ትራምፕ እና ምክትላቸው በቻይና በሚደገፉ መረጃ መንታፊዎች ዒላማ ሳይሆኑ አይቀርም ተባለ

ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትላቸው ሆነው እየተወዳደሩ የሚገኙት ቬንስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከቻይና ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ መረጃ መንታፊዎች ዶናልድ ትራምፕ ምክትል በመሆን እየተወዳደሩ ከሚገኙትን ሴናተር ጄዲ ቫኔስ ጋር የተገናኙ ስልኮችን እና ድረ ገጾችን ሰብረው ለመግባት መሞከራቸውን ተነገረ።

ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የመረጃ ምንጮች በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ እንደገለጹት የትራምፕ እና ቫንስ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ሁለቱ ተወዳዳሪዎች የሚጠቀሙበት ስልክ የሳይበር ጥቃቱ ዒላማ ካደረጋቸው መካከል ሊሆኑ እንደሚችሉ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

የካማላ ሃሪስ ምክትል ሆነው እየተወዳደሩ የሚገኙት ክሪስ ዋልዝ ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንዲሁ ግለሰቡ የጥቃቱ ዒላማ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እስካሁን ድረስ በመረጃ ሰርሳሪዎቹ እና መንታፊዎቹ እጅ የገባ መረጃ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።

የአሜሪካ ፍትህ መሥሪያ ቤት እና የአገር ውስጥ የደኅንነት ተቋሙ ኤፍቢአይ የዕጩዎቹ ዒላማ መሆንን በተመለከተ ተጠይቀው ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ኤፍቢአይ እና ኢንፍራስትራክቸር ሴኩሪቲ ኤጀንሲ (CISA) በጋራ ባወጡት መግለጫ “ከቻይና መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ፈቃድ ሳያገኙ የንግድ የቴሌኮሚዩኒኬሽን መሠረተ ልማቶችን መጠቀማቸውን ተከትሎ” የአሜሪካ መንግሥት ምርመራ እያደረገ ነው ብለዋል።

አክለውም “አጠራጣሪ እንቅስቀቃሴዎችን” በመለየት “ዒላማ የተደረጉ ኩባንያዎች ወዲያውኑ እንዲያውቁት የተደረገ ሲሆን፣ የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያገኙ እንዲሁም ሌሎች ዒላማ ሊሆኑ የሚችሉ አካላት መረጃው እንዲደርሳቸው” መደረጉን እና ምርመራው የቀጠለ መሆኑን አስታውቀዋል።

“በአሜሪካ የሚገኙ የተለያዩ አካላት ይህንን ስጋት ለመቀልበስ በጋራ እየሠሩ ሲሆን፣ በተጨማሪም የንግድ የግንኙነት መስመሮች የበለጠ የበይነ መረብ ደኅንነታቸውን የመጠበቅ አቅማቸውን ለማጠናከር በትብብር እየሰሩ” መሆኑንም ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ስለመረጃ ምዝበራው ምንም ዓይነት መረጃ ሳያቀርብ “ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ እንዳይገቡ ለመከላከል የተደረገ” ሲል ዲሞክራቶችን ተጠያቂ አድርጓል።

ሕግ አስከባሪ አካላት የመረጃ ስርሰራውን እንደ ስለላ እንጂ የምርጫ ዘመቻው ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ያለመ ነው ብለው አለመውሰዳቸውን ምንጮች ለሲቢኤስ ገልጸዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ኩባንያዎች በመረጃ መንታፊዎች ዒላማ ተደርገው ነበር።

በዚህ ጥቃት ዒላማ ከተደረጉት መካከል አንዱ ቬርዞን ሲሆን፣ መረጃ መንታፊዎቹ ትራምፕን እና ምክትላቸው ሆነው እየተወዳደሩ የሚገኙትን ግለሰብ መረጃዎች ዒላማ ስለማድረጋቸው ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቦ ነበር።

የቬሪዞን ቃል አቀባይ ሪች ያንግ በመግለጫቸው ላይ፣ ኩባንያው ስለ ጉዳዩ እውቀት እንዳለው ገልጸው በርካታ የአሜሪካ ቴሌኮሚዩኒኬሽን አቅራቢዎች ዒላማ መደረጋቸውን አስታውቀው ነበር።

አክለውም ቬሪዞን የሕግ አስከባሪ አካላት ለሚያደርጉትን ምርመራ እንዲሁም ለወደፊት ተመሳሳይ ችግር ቢፈጠር እንዴት ሊፈታ እንደሚችል ለመለየት በጋራ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ በዚህ ዓመት በመረጃ ሰርሳሪዎች ዒላማ ሲደረግ ይህ ሁለተኛው ነው።

ሦስት ከኢራን መንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ኢራናውያን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን ሆን ብለው አደጋ ላይ ለመጣል ሞክረዋል በሚል መስከረም ወር ላይ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የተለያዩ ተቋማት እና ባለሥልጣናት በአሜሪካ ምርጫውን ጨምሮ የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት ሊኖር አንደሚችል ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት ጄክ ሱሊቫን “ተቀናቃኞቻችን የአሜሪካ ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ፣ አሻራቸውን ለማሳረፍ መሞከራቸው አይቀርም” ብለው ነበር።

አክለውም “ይህ ግልጽ ሊሆን ይገባል፤ ያንንም ለማስቀረት በርካታ ሥራዎችን እየሠራን ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።

ባለፈው ዓመት በጥር ወር የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክርስቶፈር ሬይ በተገኙበት በኮንግረስ የቻይና መረጃ ሰርሳሪዎች በአሜሪካ “ውዥንብር ለመፍጠር እና ጉዳት ለማድረስ” አስበው እየሠሩ ነው በሚል ጉዳዩ ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል።