ዓላማ ከተለያዩ አገራት እና የባህል ዳራዎች የመጡ ታዳሚዎችን በቀላሉ ለማግኘት ነው።
“ሩሲያ መልዕክቷን ለማስተላለፍ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅማለች። ሁሉም ሰው አርቲን (በሩሲያ መንግሥት ቁጥጥር ስር ያለና የክሬምሊን ሐሰተኛ መረጃን የሚያጋራ መገናኛ ብዙኃን) አይከታተልም። እነዚህ ቪዲዮዎች ግን በጣም ተደራሽ ናቸው። መልዕክታቸው ሁሉን አቀፍ ነው” ይላሉ።
የፀረ-ዜሌንስኪ ፕሮፓጋንዳው ቪዲዮ 13ኛ ክፍል ሊወጣ በመሆኑ ተመልካቾች እንዳያመልጣቸው በቅድሚያ እንዲመዘገቡ ማስታወቂያ እየተሠራ ነው።












